ትራምፕ የዩኬና የፈረንሳይ መሪዎች የዩክሬንን ጦርነት ለማስቆም "ምንም አላደረጉም" ሲሉ ወቀሱ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የፈረንሳዩ አቻቸው ኢማኑኤል ማክሮን እና የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር የዩክሬንን ጦርነት ለማስቆም "ምንም አልሠሩም" ሲሉ ወቀሱ።
ትራምፕ ይህንን ያሉት ሁለቱ መሪዎች በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ዋይት ሐውስ ተጉዘው ጉብኝት እንደሚያደርጉ በሚጠበቅበት ወቅት ነው።
ትራምፕ በተጨማሪም የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ በሰላም ድርድሩ ላይ የሚመዙት ምንም ዓይነት ካርድ እንደሌላቸው ጠቅሰው "በውይይቱ ላይ መገኘቱ ጠቃሚ አይደለም" ብለዋቸዋል።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈጸመችውን ወረራ ተከትሎ ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ)፣ ፈረንሳይ እና ምዕራባውያን አጋሮች ለኪዬቭ የጦር መሳሪያ እና ሌሎች እርዳታዎችን ሲያቀርቡ ቆይተዋል።
የአሜሪካ እና ሩሲያ በሳዑዲ አረቢያ ካደረጉት የሰላም ንግግር አንድ ቀን ቀደም ብሎ ዩክሬን እና አውሮፓ ከሰላም ድርድሩ ሊገለሉ ይችላሉ በሚል ስጋት የአውሮፓ መሪዎች በዩክሬን ላይ የመከረ ጉባኤያቸውን በፈረንሳይዋ መዲና ፓሪስ አድርገዋል።
ትራምፕ የዩኬ እና የፈረንሳይን መሪዎች ቢተቹም ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ መሪዎቹንም ሲያወድሷቸው ተሰምተዋል።
ፕሬዚዳንት ማክሮንን እንደ "ጓደኛ" እንደሚያዩዋቸው ተናግረው፤ የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትርን ደግሞ "በጣም መልካም ሰው" ሲሉ ጠርተዋቸዋል።
ፕሬዚዳንት ማክሮን በመጪው ሰኞ ዋሽንግተን ዲሲን ይጎበኛሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ስታርመር ደግሞ ሐሙስ ዕለት ወደ ዋይት ሐውስ ያቀናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር የዩክሬን ደኅንንትን ለማረጋገጥ ወታደሮቻቸውን ለማሰማራት ዝግጁ እና ፈቃደኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የአውሮፓ መሪዎች ከሩሲያ ጋር ለመደራደር ፈቃደኛ ባይሆኑም በዩክሬን ስላለው ጦርነት በየጊዜው እየተገናኙ ሲመክሩ ቆይተዋል።
የዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ በኋላ አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ አውስትራሊያ፣ ካናዳ እና ጃፓን ከ20 ሺህ በላይ ማዕቀቦችን በሩሲያ ላይ ጥለዋል።
በርካታ የአውሮፓ አገራትም ለዩክሬን ድጋፍ እና እርዳታ መስጠት የሚያስችላቸውን ስምምነቶች ተፈራርመዋል።
ከጥቂት ወራት በፊት የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ስታርመር ከፕሬዚዳንት ዜሌንስኪ ጋር አንድ ስምምነት ከከተፈራረሙ በኋላ "ከእናንተ ጋር ነን፤ ዛሬ ወይም በሚቀጥለው ዓመት ብቻ አይደለም፤ ለሚቀጥሉት 100 ዓመታት፣ ይህ አስከፊ ጦርነት ካበቃ በኋላ እና ዩክሬን ነጻ ሆና እንደገና ስታንሰራራም" ሲሉ ነግረዋቸው ነበር።
የትራምፕ የዩክሬን ልዩ መልዕክተኛ ኬት ክሎግ ሐሙስ ዕለት በኪዬቭ ተገኝተው ከዜሌንስኪ ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ "አምባገነን" ብለው የጠሯቸውን ዜሌንስኪን ልዩ መልዕክተኛው ከአንድ ቀን በኋላ "ደፋር መሪ" ሲሉ አሞካሽተዋቸዋል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከፎክስ ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ ሩሲያ እና ዩክሬን ያለእሳቸው ተሳትፎ የሰላም ንግግር መጀመር አይፈልጉም ብለዋል።
በመቀጠልም ዜሌንስኪን ጠንከር ባለ ቃል ተችተዋል "ይህንን ሰው ለዓመታት እየተመለከትኩት ነበር፤ ከተሞቹ ሲፈርሱ፣ ህዝቡ ሲገደል፣ ወታደሮቹ ሲረግፉ። የመደራደሪያ ምንም ዓይነት ካርድ የለውም። የሚያሳምም ነው። በቅቶኛል" ብለዋል።
በቅርብ ቀናት ዜሌንስኪ ከተለያዩ የዓለም መሪዎች ጋር የስልክ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ መሪዎቹም ዩክሬን በሰላም ንግግሮች ውስጥ እንድትሳተፍ ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸውላቸዋል።












