ለኢትዮጵያ የተቋቋመው የተመድ መርማሪ ኮሚሽን የጊዜ ቆይታ ሳይራዘም መቅረቱ ወቀሳ ቀረበበት

የኢትዮጵያ ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን እንዲያጣራ በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የተቋቋመው መርማሪ ኮሚሽን የጊዜ ቆይታ እንዲራዘም ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ አለመቅረቡን ተከትሎ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ወቀሳ አቀረቡ።

የፕሪቶሪያን ስምምነት ተከትሎ የጦር ወንጀሎች መፈጸም ስለመቀጠላቸው እና በአገሪቱ ከፍተኛ እና መጠነ ሰፊ የመብት ጥሰቶች እንደሚፈጸሙ በርካታ ማመላከቻዎች እንዳሉ ኮሚሽኑ እየተናገረ ባለበት ወቅት ነው የመርማሪ ቡድኑ የሥራ ጊዜ ከአንድ ወር በኋላ ሊጠናቀቅ ይችላል የተባለው።

የመርማሪ ኮሚሽኑ የጊዜ ቆይታ እንዲራዘም ለማድረግ ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ በ54ኛው የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ረቡዕ መስከረም 23/ 2016 ዓ.ም መቅረብ ነበረበት።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ሂውማን ራይትስ ዋች እና ሌሎች ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ኮሚሽኑ እንዲቋቋም ቁልፍ ሚና የተጫወተው የአውሮፓ ኅብረት ቀነ ገደቡ ሳያልፍ የኮሚሽኑ የሥራ ቆይታ እንዲራዘም የሚያደርገውን ረቂቅ ውሳኔ ሃሳብ እንዲያቀርብም ተደጋጋሚ ጥሪ ሲያደርጉ ነበር።

የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ቡድኑ በርካታ ግጭቶችን እያስተናገደችው ባለችው ኢትዮጵያ የጦር ወንጀሎች እና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ጨምሮ የከፉ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን እንደሚቀጥሉ ከፍተኛ ስጋት እንዳለው መስከረም 22/ 2016 ዓ.ም ባወጣው አዲስ ሪፖርቱ አስታውቆ የገለልተኛ መርማሪዎችን አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥቶ ነበር።

“በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እየተፈጸሙ እንዲሁም ወደፊት ሊፈጸሙ የሚችሉ ጥሰቶች እጅጉን እያሳሰቡን ነው” ሲሉም የኮሚሽኑ ሊቀመንበር መሃመድ ቻንዴ ኦትማን ተናግረዋል።

ለሁለት ዓመታት የዘለቀውን ደም አፋሳሽ ጦርነት የቋጨው የፕሪቶሪያው ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነትን ተከትሎ የጦር ወንጀሎች እና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች መቀጠላቸውን ኮሚሽኑ መስከረም 07/2015 ዓ.ም. ባወጣው ሁለተኛ ሪፖርቱ አስታውቆ ነበር።

የሰብዓዊ መብቶች የባለሙያዎች ቡድን ከዚህ ቀደም የመዘገባቸው የጅምላ ግድያ፣ መድፈር፣ ረሃብ፣ አስገዳጅ መፈናቀል እና የጅምላ እስር ከስምምነቱ በኋላ ቀጥለዋል ብሏል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ጀምሮ ተቃውሞ እያቀረበ ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የተመድ የሰብዓዊ መብቶች የባለሙያዎች ቡድን የሥራ ጊዜ እንዲበቃ እና በአገሪቱ የሕግ ማዕቀፍም ጥሰቶች እንዲታዩ ከፍተኛ ጫና ሲያደርግ ቆይቷል።

በጉዳዩ ላይ የተጠየቁት የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል አቀባይ ለገሰ ቱሉ “የመርማሪ ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ ያለው ታሪክ የመጨረሻ ነው” ሲሉ በጽሁፍ ምላሸ መስጠታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

አክለውም “ስለሞተ ጉዳይ መነጋገር አያስፈልግም” ብለዋል ሚኒስትሩ።

ኮሚሽኑ በበኩሉ የኢትዮጵያ መንግሥት ጥሰቶችን በብቃት መከላከልም ሆነ መርመር እንደተሳነው እና በምትኩ አካታች እና ግልጽነት የሚጎድለው ችግር ያለበትን የሽግግር ሂደት መጀመሩን አመልክቷል።

የመርማሪ ኮሚሽኑን የሥራ ጊዜ ለማራዘም የሚያስፈልገው የውሳኔ ሃሳብ አለመቅረቡ የጊዜ ቆይታው እንዳይራዘም እንደሚያደርገው የተናገሩት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሂውማን ራይትስ ዋች የአፍሪካ ቀንድ ዳይሬክተር ላቲሺያ ባደር፣ ይህም ኢትዮጵያ በምክር ቤቱ በሰብዓዊ መብቶች አጀንዳ እንዳትሆን ያደርጋታል ብለዋል።

