ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በአገሪቱ የተነሳውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ካቢኔያቸውን በተኑ
የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ባለፉት ሳምንታት የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ ሚኒስትሮቻቸውን ከሥልጣን አሰናብተዋል።
ፕሬዝዳንት ሩቶ ዛሬ ሐሙስ ከሰዓት በኋላ በቤተ-መንግሥታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ሪጋቲ ጋሻግዋ እና የካቢኔው ዋና ፀሐፊ ሙሳሊያ ሙዳቫዲ ሲቀሩ ሌሎቹ የመንግሥታቸው ባለሥልጣናት ከሥራ ማባረራቸውን ይፋ አድርገዋል።
ፋይናንስ ቢል 2024 የተሰኘው የአገሪቱ ዜጎች ላይ ግብር የሚጥለው ሕግ ወደ ፓርላማ መላኩን ተከትሎ ነበር በኬንያውን ወጣቶች የተመራው ተቃውሞ ፕሬዝዳንቱ ሥር ነቀል እርምጃ እንዲወስዱ ያደረጋቸው።
ለሰዎች ሕይወት መጥፋት እና ለንብረት መውደም ምክንያት የሆነውን ተቃውሞ ተከትሎ ፕሬዝዳንቱ ይህን ፖሊሲ ተግባራዊ እንደማያደርጉት መግለጻቸው አይዘነጋም።
ፕሬዝዳንቱ በመግለጫቸው ካቢኔያቸውን የበተኑት ሕዝቡ ያነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ መሆኑን አሳውቀው “ኬንያውያንን በመስማት ካቢኒዬን መርምሬ ነው የወሰንኩት” ብለዋል።
ሩቶ፤ አዲስ እና ሰፋ ያለ መንግሥት ለመመሥረት ከሕዝባቸው ጋር ውይይት እንደሚያደርጉም አሳውቀዋል።
በሕጉ መሠረት ከሥራቸው የማይባረሩት ምክትል ፕሬዝዳንቱ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው የሚያገለግሉት የካቢኔው ዋና ፀሐፊ ሥልጣናቸው ላይ ይቆያሉ።
የኬንያው ፕሬዝዳንት ባለፈው ሳምንት አሁን ኤክስ በተባለው በቀድሞው ትዊተር ገፃቸው የአገሪቱን ወጣቶች ጠርተው ማነጋገራቸው ይታወሳል።
ከተቃዋሚዎቻቸው ጋር በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በተካሄደው ውይይት የተፋጠጡት ፕሬዝዳንቱ ቀጥተኛ እና መሸፋፈን ያልታየባቸው ጠንካራ ጥያቄዎች ቀርበውላቸው ነበር።
በመድረኩ የመናገር ዕድል ያገኙት ተሳታፊዎች ፕሬዝዳንት ሩቶ እና መንግሥታቸው እስካሁን ያስመዘገቡትን እና ባህሪያቸውን በተመለከተ አንስተው አብጠልጥለዋቸዋል።
ፕሬዝደንቱ የግብር ጭማሪ የሚጥለውን ሕግ ውድቅ ከማድረጋቸውም በላይ ሕዝባዊውን ተቃውሞ ተከትሎ ለፓርላማ አባላት ሊደረግ የነበረው የደሞዝ ጭማሪ ታግዷል።
የግብር መደራረቦች እና ከፍተኛ የኑሮ ውድነትን እየታገለ ያለው የኬንያ ሕዝብ ተጨማሪ ግብር አንከፍልም የሚል ተቃውሞ ካሰማ በኋላም ነው የፕሬዝዳንት ሩቶ መንግሥት የፋይናንስ ሕጉን የሰረዙት።
ሩቶ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በተነሳው ከፍተኛ ሕዝባዊ ተቃውሞ 39 ሰዎች መገደላቸውን የአገሪቱ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ገልጿል።
ወጣት ኬንያውያን ማኅበራዊ የትስስር መድረኮችን በመጠቀም ባካሄዱት ተቃውሞ የግብር ሕጉ በአገሪቱ ፓርላማ ቢጽድቅም ፕሬዝዳንቱ ተግባራዊ እንዳይሆን አግደውታል።
ፕሬዝዳንት ሩቶ አዲሱ ታክስ የአገሪቱን ዕዳ ለመቀነስ ዋነኛው አማራጭ መሆኑን የተከራከሩ ሲሆን፣ ነገር ግን ሕዝቡ የማይፈልገው ከሆነ ተግበራዊ እንደማይሆን በመግለጽ የመንግሥትን ወጪዎች መቀነስ ላይ እንደሚያተኩሩ አሳውቀዋል።
ወደ 40 ለሚጠጉ ሰዎች ሞት ምክንያት እንደሆነ የተነገረው ተቃውሞ ከፋይናንስ ሕጉ ውድቅ መሆን ባሻገር ፕሬዝዳንቱ ከሥልጣን እንዲወርዱ አስከመጠየቅ ደርሶ ነበር።
ፕሬዝዳንት ሩቶ የሕዝቡን በተለይም የወጣቱን ጥያቄ የሚያዳምጥ እና መፍትሄ የሚፈለግ ቡድን ያቋቋሙ ሲሆን፣ በመንግሥት ውስጥ ያለውን ሙስና ለመወጋት ጠንካራ እርምጃ እንደሚወስዱ በተደጋጋሚ ቃል ገብተዋል።