ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጃፓን ዕድሜያቸው ከ100 ዓመት በላይ በሆኑ ሰዎች ብዛት አዲስ ክብረ ወሰን አስመዘገበች
በጃፓን ዕድሜያቸው 100 እና ከዚያ በላይ የሆናቸው ሰዎች ቁጥር በ55 ዓመት ውስጥ ክብረ ወሰን በሆነ ሁኔታ ጨምሮ 100 ሺህ መድረሱን መንግሥት አስታወቀ።
አገሪቷ በ55 ዓመታት ውስጥ አዲስ ክብረ ወሰን በማስመዝገብ ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ የኖሩ ሰዎች ቁጥር እስከ መስከረም ወር ድረስ 99 ሺህ 763 መድረሱን እና ከእነዚህ መካከል የሴቶቹ ቁጥር 88 በመቶውን እንደሚይዝ የጃፓን ጤና ሚኒስቴር ዓርብ ዕለት አስታውቋል።
ጃፓን በዓለማችን ሰዎች ረጅም ዕድሜ የሚኖሩባት አገር ስትሆን፤ በዓለማችን ረጅም ዕድሜ ያላቸው ግለሰብ መኖሪያ በመሆኗም ትታወቃለች።
ከዚህም ባሻገር በርካታ ዕድሜያቸው የገፉ ሰዎች ያሉባት አገር ናት። ዜጎቿ ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓትን የሚከተሉ ቢሆንም የወሊድ ምጣኔያቸው ግን ዝቅተኛ ነው።
በጃፓን በዕድሜ አንጋፋዋ ሴት የ114 የዕድሜ ባለጸጋዋ ሺጌኮ ካጋዋ ናቸው። ነዋሪነታቸው በናራ ከተማ በምትገኘው ያማቶኮሪያም ነው። በዕድሜ አንጋፋው አዛውንት ደግሞ በባሕር ዳርቻዋ ኢዋታ ነዋሪ የሆኑት የ111 ዓመቱ ኪዮታካ ሚዙኖ ናቸው።
የጤና ሚኒስትሩ ታካማሮ ፉኮማ፣ ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ የኖሩትን 87 ሺህ 784 ሴቶች እና 11 ሺህ 979 ወንዶችን እንኳን ደስ ያላችሁ ያሉ ሲሆን፣ ለማኅበረሰቡ ዕድገት ለበርካታ ዓመታት አስተዋፅኦ በማድረጋቸውም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ይህ መረጃ የወጣው የጃፓን የአዛውንቶች ቀን ከሚከበርበት አራት ቀናት ቀደም ብሎ ነው።
የአዛውንቶች ቀን በጃፓን ብሔራዊ ቀን ተደርጎ የሚከበር ሲሆን፣ በዚህ ዕለት አንድ ክፍለ ዘመን የደፈኑ ሰዎች የእንኳን ደስ ያላችሁ ደብዳቤ እና የብር ዋንጫ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ይበረከትላቸዋል። በዚህ ዓመትም 52 ሺህ 310 አረጋውያን የዚህ ሽልማት ተቋዳሽ እንደሚሆኑ የጤና ሚኒስቴር ገልጿል።
እንደ አውሮፓውያኑ 1960ዎቹ የጃፓን ሕዝብ በቡድን ሰባት አገራት ውስጥ ካሉት ጋር ሲነጻጸር ከ100 ዓመት በላይ ዕድሜ ያላቸው ሰዎች ቁጥር አነስተኛ ነበር። ሆኖም ይህ ቁጥር በአስርተ ዓመታት ውስጥ በአስገራሚ ሁኔታ ተለውጧል።
