የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዚዳንት በነፍስ ማጥፋት እና በአገር ክህደት ወንጀል ተከሰሱ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የደቡብ ሱዳን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ሪክ ማቻር በነፍስ ማጥፋት፣ በአገር ክህደት እንዲሁም በሰብዓዊነት ላይ በተፈጸሙ ወንጀሎች ተከሰሱ።
የምክትል ፕሬዚዳንቱ ክስ በአገሪቱ የእርስ በእርስ ጦርነት ይቀሰቅሳል የሚል ፍራቻን ቀስቅሷል።
የአገሪቱ የፍትህ ሚኒስትር ጆሴፍ ጌንግ አኬች ምክትል ፕሬዚዳንቱ ላይ የተመሰረተው ክስ ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ከእርሳቸው ጋር በተያያዘ የተፈጸመ ጥቃት ላይ መነሻ ያደረገ ነው።
በዋና ከተማዋ ጁባ ወደ መኖሪያ ቤታቸው የሚወስድ ዋና መንገድ በታንኮች እና ወታደሮች ተዘግቷል።
ለማቻር ታማኝ የሆኑ ኃይሎች ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርን ከሚደግፉ ታጣቂዎች ጋር ለአምስት ዓመት ያህል የተዋጉ ሲሆን እአአ በ2018 በተደረሰ የሰላም ስምምነት ጦርነቱ አብቅቷል።
ማቻር ከባለፈው ዓመት መጋቢት ወር አንስቶ በቁም እስር ላይ የሚገኙ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የአፍሪካ ኅብረት እንዲሁም የጎረቤት አገራት ሁኔታዎች እንዲረጋጉ ጠይቀዋል።
እአአ በ2018 በተፈረመው የሰላም ስምምነት መሠረት 400,000 ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው የእርስ በእርስ ጦርነት የቆመ ቢሆንም በማቻር እና በኪር መካከል ያለው ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሻከረ መጥቶ በሁለቱ ብሔር መካከል ውጥረት እና አልፎ አልፎ ግጭት እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል።
ከማቻር ጋር ሌሎች ሰባት ሰዎች ክስ የተመሰረተባቸው ሲሆን ከእነዚህም መካከል የነዳጅ ሚኒስትሩ ፑት ካንግ ቾል፣ እና የጦሩ ምክትል ሚኒስትሩ ሌተናል ጄነራል ጋብሬል ዱኦፕ ላ እንደሚገኙበት የፍትህ ሚኒስትሩ ጆሴፍ ጌንግ አኬች በመግለጫቸው ላይ ተናግረዋል።
ሁሉም የማቻር አጋሮች ሲሆኑ በቁጥጥር ስር የዋሉት በተመሳሳይ ወቅት ነው።
ሚኒስትሩ 13 ተጠርጣሪዎች አሁንም ድረስ በቁጥጥር ስር አለመዋላቸውን ተናግረዋል።
በአገሪቱ ሰሜን ምሥራቅ ከተማ፣ ናስር የጦር ካምፕ ያንቀሳቀቅሳሉ የተባለ ሲሆን 250 ወታደሮች እና አንድ ጄነራልን መግደላቸው ተሰምቷል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ንብረት የሆነ ሄሊኮፕተር እንዲሁ በእሳት ተያይዞ ፓይለቱ ሞቷል።
ፍትህ ሚኒስትሩ "ክሱ በደቡብ ሱዳን ሕዝብ ላይ እና በሰብዓዊ እርዳታ ድርጅት ሠራተኞች ላይ ወንጀል ለሚፈጽሙ ሰዎች ግልጽ መልዕክት የሚያስታልልፍ ነው። የትኛውም ሥልጣን ላይ ቢኖሩ ወይም ተጽዕኖ ቢኖራቸው ለሚሰሩት ጥፋት ተጠያቂ መሆናቸው አይቀርም" ብለዋል።
አክለውም ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት መመራቱን ገልጸው የፍርድ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ለፖለቲካ ወይም ለዲፕሎማቲክ ክርክር ክፍት መሆኑን ተናግረዋል።
ማቻር ተፈፀመ ከተባለው ጥቃት ጀርባ አሉበት ስለመባሉ ያሉት ነገር የለም።
ደቡብ ሱዳን ለረዥም ዓመታት ከተደረገ ጦርነት በኋላ እአአ በ2011 ከሱዳን ነጻነቷን አግኝታለች።















