ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሩሲያ ጥቃቶች በመጠናከሩ የዩክሬን ጦር እያፈገፈገ መሆኑን የሰራዊቱ አዛዥ ተናገሩ
ሩሲያ በተለያዩ ግንባሮች የምታደርገው ጥቃቶች በመጠናከሩ ምክንያት የዩክሬን ጦር ተቆጣጥሯቸው ከነበሩ ቦታዎች እየለቀቀ መሆኑን የዩክሬን ሰራዊት ዋና አዛዥ ተናገሩ።
የዩክሬን ጦር መልሶ ተቆጣጥሯቸው ከነበሩት ምስራቃዊ ዶኔትስክ ግዛቶች ለቆ መውጣቱን ዋና አዛዡ ኦሌክሳንደር ሲይርስኪ ገልጸዋል።
ሩሲያ ባላት የሰው ኃይል እና የከባድ መሳሪያዎች የበላይነት ለመጠቀም እየሞከረች እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን ዩክሬን ለመልሶ ማጥቃት የሚያስፈልጋትን አዳዲስ የጦር መሳሪያዎች ልገሳ ከአሜሪካ እየጠበቀች ትገኛለች።
አሜሪካ ባለፈው ሳምንንት 61 ቢሊዮን ዶላር ወታደራዊ ዕርዳታ ለዩክሬን ለማድረግ ተስማምታለች።
የዩክሬን ኃይሎች በጦር ግንባሮች ላይ በሰው ኃይል፣ ጥይቶች እና በአየር መቃወሚያ እጥረቶች ለወራት እየታገሉ ይገኛሉ።
“በጦር ግንባሮች ላይ ያለው ሁኔታ እየከፋ ይገኛል” ሲሉ ጄነራል አሌክሳንደር ሲይርስኪ በቴሌግራም መልዕክታቸው በለጠፉት ጽሁፍ አስፍረዋል።
ሩሲያ በየካቲት ወር የአቪዲቪካን ግዛቶች ከተቆጣጠረች በኋላ የተቋቋመው የመከላከያ ግንባር በሆነት የዶኔትስክ አካባቢ የሰፈረው የዩክሬን ኃይሎች ከአንዳንድ ቦታዎች መውጣታቸውን አረጋግጠዋል።
ጦርነቱ በአብዛኛው የተካሄደው ሩሲያ የአቪዲካን ግዛቶች ከያዘች በኋላ በቀጣይነት ለመቆጣጠር እየሞከረች ባለችው ቻሲቭ ያር አካባቢ መሆኑ ተገልጿል።
የሩሲያ ኃይል እነዚህን አዳዲስ ግዛቶች በመቆጣጠርም እየገፋ መሆኑን ጄነራሉ አምነዋል።
ሩሲያ “ታክቲካዊ ስኬቶችን አግኝታለች” ብለዋል ጄነራሉ።
ጄነራሉ አክለው እንደተናገሩት በሰው ኃይል የደረሰባቸውን ኪሳራ ለመተካት የተረፉት የዩክሬን ኃይሎች በእነዚያ አካባቢዎች እየተፈራረቁ እንደሚገኙም ነው የገለጹት።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ ጦሩ ከአቪዲቪካ በስተሰሜን 10 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኘውን ኖቫባክሙቲካ ግዛት መያዙን አስታውቋል።
ጄነራል አሌክስሳንደር ሲይርስኪ የዩክሬን ጦር ኃይሎች ዋና አዛዥ ሆነው የተሾሙት በያዝነው ዓመት የካቲት ወር ላይ ነው።
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ቮሌድሚር ዘሌንስኪ እና የቀድሞው ጦር አዛዥ ቫለሪ ዛሉዝህኒ መካከል አለመግባባት እንደተፈጠረ ከተነገረ በኋላ ነው የተሾሙት።
የዩክሬን ብሔራዊ ጥበቃ አዛዥ አሌክሳንደር ፒቭኔንኮ በበኩላቸው በሩሲያ ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው የዩክሬን ሁለተኛ ከተማ ካርኪቭ የሩስያ ኃይሎች የመግፋት ሙከራ ሊያደርጉ እንደሚችሉ በዚህ ሳምንት ተናግረዋል።
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በባለፈው ሳምንት ከአንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት ተቃውሞ ቢቀርብም የ95 ቢሊዮን ዶላር የእርዳታ ፓኬጅ ለዩክሬን፣ እስራኤል እና ታይዋን ፈርመዋል።