ሳይንቲስቶች አዲስ ያገኟትን የንብ ዝርያ 'ሉሲፈር' ብለው ሰየሙ

አውስትራሊያ ብቻ የሚኖሩ አዲስ የንብ ዝርያዎችን ያገኙት ሳይንቲስቶች መጠሪያውን 'ሉሲፈር' ማለታቸው አነጋጋሪ ሆኗል።

ሴቶቹ የንብ ዝርያዎች ትንንሽ ቀንዶች ስላሏቸው 'Megachile Lucifer' ተብለው ተሰይመዋል።

ተመራማወዎቹ፤ በምዕራብ አውስትራሊያ፣ ጎልድፊሽ ግዛት በቀላሉ የማይደረስበት የዱር አበባ እያጠኑ ሳለ ነበር 'ሉሲፈርን' ያገኙት።

"በጣም ልዩ የሆነ ዝርያ ነው፤ ቀንዳቸውም የተለየ ቅርጽ አለው" ሲሉ ገልጸውታል።

ሴቶቹ ንቦች ቀንዳቸውን ራሳቸውን ለመከላከል ይጠቀሙበታል። የአበባ ማር ወይም ወለላ የሚቀስሙትም በቀንዳቸው ነው። ጎጆ ሲቀልሱ ቁሳቁስ ለመሰብሰብ ቀንዳቸውን ይጠቀማሉ።

በከርተን ዩኒቨርስቲ ምርምር የምታደርገው የጥናቱ መሪ ዶ/ር ኪት ፕሬደጋስት እንዳለችው፤ ንቧን 'ሉሲፈር' ያለችው ኔትፍሊክስ ላይ ያለውን 'ሉሲፈር' ተከታታይ ፊልም እያየች ስለሆነ ነው።

"በ20 ዓመታት ውስጥ እነዚህ የንብ ዝርያዎች አልታዩም ነበር። ሴቶቹ ንቦች ፊታቸው ላይ አስደናቂ ቀንድ አላቸው" ስትል ታስረዳለች።

"ስለ ንቦቹ ስጽፍ 'ሉሲፈር' ፊልምን እያየሁ ነበር። ፊልሙን ስለምወደው ነው በርዕሱ የሰየምኳቸው" ትላለች የጥናቱ መሪ።

'ሉሲፈር' በላቲን ቋንቋ 'ባለ ብርሃን' ማለት ነው። ግኝቱ፤ አገር በቀል ስለሆኑ ንቦች ውይይት ለመጀመር 'ብርሃን ይፈነጥቃል' በሚል ስያሜውን እንደመረጠች ትናገራለች።

በመላው ዓለም የመጥፋት አደጋ የተደቀነባቸው የአበባ ዝርያዎችን በየቦታው ለማዳረስ ንቦች ያላቸው ሚና ቀላል አይደለም።

በአውስትራሊያ የተገኙት ንቦች የሚኖሩበት አካባቢ ጥብቅ የዱር አበባ የሚበቅልበት እንደሆነ 'ሃይመኖፓትራ ሪሰርች' መጽሔት ላይ የወጣው ዘገባ ይጠቁማል።

"ንቦቹ የተገኙት የመጥፋት አደጋ የተደቀነባቸው አበቦች አቅራቢያ ነው። ንቦቹም አበቦቹም መኖሪያ አካባቢያቸው አደጋ ውስጥ ወድቋል። የአየር ንብረት ለውጥ ለኅልውናቸው አስጊ ነው" ትላለች ዶ/ር ኪት።

በአየር ንብረት ለውጥ እየተፈተነች ላለችው ምድር ተስፋ የሚሰጡ እና ለመጥፋት የተቃረበ ብዝኃ ሕይወትን የሚታደጉ ዝርያዎች እምብዛም ትኩረት እንዳልተሰጣቸው ታስረዳለች።

"የትኞቹ የንብ ዓይነቶች ሊጠፉ እንደተቃረቡ ወይም ሕይወታቸው በየትኞቹ የአበባ ዓይነቶች እንደሚቀጥል ባለማወቅ ንቦቹንም ብዝኃ ሕይወቱንም እያጣን ነው።"