ላቲሺያ ኮሚሽኑ እንዲቋቋም ከፍተኛ ሚና የተጫወተው የአውሮፓ ኅብረት በጦርነቱ መጀመሪያ አካባቢ ለተፈጸሙ ጥሰቶች ተጠያቂነት እንዲኖር ያሳያውን ቁርጠኝነት የጣሰ ውሳኔ ነው ሲሉ ወቅሰውታል።

“ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ዘግናኝ ጥሰቶች ሰለባ ለሆኑ ለቁጥር የሚታክቱ ተጠቂዎች እጅግ አስከፊ ወቅት ነው። በጦርነቱ በደል እና ጥሰቶች የተፈጸመባቸው ተጎጂዎች በኢትዮጵያ መንግሥት ምርመራም ሆነ ሂደቶች እንደማያምኑ ለኮሚሽኑ ተናግረዋል” ብለዋል።

የኮሚሽኑ የሥራ ጊዜ መራዘም ጥያቄ ውስጥ የገባው በአውሮፓ ኅብረት ብቻ ሳይሆን “ከኮሚሽኑ መቋቋም ጀምሮ እየተቃወመች የነበረችው ኢትዮጵያ ሥራውን ለማደናቀፍ ያደረገችው የተቀናጀ ጥረትም ነው” ሲሉም ላቲሺያ ተችተዋል።

የሂውማን ራይትስ ዋች የአውሮፓ ኅብረት ዳይሬክተር ፊሊፔ ዳም በበኩላቸው በጄኔቫ የሚገኘውን የተመድ የኅብረቱ ተቀማጭ ተልዕኮ ወቀሳ አቅርበውበታል።

“የአውሮፓ ኅብረት የኢትዮጵያን ሁኔታ ለማጣራት ረቂቅ ውሳኔ ባለማቅረቡ ከሚቆምላቸው ሁሉም መርሆዎች በተቃራኒ ቆሟል። ኅብረቱ ያስተላለፈው ውሳኔም ለመጀመሪያ ጊዜ የተባበሩት መንግሥታትን ቁልፍ የማጣራት ተግባር እንዲቀበር አድርጎታል” ብለዋል።

ሌላኛው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ የአውሮፓ ኅብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባል አገራት በዚህ ውሳኔያቸው ለጦርነቱ ሰለባዎች እና ተጎጂዎች ጀርባቸውን ሰጥተዋል በማለት ሁኔታውን “አሳፋሪ” ሲል ጠርቶታል።

ኮሚሽኑ ከተቋቋመ በኋላ በጦርነቱ የተፈጸሙ ጥሰቶችን የሚመለከቱ የተለያዩ ሪፖርቶችን ያወጣ ሲሆን፣ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት የተፈጸሙ ጥሰቶችን እንድመረምር መንግሥት አልፈቀደልኝም ሲልም ወቀሳውን በተደጋጋሚ ማቅረቡም ይታወሳል።

ኮሚሽኑ “የዘር ማጥፋት፣ የጦር ወንጀሎች እና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን” ጨምሮ በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙ አሰቃቂ ወንጀሎች በአገሪቷ ውስጥ ሊቀጥሉ እንደሚችሉ በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት በዝርዝር አካቷል።

“ሁኔታዎች በበለጠ እየከፉ እና እየተባባሱ ሊሄዱ የሚችሉበት አሳማኝ ስጋቶች ተደቅነዋል። የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ትኩረት እንዲሰጣቸው ምርመራዎች መቀጠል አለባቸው እንዲሁም አስከፊ እና አሳዛኝ የሆኑ ሁኔታዎችን መከላከል ይቻል ዘንድ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ግዴታ ተጥሎበታል” ሲሉም ሌላኛው ኮሚሽነር ስቲቨን ራትነር ተናግረው ነበር።

ቡድኑ የፕሪቶሪያ ስምምነት የጦር ወንጀሎችን ማስቆም እንዳልቻለ እና የኤርትራ ወታደሮች፣ የአማራ ኃይሎች እና ሚሊሻዎች በትግራይ ክልል መዋቅራዊ የሆነ መድፈርን ጨምሮ ሌሎች የመብት ጥሰቶችን እየፈጸሙ ነው ብሏል።

በምዕራብ ትግራይ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች ከስምምነቱም በኋላ ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ መደረጉንም ነው ቡድኑ የመዘገበው።

