ቲፋኒ ሐዲሽ ዕጽ ተጠቅማ በማሽከርከር ከተያዘች በኋላ እርዳታ እደሚያስፈልጋት ተናገረች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኤርትራዊ የዘር ሐረግ ያላት እውቋ አሜሪካዊት ኮሜዲያን ቲፋኒ ሐዲሽ ዕጽ ተጠቅማ ስታሽከረክር በቁጥጥር ስር ከዋለች በኋላ የባለሙያ ድጋፍ ለማግኘት እንደምትጠር አስታወቀች።
ቲፋኒ ባለፈው አርብ ሞተሩ ያልጠፋ መኪናዋ ውስጥ እራሷን ስታ ተገኝታ የቤቨርሊ ሂልስ ፖሊስ በቁጥጥር ስር አውሏት ነበር።
ከክስተቱ በኋላ የ43 ዓመቷ ቲፋኒ “ይህ ዳግም አይከሰትም” ስትል ለኢንተርቴይንመት ቱናይት ተናግራለች።
ቲፋኒ “ከልክ እንዳላልፍ ድጋፍ ለማግኘት እጥራለሁ” ብላለች።
ቲፋኒ በዕለቱ ስታሽከረክረው የነበረው ቴስላ መኪናዋ ራሱን በመኪና ማቆሚያ ስፍራ ላይ ቢያቆምም የመኪናው የኋላ አካል መንገድ ዘግቶ መቆሙን እርሷም እንቅልፍ እንደጣላት ለኢንተርቴይንመት ቱናይት አስረድታለች።
ቲኤምዚ የተባለው ድረ-ገጽ ያገኘው ተንቀሳቃሽ ምስል ቲፋኒ እጇ ታስሮ ወደ ፖሊስ መኪና እንድትገባ ስትደረግ አሳይቷል።
የግራሚ እና የፕራይምታይም ኤሚ አዋርድ አሸናፊዋ ቲፋኒ ክስተቱ ካጋጠመበት ዕለት አንድ ቀን ቀደም ብሎ በሎስ አንጀለስ ከተማ የታንክስጊቪንግ በዓልን ምክንያት በማድረግ በነጻ የማኅብረሰብ አገልግሎት ላይ ስትሳተፍ ነበር።
ቲፋኒ በአደንዛዥ ዕጽ ተጽእኖ ስር ሆና በማሸከርከር በቁጥጥር ስር ስትውል ይህ የመጀመሪያዋ አይደለም።
እአአ በ2022 በጆርጂያ ግዛት ፒችትሪ ከተማ አደንዣዥ ዕጽ ወስዳ ስታሽከረክር ተገኝታ በቁጥጥር ስር ውላ ነበር።
ቲፋኒ እአአ 2017 ላይ ገርልስ ትሪፕ በተሰኘ ኮሜዲ ፊልም ላይ ከጃዳ ስሚዝ እና ኩዊን ላቲፋ ጋር ተጣምራ በሠራችው ሥራ ትልቅ ዝናን አትርፋለች።
እአአ በ2018 ላይ በሳተርደይ ናይት ላይቭ ተሳትፎዋ የኤሚ ሸልማት ያገኘች ሲሆን፣ እአአ 2021 ላይ ደግሞ ብላክ ሚትዝቫህ በተባለው የኮሜዲ ሥራዋ ምርጥ የኮሜዲ አልበም በሚል የግራሚ አሸናፊ ሆናለች።












