የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በ16 ተቃውሞ እና በ12 ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ ጸደቀ

የምክር ቤቱ አባላት ድምጽ ሲሰጡ

የፎቶው ባለመብት, hopr/fb

የምስሉ መግለጫ, የምክር ቤቱ አባላት ድምጽ ሲሰጡ

የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአማራ ክልል ላይ ያሳለፈውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአብላጫ ድምጽ አጸደቀ።

ምክር ቤቱ ዛሬ ሰኞ ነሐሴ 8/2015 ዓ.ም. ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአማራ ክልል እንዲተገበር ያሳለፈውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በ12 ድምጸ ተአቅቦ በ16 ተቃውሞ በአብላጫ ድምጽ መጽደቁን ምክር ቤቱ አስታወቀ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዙር 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባ የቀረበለትን የአስቸኳይ ጊዜ ረቂቅ አዋጅ በተመለከተበት ጊዜ የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ በልጅጌ የአዋጁን አስፈላጊነት ለምክር ቤቱ አስረድተዋል።

በአማራ ክልል በትጥቅ የተደገፈ ጥቃት መፈጸሙን እና አደጋው በመደበኛው የሕግ ሥነ ሥርዓት ለመቆጣጠር የማይቻልበት ሁኔታ መፈጠሩ፣ ይህም የክልሉን መንግሥታዊ ሥርዓት አደጋ ላይ የጣለ በመሆኑ አገርን ከጥፋት ለመታደግ እና የሕዝቦችን ሰላም እና ደኅንነት ለማስጠበቅ አዋጁ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሐምሌ 28/2015 ዓ.ም. በደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ ውሳኔ በሰጠው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ ላይ 360 የምክር ቤት አባላት መገኘታቸው ተዘግቧል።

የመንግሥት ተጠሪን ማብራሪያን ተከትሎ የምክር ቤቱ አባላት ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ ተቃውሞን ካሰሙ አንዱ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው መሆናቸውን ቢቢሲ ከአንድ የምክር ቤት አባል ሰምቷል።

የቀድሞው የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ የነበሩት እና የገዢው ብልጽግና አባል የሆኑት አቶ ገዱ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተችተው ተቃውሟቸውን ገልጸዋል ተብሏል።

የመንግሥት ተጠሪ በጉዳዩ ላይ በሰጡት ማብራሪያ እና በቀረበው ረቂቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ የምክር ቤት አባላት አስተያየቶች እና ጥያቄዎችን አቅርበው፣ በፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ማብራሪያ እና ምላሽና ሰጥተዋል።

ይህንንም ተከትሎ በአስቸኳይ በስብሰባው ላይ ከተገኙት የምክር ቤቱ አባላት መካከል አስራ ስድስቱ አዋጁን የተቃወሙት ሲሆን 12 ድምጻቸውን አቅበዋል።

ምክር ቤቱ በተጨማሪም ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ አባላትን በአንድ ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ አጽድቋል።

በዚህም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርዱን በሰብሳቢነት አቶ አዝመራው አንዴሞ፣ ምክትል ሰብሳቢነት ነጃት ግርማ (ዶ/ር) እንዲመሩ የተሰየሙ ሲሆን፤ አቶ ሣዲቅ አደም፣ አቶ መስፍን እርካቤ፣ አብርሃም በርታ (ዶ/ር )፣ ወ/ሮ ፍሬህይወት ተሾመ እና አቶ ወንድሙ ግዛው ደግሞ አባል ሆነዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የመብት ተሟጋቾች በአማራ ክልል የተጣለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጊዜ እንዲያጥር እና ግጭቱ በሰላማዊ መንገድ በውይይት እንዲፈታ ሲጠይቁ ቆይተዋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከቀናት በፊት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ ለመወሰን አስቸኳይ ስብሰባ ለተጠራው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰብአዊ መብቶች ትንታኔ እና ምክረ ሐሳቦችን ማቅረቡን ከቀናት በፊት አሳውቆ ነበር።

ኮሚሽኑ የአዋጁ አስፈላጊነት፣ ተመጣጣኝነት እና ሕጋዊነት እንዲሁም አዋጁ ተፈጻሚ የሚሆንበት አካባቢ እና የጊዜ ወሰን፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እና የዳኞችን ያለምክር ቤቱ ውሳኔ አለመያዝ እና ያለመከሰስ ልዩ መብት እና ሌሎችም ሊገደቡ ስለማይችሉ መብቶች ጥበቃን እንዲመረምር ነበር ለምክር ቤቱ ሃሳብ ያቀረበው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በመከላከያ ኃይል እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደው ባለው ግጭት በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች እና የሆስፒታል ምንጮች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ባለፈው ሳምንት በአማራ ክልል ትላልቅ ከተሞች ባሕር ዳር፣ ጎንደር እና ደብረ ብርሃን ግጭቱ ተባብሶ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሕጻናትና አረጋውያንን ጨምሮ በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን፣ በንብረትም ላይ ጉዳት መድረሱን ቢቢሲ ከነዋሪዎች እና ከሆስፒታል ምንጮች ሰምቷል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ አርብ አመሻሽ ነሐሴ 5/2015 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫም ስለደረሰው ጉዳት ዝርዝር መረጃ ባይሰጥም፣ በክልሉ በተከሰተው ግጭት የንጹሃን ሕይወት መጥፋቱን፣ ንብረት መውደሙን እና ዘረፋ መፈጸሙን ገልጿል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ቀደም ብሎ ግጭት የተከሰተባቸውን ስድስት የአማራ ክልል ከተሞች (በባሕር ዳር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ደብረ ብርሃን፣ ላሊበላ፣ ጎንደር እና ሸዋ ሮቢት) ከታጣቂዎች ነጻ የማድረጉ ተግባር እየተጠናቀቀ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፣ በከተሞቹ ላይ ሠዓት እላፊ ገደብ መጣሉን አስታውቋል።

በእነዚህ ከተሞች አንጻራዊ መረጋጋት የታየባቸው ቢሆንም በሌሎች የክልሉ ከተሞች ግጭቶች እንደቀጠሉ መሆናቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በፍኖተ ሠላም እና ቡሬ ከተሞች ግጭቶች የተካሄዱ ሲሆን የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና ከተማ በሆነችው ፍኖተ ሰላም ከተማ እሁድ ነሐሴ 07/2015 ዓ.ም. በተፈፀመ ጥቃት ቢያንስ 25 ሰዎች ሲገደሉ፣ ከ50 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ነዋሪዎች እና የሆስፒታል ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በአዲስ አበባ እና በተለያዩ ከተሞች በአማራ ተወላጆች ላይ የጅምላ እስሮች እየተፈፀሙ መሆናቸው እየተዘገበ ሲሆን፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ በበኩሉ የምክር ቤት አባሉን ክርስቲያን ታደለን ጨምሮ ከታጣቂ ቡድኑ ጋር ግንኙነት አላቸው ያላቸውን 23 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር አውሎ እየመረመረ መሆኑን አስታውቋል።

የተባበሩት መንግሥታት፣ የተለያዩ አገራት፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ግጭቱ በውይይት እንዲፈታ ጥሪ ማቅረባቸውን ቀጥለዋል።