በአማራ ክልል ግጭት የመንግሥት ባለስልጣናት መገደላቸውን ኢሰመኮ ገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በአማራ ክልል ግጭት በአስቸኳይ እንዲቆም በጠየቀበት መግለጫው በክልሉ የመንግሥት ባለስልጣናት መገደላቸውን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ ዛሬ ነሐሴ 8/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በተለያዩ ደረጃ ያሉ የአማራ ክልል ባለስልጣናት ዒላማ ተደርገው ነበር ያለ ሲሆን በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች መንግሥታዊ መዋቅር ከመፍረሱም በላይ በባለስልጣናት ላይ ግድያም ተፈጽሟል ብሏል።
ኮሚሽኑ በአማራ ክልል ከተሞች እና በከተሞች ዙሪያ ግጭቶች መከናወናቸውን አረጋግጫለሁ ያለ ሲሆን በእነዚህ ግጭቶች ከባድ የጦር መሳሪያዎች ጥቅም ላይ መዋላቸውን፣ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን እና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ገልጿል።
መንገድ ለመዝጋት የሞከሩ ተቃዋሚዎች እና ሰላማዊ ሰዎች ስለመገዳላቸው፣ በክልሉ ያሉ እስር ቤቶች እና ፖሊስ ጣቢያዎች ዘረፋ ተፈጽሞባቸው ጦር መሳሪያ እና ተተኳሾች ስለመዘረፋቸው፣ ፍርድ የሚጠባበቁ እስረኞች እና ፍርደኞች ከእስር ቤት እንዲያመልጡ ስለደመረጋቸው ኢሰመኮ ገልጿል።
በአማራ ክልል በርካታ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ፣ የውሃ፣ የባንክ፣ ሆስፒታል፣ የትምህርት ቤት፣ የስልክ እና ኢንተርኔት አገልግሎቶች ተቋርጠው ነበር።
በክልሉ በነበረው ግጭት ነዋሪዎች ለደኅንነታቸው በመስጋታቸው ከዕለታዊ እንቅስቃሴ ታግደው በቤት ውስጥ እራሳቸውን ሸሽገው ለመቀመጥ መገደዳቸውን የገለጸ ሲሆን፤ የንግድ ተቋማትም ዝግ ሆነው እንደነበረ አስታውሷል።
የአማራው ክልል ግጭት እና መንገድ መዘጋት የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ስራን ማስተጓጎሉን የገለጸው ኢሰመኮ በሰሜን ጎንደር ዞን እና በዳባት ወረዳ የሚገኙ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ደኅንነት አደጋ ላይ የጣለ ክስተት ነው ብሏል።
ባለፈው ሚያዚያ ወር የፌደራል መንግሥቱ የክልል ልዩ ኃይሎች ፈርሰው ወደ ተለያዩ የፀጥታ እና የመከላከያ መዋቅሮች እንዲገቡ ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ በአማራ ክልል የተከሰተው ተቃውሞ እየተጠናከረ ሄዶ፣ በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል ግጭቶች እና የተኩስ ልውውጦች ሲካሄዱ ቆይተዋል።
ባለፉት ሳምንታት ደግሞ ግጭቱ ተባብሶ ከክልሉ አቅም ውጪ በመውጣት የፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ እንዲገባ ተጠይቆ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ታውጇል።
በእረፍት ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአማራ ክልል የተከሰተውን የፀጥታ ችግር ተከትሎ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርምሮ ለመወሰን ዛሬ አስቸኳይ ስብሰባ ያደርጋል።
የከተማ ውስጥ ግጭት
ኢሰመኮ የአማራ ከተሞች የከተማ ውስጥ ግጭት ማስተናገዳቸውን ገልጿል።
