በሩሲያ በነዳጅ ማደያ ላይ በደረሰ ፍንዳታ በርካታ ሰዎች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, @mchs_official
በደቡባዊቷ ሩሲያ ዳግስታን ክልል በሚገኝ የነዳጅ ማደያ ላይ በደረሰ ፍንዳታ እና ቃጠሎ ቢያንስ 27 ሰዎች ተገደሉ።
ፍንዳታው የተከሰተው በካስፒያን ባህር ዳርቻ በምትገኘው በክልሉ መዲና ማካችካላ ነው።
በአገሬው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 3፡40 ላይ የደረሰው አደጋ በርካታ ሰዎችንም ያቆሰለ ሲሆን ትክክለኛው መንስዔም አልታወቀም።
የፍንዳታውን ሁኔታ የሚያሳዩ ፎቶዎች በከፍተኛ ሁኔታ የሚንቦገቦግ የእሳት ነበልባል አሳይተዋል።
በስፍራውም ላይ በርካታ የእሳት አደጋ መከላከያ ሞተሮችም ይታያሉ።
በፍንዳታው በከፋ የተጎዱትን ለመታደግና ወደ ሞስኮ ለመውሰድ ሄሊኮፕተርን ጨምሮ 260 ያህል የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች መሰማራታቸውን የአገሪቱ የድንገተኛ አደጋ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በአደጋው ከሞቱት መካከል ሶስት ህጻናት እንደሚገኙበት የሩሲያው ኢንተርፋክስ ዶክተሮችን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
እሳቱ 600 ካሬሜትር በሚሸፍን ስፍራ ላይ መዛመቱን እና ተጨማሪ የፍንዳታ አደጋዎችም ሊያጋጥሙ እንደሚችሉም አክሏል።
የሩሲያው ጋዜጣ ኢዝቬሺያ አንድ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ እማኝን ጠቅሶ እንደዘገባው እሳቱ ከነዳጅ ማደያው ትይዩ ባለ የመኪና ማቆሚያ ስፍራ መነሳቱን ተናግረዋል።
“ከፍንዳታው በኋላ ሁሉም ነገር በላያችን ላይ ወደቀ። ምንም ነገር ማየት አልቻልንም” ሲሉም ይኸው የዓይን እማኝ ተናግረዋል።
የሩሲያ መርማሪ ኮሚቴ በበኩሉ እሳቱ የተቀሰቀሰው በመኪና ጥገና ስራ ወቅት ላይ ሲሆን በፍጥነትም ፍንዳታ ማስከተሉንም አስታውቋል።
ለበርካታ ሰዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት የሆነውን ይህንን ፍንዳታ እዚህ እንዴት እንደደረሰም ለማወቅ የወንጀል ምርመራ መክፈቱንም ኮሚቴው ገልጿል።
የዳግስታን ሪፐብሊክ ከ83ቱ የሩስያ ፌዴሬሽን አንዱና የአገሪቱም ደቡባዊ ክፍል ነው። መዲናዋ ማካችካላ ከሞስኮ በ1 ሺህ 600 ኪሎሜትር ርቀት ትገኛለች።












