ጫና የበዛባቸው ባይደን የዩክሬኑን መሪ “ፕሬዝደንት ፑቲን” ብለው መጥራታቸው አነጋጋሪ ሆነ

ሐሙስ ምሽት ጋዜጣዊ መግለጫ የጠሩት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን የዩክሬኑ አቻቸው ቮሎድሚር ዜሌንስኪን “ፕሬዝደንት ፑቲን” ብለው መጥራታቸው መነጋገሪያ ሆኗል።

በሚቀጥለው የአሜሪካ ምርጫ ፓርቲያቸውን ወክለው ይወዳደራሉ ተብለው የሚጠበቁት ባይደን የጤናቸው ነገር አሳሳቢ ቢሆንም ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ተደጋጋሚ ጥያቄ ጤናማ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ባይደን፤ ሌጋሲያቸውን ለማስቀጠል ሳይሆን እየታገሉ ያሉት በአውሮፓውያኑ 2021 የጀመሩትን ሥራ ለመጨረስ እንደሆነ አንድ ሰዓት ያክል በፈጀው መግለጫ ተናግረዋል።

“እንደ ቀድሞው መንቀሳቀስ አቅቶኝ ሥራዬን መጨረስ ካልቻልኩ ነው እንደበቃኝ ምልክት የሚሆነው” ያሉት ባይደን “ነገር ግን ምንም ዓይነት የድካም ምልክት አይታይብኝም” ሲሉ አስረግጠዋል።

አንዳንዶች ይህ የባይደንን ጥንካሬ ያሳያል ሲሉ ሌሎች ደግሞ ፕሬዝደንቱ ሽንፈት አለመቀበል መፈለጋቸው ነው ግትር ያደረጋቸው የሚል አስተያየት እየሰጡ ነው።

ጋዜጣዊ መግለጫው ከተጠናቀቀ ከደቂቃዎች በኋላ በርካታ የዲሞክራቲክ ፓርቲ አባላት ፕሬዝደንት ባይደን ከሥልጣናቸው እንዲወርዱ ጠይቀዋል።

ባይደን ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው የመጀመሪያ ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ የገዛ ምክትላቸው ካማላ ሀሪስን “ምክትል ፕሬዝደንት ትራምፕ” ብለው ሲጠሩ በርካቶች በድንጋጤ ተመልክተዋቸዋል።

ይህ የሆነው ከአንድ ሰዓት በፊት ከኔቶ አባላት ጋር ፕሮግራም የነበራቸው ባይደን የዩክሬኑ አቻቸው ቮሎድሚር ዜሌንስኪን “ፕሬዝደንት ፑቲን” ሲሉ አስተዋውቀው በሥፍራው የነበረውን ታዳሚ ካስደነገጡ በኋላ ነው።

ባይደን፤ ዜሌንስኪን በተመለከተ የፈፀሙትን ስኅተት ወዲያው ያረሙ ሲሆን ካማላ ሀሪስን በተለመከተ የፈፀሙት የቃላት ስህተት ግን ነባር የካቢኔ አባላቶቻቸውን ጭምር አፍ ያስከፈተ ነበር።

የዲሞክራቲክ ፓርቲ አባላት ፕሬዝደንቱ ሌሎች ስህተቶችን ሠርተው የፓርቲውን ስም የበለጠ ከማጉደፋቸው በፊት አንድ እርምጃ መወሰድ አለበት ይላሉ።

ፕሬዝደንቱ ግን ይህን ሐሳብ በፍፁም የሚቀበሉት አይመስሉም። ስህተት እየሠሩም ቢሆን በሚቀጥለው ኅዳር በሚደረገው ምርጫ ከትራምፕ ጋር ለመፋጠጥ ቆርጠው የተነሱ ይመስላል።

ከጋዜጠኞች በርካታ ጥያቄ የቀረበላቸው ባይደን ፈገግ እያሉ በሰጡት ምላሽ ከቻይናው ፕሬዝደንት ዢ ጂንፒንግ እና ከሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር የሚፎካከር አቅም ላይ እንደሆኑ ተናግረዋል።

ባይደን ከዚህ ቀደም ጤናቸው ሳይጓደል አይቀርም የሚያስብሉ ምልክቶች ቢያሳዩም ከሁለት ሳምንታት በፊት ከትራምፕ ጋር በነበራቸው ክርክር ወቅት ያሳዩት አቋም ነው ለነቀፌታና ትችት የዳረጋቸው።

የምርጫ ቅስቀሳው ገና አልተጀመረም የሚሉት ባይደን በሚቀጥለው ወር በሚካሄደው የዲሞክራቲክ ፓርቲ ስብሰባ ወቅት የፓርቲያቸው አባላት የፈለጉትን ዕጩ ማቅረብ እንደሚችሉ ቢናገሩም “የማይሆን ነው” ሲሉ ቀልድ ለበስ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ከቡድናቸው የሚቀጥለው ምርጫ ማሸነፍ እንደማይችሉ የሚያሳይ መረጃ ካገኙ ራሳቸውን እንደሚያገሉ ቢናገሩም ቁጥሮች እንደሚያሳዩት ባይደን እና ትራምፕ አሁንም ተናንቀዋል። ሐሙስ ዕለት በወጣ የሕዝብ ድምፅ ባይደን በአንድ ነጥብ ከትራምፕ ዝቅ ብለው ይገኛሉ።

ነገር ግን ከምርጫው በፊት የሚሰበሰብ “ማንን ትመርጣላችሁ?” የሚል የሕዝብ ድምፅ ምን ያህል አስተማማኝ ነው የሚለው አጠያያቂ ቢሆንም፤ ባይደን እየደረሰባቸው ያለው ጫና እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ የሚመጣ አይመስልም።

የ81 ዓመቱ ፕሬዝደንት ባይደን በሚቀጥለው ሰኞ ኤንቢሲ ከተሰኘው ቴሌቪዥን ጋር ከበድ ያለ የሚባል ቃለ-መጠይቅ ይጠብቃቸዋል።