የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ተጽዕኗቸው ከፍተኛ ነው የተባለውን ምክትል ፕሬዚዳንት አሰናበቱ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ተተኪ ሊሆኑ ይችላሉ የተባሉትን ምክትል ፕሬዚዳንታቸውን ቤንጃሚን ቦል ሜልን በአስደንጋጭ ሁኔታ ከሥልጣናቸው አሰናበቱ።
ኪር ቦል ሜልን የጄኔራልነት ማዕረጉን በመግፈፍ ከብሔራዊ ደህንነት አገልግሎት አሰናብተዋል። እንዲሁም የቦል ሜል የቅርብ አጋር ናቸው የተባሉትን የማዕከላዊ ባንክ ገዥ እና የገቢዎች ባለሥልጣን ኃላፊን አሰናብተዋል።
በብሔራዊ ቴሌቪዥን በተላለፈ መግለጫ ላይ ስለተሰናበቱት ባለሥልጣናት ምንም ዓይነት ማብራሪያ አልተሰጠም።
ፕሬዚዳንቱ ይህንን ውሳኔ የወሰዱት በቅርቡ በእርሳቸው እና በተቃዋሚ መሪ ሪክ ማቻር መካከል የተደረሰው ሥልጣንን የመጋራት ስምምነት ከፈረሰ በኋላ አገሪቱ ወደ የፖለቲካ አለመረጋጋት እና የእርስ በርስ ጦርነት ልትገባ ትችላለች የሚል ስጋት እየጨመረ በመጣበት ወቅት ነው።
የ47 ዓመቱ ቦል ሜል ከሥልጣን በመባረራቸው ቅሬታ አንደተሰማቸው አልገለፁም።
ለኪር በጻፉት ደብዳቤ ላይ "የደቡብ ሱዳንን ሕዝብ በምክትል ፕሬዝዳንትነት የማገልገል ዕድል ስለሰጣችሁኝ ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ" ብለዋል።
"ደቡብ ሱዳን እና ኤስፒኤልኤም (ገዢው ፓርቲ) በእርስዎ አመራር ስር ከፍ ብለው እንደሚቀጥሉ ሙሉ እምነት አለኝ።"
ቦል ሜል ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው የተሾሙት ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ አንጋፋው ፖለቲከኛ እና ጄኔራል ጄምስ ዋኒ ኢጋን በመተካት ነበር።
በተጨማሪም የኤስፒኤልኤም ተቀዳሚ ምክትል ሊቀ መንበር መሆን የቻሉ ሲሆን ተንታኞች የበለጠ ሥልጣን እንደተሰጣቸው እና የ74 ዓመቱ ኪርን ሊተኩ ይችላሉ ሲሉ ተንብየው ነበር።
ፕሬዚዳንቱ በኋላም በብሔራዊ ደኅንነት አገልግሎት (ኤንኤስኤስ) ውስጥ ወደ ሙሉ ጄኔራልነት ደረጃ ከፍ አድርገዋቸዋል።
ቤል እድገቱን ያገኙት እንደ አውሮፓውያኑ በ2017 በሙስና ወንጀል ዩናይትድ ስቴትስ ማዕቀብ ከጣለችባቸው በኋላ ሲሆን ማዕቀቡ በዚሁ ዓመትም አንዲቀጥል ተደርጓል።
የአሜሪካ ግምጃ ቤት ቦል ሜል የኪር ዋና የፋይናንስ አማካሪ በማለት ገልጿቸዋል። የኪር ጽህፈት ቤት ይህንን የአሜሪካ መንግሥት መግለጫ ውድቅ አድርጓል።
ቦል ሜል በእርሳቸው ላይ ለተሰነዘረው የሙስና ክስ በቀጥታ ምላሽ አልሰጡም።
ፕሬዚዳንቱ ከሥልጣናቸው የተነሱትን ምክትል ፕሬዚዳንት የሚተካው ማን እንደሆነ እስካሁን ድረስ አላሳወቁም።
ከሥልጣን መነሳታቸው የተሰማው በኤስፒኤልኤም ውስጥ የሥልጣን ሽኩቻ መኖሩ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት መወራቱን ተከትሎ ነው።
ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን ቦል ሜል በመንግሥት ውስጥ "ከፋፋይ" እንደነበሩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ከሥልጣን መነሳቱ ጥሩ ነው" ሲሉ አክለዋል።
በመዲናይቱ ጁባ የሚኖር የታክሲ ሹፌርም ከኃላፊነት መነሳታቸውን በደስታ እንደሚቀበለው ገልጿል።
"ሁሉም ሰው ይጠላቸዋል። በትውልድ ከተማቸው አዊል እንኳን ከሥልጣናቸው በመባረራቸው ደስታ ፈጥሯል። ለፕሬዚዳንት ኪርም ቢሆን ደስተኛ ነን" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግሯል።
ቦል ሜል ከሥልጣን መነሳታቸው በይፋ ከመገለፀው በፊት በዋና ከተማዋ ጁባ በሚገኝ መኖሪያቸው እና ቢሯቸው የሚገኙ ጥበቃዎች እንዲነሱ መደረጋቸው ተገልጿል።
በነዳጅ ሀብቷ የበለፀገችው ደቡብ ሱዳን ከሱዳን በመገንጠል ነጻ አገር ሆና የተመሠረተችው እአአ በ2011 ነው።
ከሁለት ዓመት በኋላ በኪር እና ማቻር መካከል አለመግባባት ከሰፈነ በኋላ በእርስ በርስ ጦርነት ስትታመስ ቆይታለች።
እአአ የ2018 የተፈረመው ጦርነቱን ያስቆመው የሥልጣን መጋራት ስምምነት የተለያዩ ተግዳሮቶች እየገጠሙት ሲመጣ በአገሪቱ ውጥረት እየጨመረ እንዲሁም አልፎ አልፎ ግጭቶች መፈጠር ጀምረዋል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት ለማካሄድ ታቅደው የነበሩ አገራዊ ምርጫዎች ሁለት ጊዜ የተራዘሙ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፕሬዚዳንቱ ታማኝ ኃይሎች እና በታጣቂዎች መካከል የሚደረገው ውጊያ ተባብሷል።
ማቻር ከምክትል ፕሬዝደንትነት ተነስተው በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በነፍስ ግድያ፣ የአገር ክህደት እና በሰብዓዊነት ላይ በተፈፀሙ ወንጀሎች ክስ ተመስርቶባቸዋል።
ይህ እርምጃ ውጥረቱን የሚያባብስ እና ዳግም ሕዝባዊ አመፅ ሊቀሰቅስ ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።
የማቻር ክስ አሁንም በፍርድ ቤት በመታየት ላይ ነው።
ቃል አቀባያቸው የተከሰሱበትን ክስ "ያልተፈጠረውን ለመፈለግ የተወሰደ ፖለቲካዊ እርምጃ" ሲሉ ገልፀውታል።
ክሱ የተመሠረተው ከማቻር ጋር ግንኙነት አለው የተባለው የሚሊሺያ ቡድን ጥቃት ፈጽሞ መንግሥት 250 ወታደሮች እና አንድ ጄኔራል ተገድለዋል ካለ በኋላ ነው።















