በጃፓን የውልደት መጠን መቀነስና የአዛውንት መብዛት እጅግ አሳሳቢ ነው ተባለ

በጃፓን ታሪክ ለመጀመሪያ ግዜ ከአጠቃላይ የአገሪቱ ሕዝብ 10 በመቶ ያክሉ ዕድሜያቸው 80 እና ከዚያ በላይ ሆነ ተባለ።

የዓለማችን ዝቅተኛው የውልደት መጠን ባላት ጃፓን አዲስ የሚወለዱ ሕጻናት ቁጥር መቀነስ እና የአዛውንቶች ቁጥር መጨመር እጅግ አሳሳቢ ሆኗል።

በዓለማችን ዝቀተኛው የውልደት መጠን ያላት ጃፓን በዕድሜ የገፉ ዜጎቿን መንከባከብ ፈተና ሆኖባታል።

እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከሆነ እሲያዊቷ አገር አነስተኛ የውልደት መጠን ብቻ ሳይሆን ያላት በዓለማች ካሉ አገራት ከአጠቃላይ ሕዝባቸው ከፍተኛ መጠን ያለው አዛውንት መገኛም ጭምር ናት።

ይፋዊ አሃዞች እንደሚያሳዩት ከአጠቃላዩ የጃፓን 125 ሚሊዮን ሕዝብ 29 በመቶ ዕድሜያቸው 65 ዓመት እና ከዚያ በላይ ነው።

ከጃፓን በመቀጠል ጣሊያን አጠቃላይ ዜጎቿ 24.5 በመቶ እንዲሁም የፊንላንድ 23.6 በመቶ ሕዝብ ዕድሜያቸው 65 ወይም ከዚያ በላይ ነው።

ናሽናል ኢንስቲትዩት ኦፍ ፖፒዩሌሽን ኤንደ ሶሻል ሴኪዩሪቲ ሪሰቸር የተባለ ተቋም በ2040 ከጃፓን አጠቃላይ ሕዝብ 34.8 በመቶ የሚሆነው ዕድሜው 65 እና ከዚያ በላይ ይሆናል ሲል ይገምታል።

ጃፓን አዛውንት ዜጎቿን ለመጦር የምታወጣው ወጪ ጣራ ነክቷል። የአገሪቱ መንግሥት እየጨመረ የመጣውን ማኅበራዊ ወጪ ለመሸፈን ሲል በቀጣዩ በጀት ዓመት ሬኮርድ የሆነ በጀት መድቧል።

አገሪቱ በአዛውንት ዜጎቿ ምክንያት የጨመረባትን ማኅበራዊ ወጪ ለመቀነስ ዜጎቿ በዕድሜ ቢገፉም በስራ ላይ እንዲቆዩ ማድረግን እንደ አማራጭ እየተጠቀመች ነው።

በዓለማችን ካሉት ግዙፍ የምጣኔ ሃብት ባለቤት አገራት መካከል ዕድሜያቸው 65 የሆኑ ሰዎችን ሥራ ላይ በማሰማራት ጃፓን ቀዳሚዋ ናት። ከአጠቃላይ ሠራተኛዋ መካከል 13 በመቶ ከ65 ዓመት በላይ ናቸው።

የጃፓን መንግሥት የውልደት መጠንን ከፍ ለማድረግ የሚያደርገው ጥረት እየጨመረ በመጣው የኑሮ ውድነት እና ረዥም የሥራ ሰዓት ምክንያት ይህ ነው የሚባል ውጤት አላስገኘም።

ባለፈው ዓመት በጃፓን የተወለዱት ሕጻናት ቁጥር ከ800ሺህ አይበልጥም። ይህ አሃዝ በ1970ዎቹ ከነበረው ቁጥር ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ ያንሳል።

ጠቅላይ ሚንስትር ፉሚዮ ኪሺዳ በአገራቸው የውልደት መጠን እየቀነሰ በመምጣቱ እንደ ማኅብረሰብ መቀጥል የማንችልበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ከጫፍ ነን ብለዋል።

ከጃፓን በተጨማሪ በቀጠናው የሚገኙ አገራት አነስተኛ የውልደት መጠን እያስመዘገቡ ነው። ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት ቻይና ከ1960ዎቹ በኋላ ለመጀመሪያ ግዜ የሕዝብ ቁጥሯ ቀንሷል።

በተመሳሳይ ደቡብ ኮሪያም አነስተኛ የውልደት መጠን መዝግባለች።