በተለይ ደግሞ የሰሜን ሸዋ ዞን መቀመጫ ደብረ ብርሃን እሁድ ሐምሌ 30 እና ነሐሴ 1/2015 ዓ.ም. ሰዎች በብዛት በሚኖሩባቸው 4 ቀበሌዎች ግጭት ተደርጎ እንደነበረ አስታውሷል።
በዚህም ምክንያት በከባድ ጦር መሳሪያ ፍንጣሪ እና በተባራሪ ጥይት በሆስፒታል፣ በቤተ-ክርስቲያን፣ በትምህር ቤት ውስጥ እና በመኖሪያ መንደሮቻቸው ውስጥ የነበሩ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል ብሏል።
የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በደብረ ብርሃን፣ ፍኖተ ሰላም እና ቡሬ ከተሞች ሰላማዊ ሰዎች እና በመኖሪያ ሕንጻዎች ላይ ጉዳት ያደረሱ የአየር ጥቃቶች ስለመፈጸማቸው ተዓማኒነት ያላቸው ሪፖርቶች ደርሰውኛል ብሏል።
በባሕር ዳርም በበርካታ ስፍራዎች ሰላማዊ ሰዎች በመንገዶች እና በመኖሪያ ቤቶች መገደላቸውን የገለጸ ሲሆን፤ ሙሉ ምርመራ በማድረግ የማጣራት ስራ የሚያስፈልጋቸው ሪፖርቶች በሸዋ ሮቢት በጸጥታ ኃይሎች ከሕግ ውጭ የሆነ ግድያ መፈጸማቸውን ጠቁመዋል ብሏል።
በአዲስ አበባ ደግሞ የአማራ ብሔር ተወላጅ የሆኑ ሰላማዊ ሰዎች በስፋት መታሰራቸውን፤ አልፎ አልፎም ጥገኝነት ጠያቂ ሊሆኑ የሚችሉ ኤርትራውያን ስደተኞች ታስረዋል ብሏል ኢሰመኮ በመግለጫው።
ግጭት ይቁም
ኢሰመኮ በዛሬ መግለጫው ላይ በአማራ ክልል ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ ግጭት እንዲቆም ሲል ጠይቋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአማራ ክልል ግጭት ውስጥ የገቡ አካላት ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ ግጭት አቁመው ወደ ንግግር እንዲገቡ አሳስቧል።
ኢሰመኮ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ በንግግር ለመፍታት እንዲቻል መንግሥት እና የፋኖ ታጣቂዎች ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ ለማቆም መስማማት አለባቸው ብሏል።
ኮሚሽኑ በአማራ ክልል ከተሞች በአገር መከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የነበረው የከተማ ውስጥ ግጭት ጋብ ያለ ቢሆንም አሁንም በተቀረው የክልሉ አካባቢዎች ግጭት በመቀጠሉ ዘላቂ ሰላማዊ አማራጭ እስኪተገበር ድረስ በክልሉ ያለው የጸጥታ ሁኔታ አሳሳቢ ነው ብሏል።
ኮሚሽኑ በአማራ ክልል ካለው የጸጥታ ሁኔታ ጋር በተያያዘ መግለጫዎችን ማውጣቱን ያስታወሰ ሲሆን የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ ለመወሰን አስቸኳይ ስብሰባ ለተጠራው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰብዓዊ መብቶች ትንታኔ እና ምክረ ሐሳቦችን ማቅረቡን ጨምሮ ገልጿል።
ኢሰመኮ የፌደራል መንግሥቱ መጠነ ሰፊ የሆነ እስሮችን እንዲያቆም ጠይቆ እስረኞች ታስረው የሚገኙበትን ሁኔታ እንዲጎበኝ ፍቃድ እንዲሰጠው ጠይቋል።
እንዲሁም ኮሚሽኑ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ)፣ የአፍሪካ ኅብረተ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዲሁም በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ ዓለም አቀፉ ማኅብረሰብ አባላት በሁለቱ አካላት መካከል ንግግር እንዲጀመር ሁኔታዎችን እንዲያመቻቹ ጠይቋል።












