የማዳጋስካር ወታደራዊ መኰንኖች ሥልጣን መቆጣጠራቸውን አስታወቁ

ወታደራዊ መኰንኖች

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የማዳጋስካር ፕሬዝዳንት አንድሪ ራጀሊና 'ደኅንነቱ ወደተጠበቀ ሥፍራ' መወሰዳቸውን ተከትሎ ወታደራዊ መኰንኖች ሥልጣን መያዛቸውን አስታወቁ።

ከቤተ መንግሥት መግለጫ የሰጡት ኮሎኔል ማይክል ራንድሪናሪራ እንዳሉት፤ መታደራዊ መኰንኖች መንግሥት ያቋቁማሉ።

በቀጣይ ሁለት ዓመታት ውስጥ ምርጫ እንደሚካሄድም ገልጸዋል። ኮሎኔሉ የምርጫ ኮሚሽንን አግደዋል።

ለሳምንታት በቀጠለው የወጣቶች ተቃውሞ ወደ ሥልጣን የመጡት ወታደራዊ መኰንኖች "ንቅናቄውን የጀመሩት ወጣቶች ስለሆኑ ፍላጎታቸውን እናሟላለን" ብለዋል።

ተቃዋሚዎች እና ወታደሮች ፕሬዝዳንቱ ከሥልጣን ገሸሽ በመደረጋቸው ደስታቸውን እየገለጹ ነው።

በማዳጋስካር መዲና አንታናናሪቮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች ሰንደቅ አላማ ሲያውለበልቡ ታይተዋል።

'ፐርሶኔል አድምንስትሬሽን ኤንድ ቴክኒካል ኤንድ አድምንስትሬቲቭ ሰርቪስ ኮርፕስ' የተባለው ወታደራዊ ክንፍ የማዳጋስካር ጠንካራው ሠራዊት ነው።

የዚህ ወታደራዊ ክንፍ መሪ ኮሎኔል ማይክል ራንድሪናሪራ ሥልጣኑን መረከባቸውን አስታውቀዋል።

ይህ ወታደራዊ ክንፍ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የፕሬዝዳንቱ ደጋፊ ነበር። ከሰሞኑ ግን የወጣቶችን ተቃውሞ በመደግፍ ወደ ሥልጣን መጥቷል።

ኮሎኔል መፈንቅለ መንግሥት ተካሂዷል የሚለውን ባይቀበሉም የአገሪቱ አዲስ መሪ ተብለው ተሰይመዋል።

ፕሬዝዳንቱ "ደኅንነቱ የተጠበቀ ቦታ" እንደሚገኙ ከመገለጹ በዘለለ የት እንዳሉ እስካሁን በይፋ አልታወቀም።

የግድያ ሙከራ የተደረገባቸው ፕሬዝዳንቱ በፌስቡክ ባስተላለፉት መልዕክት "የወታደራዊ መኰንኖች እና የፖለቲከኞች ቡድን እኔን ለመግደል አሲረዋል" ብለዋል።

ከግድያ ሙከራው በኋላ በፈረንሳይ ወታደራዊ አውሮፕላን ከአገር እንደወጡ ያልተረጋገጡ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ።

ወጣት ተቃዋሚዎች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

አሜሪካ ሁሉም ወገኖች "ሕገ መንግሥቱን በመከተል ሰላማዊ አማራጭ ይፈልጉ" ስትል አሳስባለች።

ኮሎኔል ማይክል ራንድሪናሪራ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ "ማዳጋስካር ፕሬዝዳንት ስለሌላት ቀውስ ውስጥ ናት" ብለዋል።

ከሁለት ሳምንታት በፊት የውሃ እና መብራት መቆራረጥን በመቃወም አደባባይ የወጡት ወጣቶች ተቃውሞውን አቀጣጥለው ገፍተውበታል።

ሥራ አጥነት፣ ሙስና እና የኑሮ ውድነት ዋነኛ የተቃውሞው ማጠንጠኛ ናቸው። ሰልፈኞች ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ተጋጭተው ቢያንስ 22 ሰዎች ሲገደሉ 100 የሚደርሱ እንደተጎዱ የመንግሥታቱ ድርጅት ገልጿል።

የማዳጋስካር መንግሥት የተገለጸው ቁጥር "ሐሰተኛ ነው" ብሏል።

ነጋዴ እና ዲጄ የነበሩት የማዳጋስካር ፕሬዝዳንት አንድሪ ራጀሊና በአንድ ወቅት የአገሪቱ ተስፋ ተደርገው ይታዩ ነበር።

በ34 ዓመታቸው ሥልጣን ሲይዙ የአፍሪካ ወጣቱ መሪ ተብለውም ነበር። ለአራት ዓመታት አገሪቱን ከመሩ በኋላ እአአ በ2018 በድጋሚ ወደ ሥልጣን ተመልሰዋል።

ለወዳጅ ዘመዶቻቸው ሥልጣን በመስጠት እና በሙስና የሚከሰሱት ፕሬዝዳንቱ ከወጣቶች ጠንካራ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል።

የወጣቶች የአደባባይ ተቃውሞ ሳይባባስ በፊት ፕሬዝዳንቱ መንግሥታቸውን በትነዋል።

የራሳቸውን ፓርቲ አባላት ጨምሮ የሕዝብ ተወካዮች ፕሬዝዳንቱ እንዲከሱ ድምጽ ሰጥተዋል።

የአፍሪካ ኅብረት የወታደራዊ መኰንኖች "ጣልቃ ገብነት" እንደማያስፈልግ በመጥቀስ "ሕገ መንግሥታዊ ያልሆነ የመንግሥት ለውጥን" እንደማይቀበል አስታውቋል።

ከማዳጋስካር 30 ሚሊዮን ሕዝብ 75 በመቶ የሚሆነው ከድህነት ወለል በታች እንደሚኖር የዓለም ባንክ መረጃ ያመለክታል።