አገሪቱ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የተለያዩ ማዕዘኖች ግጭቶች እየተካሄዱ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የከፉ የመብት ጥሰቶች ሊከሰቱ እንዲሚችሉ እና የምሥራቅ አፍሪካንም የፀጥታ ሁኔታ አደጋ ላይ ሊጥል እንደሚችል የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያዎች ቡድኑ አስጠንቅቋል።

በአማራ ክልል እንዲሁም በሌሎች ክልሎች እንደ አስፈላጊነቱ ተፈጻሚ ይሆናል ከተባለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር ተያይዞ፣ በክልሉ ነዋሪዎች በጅምላ መታሰራቸው ቢያንስ አንድ የድሮን ጥቃት እንዲሁም በርከት ያሉ የመብት ጥሰቶች ስለመፈጸማቸው አሳማኝ ሪፖርቶች ደርሰውኛል ብሏል።

ኮሚሽኑ በአሮሚያ ክልል ውስጥ የመንግሥት ኃይሎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ ስቅይት እና እንግልትን ጨምሮ እስሮችን እያካሄዱ መሆኑንም ነው ባወጣው ሪፖርት የመለከተው።

ከዚህ ቀደም 19 ገጾች ባሉት የመጀመሪያው ግኝት ሪፖርቱ በጦርነቱ መደፈር፣ ወሲባዊ ጥቃቶች፣ የዘፈቀደ ግድያ እና ረሃብ እንደ ጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ መዋላቸውን ይፋ አድርጓል።

ኢትዮጵያ በበኩሏ በአገሪቱ በጦርነቱ የተፈጸሙ ጥሰቶችን መርምሮ ተጠያቂነት ለማስፈን የሽግግር ፍትሕ ሂደት እንደጀመረች አስታውቃለች።

ኮሚሽኑ በበኩሉ ኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ሂደቱን ያቋቋመችው ዓለም አቀፍ ምርመራዎችን ለማምለጥ እንዲሁም ጥሰት የተፈጸመባችን ያገለለ ነው ሲልም ተችቶታል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በትግራይ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም. ተቀስቅሶ ወደ አጎራባቾቹ የአማራ እና የአፋር ክልልሎች በተዛመተው የእርስ በርስ ጦርነት የተፈጸሙ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች፣ የስደተኛ ሕጎች እና ሌሎች ጥሰቶችን የሚያጣራ ገለልተኛ ምርመራ የሚያካሂድ መርማሪ ቡድን ለማቋቋም የውሳኔ ሃሳብ ያሳለፈው ታኅሣሥ 2014 ዓ.ም. ነበር።

በአውሮፓ ኅብረት ጠያቂነት በተካሄደው የምክር ቤቱ ልዩ ስብሰባ በሰብዓዊ ምክር ቤቶች ፕሬዝዳንት የሚሾሙ አባላትን የያዘ ዓለም አቀፍ ኮሚሽን ለማቋቋም ውሳኔ ላይ የደረሰው በዚያ ወቅት ነው።

በወቅቱም ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ መርማሪ እንዲቋቋም የተላለፈውን ውሳኔ እንደማትቀበለው እና አንዳንዶች የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔን ለፖለቲካ ዓላማ ማራመጃነት ሲጠቀሙበት በድጋሚ ማየቷ እንዳሳዘናት በመግለጽ በውስጥ ጉዳይዋ ጣልቃ ለመግባት የሚደረግ ሙከራን እንደማትቀበል፣ እንደማትተባበርም ገልጻ ነበር።

የምርመራ ቡድኑ የካቲት 23/2014 ዓ.ም. ሲቋቋም የቀድሞ የዓለም አቀፉ ወንጀል ፍርድ ቤት ዐቃቤ ሕግ ፋቱ ቤንሱዳ ሊቀ መንበር ሆነው ተሹመው ነበር።

ፋቱ ቤንሱዳ በዩናይትድ ኪንግደም የጋምቢያ ከፍተኛ ኮሚሽነርነትን ሥልጣን መቀበላቸውን ተከትሎ ከኮሚሽኑ ሊቀመንበርነት ለቀዋል።

በእሳቸውም ፈንታ በመጀመሪያ አባል ሆነው የተሰየሙት ኬንያዊቷ ጠበቃ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ካሪ ቤቲ ሙሩንጊ ቡድኑን በሊቀ መንበርነት ሲመሩ ቆይተዋል።

በሚቺጋን የሕግ ትምህርት ቤት ፕሮፌሰር የሆኑት አሜሪካዊ ስቲቨን ራትነር በጦርነቱ ተፈፅመዋል ለተባሉ ዓለም አቀፍ ወንጀሎች መርማሪ ቡድን አባል ሆነው መሾማቸውም ይታወሳል።