መንግሥት በ1963 ባካሄደው ጥናት ዕድሜያቸው 100 እና ከዚያ በላይ የሆናቸው ሰዎች ቁጥር 153 ብቻ ነበሩ። ነገር ግን ይህ ቁጥር በ1981 ወደ አንድ ሺህ ከፍ ያለ ሲሆን፣ በ1998 10 ሺህ ደርሷል።
በልብ እንዲሁም በካንሰር በተለይም በጡት እና በፕሮስቴት ካንሰር የሚከሰቱ ሞቶች ዝቅተኛ በመሆናቸው ዜጎቿ ረጅም ዕድሜ እንዲኖሩ አስተዋፅኦ እንዳደረገ በዋናነት ይጠቀሳል።
በጃፓን ለእነዚህ በሽታዎች መንስኤ ሊሆን የሚችለው ከልክ በላይ ውፍረት ምጣኔ ዝቅተኛ ሲሆን፣ አመጋገባቸው ለዚህ አስተዋፅኦ አድርጓል። ጃፓኖች ቀይ ሥጋ እምብዛም የማይመገቡ ሲሆን፣ ዓሳ እና አትክልቶች በብዛት ይመገባሉ።
ከልክ በላይ የውፍረት ምጣኔ በሴቶች ዘንድ ዝቅተኛ ሲሆን፣ ይህም የጃፓን ሴቶች ከወንዶቹ በበለጠ ረጅም ዕድሜ ለመኖራቸው ምክንያት ሊሆን ይችላል።
በሌላው ዓለም ስኳር እና ጨው አብዝቶ የመጠቀም ልማድም በጃፓን አይታይም። የሕብረተሰብ ጤና መልዕክቶች በሕዝቡ ዘንድ በመድረሳቸውና ነዋሪዎችም መልዕክቱን በመቀበላቸው የሚወስዱትን የጨው መጠን ቀንሰዋል።
ነገር ግን ረጅም ዕድሜ ለመኖራቸው ምክንያቱ አመጋገባቸው ብቻ አይደለም።
ጃፓናውያን በተለይ ወደ ኋለኛው ዕድሜያቸው ላይ ንቁ የአኗኗር ዘይቤን ይከተላሉ። በአሜሪካ እና በአውሮፓ ከሚኖሩ አረጋውያን በላይ የእግር ጉዞ ያደርጋሉ፤ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎትም ይጠቀማሉ።
ዕለታዊ የቡድን አካላዊ እንቅስቃሴ የሚተላለፍበት ራዲዮ ታኢሶም ከአውሮፓውያኑ 1928 ጀምሮ የጃፓኖች ባህል ሆኗል።
ይህ የተጀመረው የሕብረተሰብ ጤናን ለማበረታታት ነው። የሦስት ደቂቃው ፕሮግራም በቴሌቪዥን የሚተላለፍ ሲሆን፣ በመላ አገሪቷ ነዋሪዎች በቡድን በመሆን በእንቅስቃሴው ይሳተፋሉ።
ሆኖም በርካታ ጥናቶች በዓለም ላይ ባለው የአንድ ክፍለ ዘመን ነዋሪዎች ቁጥር ላይ ጥርጣሬ አላቸው። እነዚህ ጥናቶች ለጥርጣሬያቸው እንደ ምክንያት የሚጠቅሱት የመረጃዎች ስህተት፣ ተጨማጭ ያልሆነ የሕዝብ ምዝገባ እና የልደት የምሥክር ወረቀት አለመኖርን ነው።
በአውሮፓውያኑ 2010 በጃፓን የቤተሰብ መዝገብ ላይ የተደረገ ቆጠራ ከ230 ሺህ በላይ የሚሆኑ 100 ዓመት እና ከዚያ በላይ የሞላቸው ሰዎች የደረሱበት አለመታወቁን ያጋለጠ ሲሆን፣ ከእነዚህ ሰዎች መካከል የተወሰኑት ከአስርተ ዓመታት በፊት በሞት የተለዩ ነበሩ።
ለዚህም ምክንያቱ አንዳንድ ቤተሰቦች የጡረታ አበል ለመጠየቅ ሲሉ የአረጋውያን ዘመዶቻቸውን ሞት በመደበቃቸው ሊሆን እንደሚችል ተነግሯል።
ብሔራዊ ምርመራው የተጀመረው በቶኪዮ በዕድሜ አንጋፋው እንደነበሩ የሚታመነው የ111 ዓመቱ የሶገን ኮቶ ከሞቱ ከ32 ዓመታት በኋላ አስክሬናቸው በቤተሰባቸው ቤት ውስጥ ከተገኘ በኋላ ነበር።