ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አምነስቲ በኢትዮጵያው ጦርነት የተሳተፉት በሙሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ፈጽመዋል አለ
ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የተሳተፉት በሙሉ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ፈጽመዋል አለ።
አምነስቲ ትናንት በኬንያ መዲና ናይሮቢ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የኢትዮጵያ እና ኤርትራ መከላከያ፣ የትግራይ ኃይሎች፣ የአማራ ልዩ ኃይል እና ፋኖ ሚሊሻ ከባድ የመብት ጥሰቶችን ፈጽመዋል ብሏል።
በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የአፍሪካ ቀንድ ተመራማሪ የሆኑት ፍስሃ ተክሌ፤ "ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ ከጦር ወንጀል እና በሰብዓዊነት ላይ ከሚፈጸሙ ወንጀሎች ጋር ሊስተካከሉ የሚችሉ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ተመልክተናል” ብለዋል።
ፍስሃ ተክሌ በዚህ ጦርነት ከተፈጸሙ ወንጀሎች መካከል "አስገድዶ መድፈርን፣ ሌሎች ጭካኔ የተሞሉባቸው ጾታዊ ጥቃቶች” ይገኙበታል ሲሉ አክለዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከዘር ማጥፋት ወንጀል ጋር ተስተካካይ የሆኑ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ተፈጽመዋል የሚሉ ሪፖርቶች ቀደም ብለው ሲወጡ ነበር።
መገኛው አሜሪካ የሆነው ሆሎኮስት መታሰቢያ ሙዚየም በትግራይ ክልል በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች እና የዘር ማጥፋት ወንጀል የመከሰት እድል መጨመር አሳስቦኛል ብሎ ነበር።
ሙዚየሙ የኢትዮጵያ ጦር በኤርትራ እና በአማራ ልዩ ኃይሎች ታግዞ ቁልፍ የሚባሉ የትግራይ ከተሞችን መያዙ ሰላማዊ የትግራይ ነዋሪዎችን ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል ነው ሲል ማክሰኞ ጥቅምት 15/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቆ ነበር።
“የዘር ማጥፋት ወንጀል ማስጠንቀቂያ ምልክቶች የሆኑት የጭፍጨፋዎች ሪፖርቶች፣ ሰላማዊ የትግራይ ነዋሪዎችም ዒላማ ያደረጉ ግድያዎች፣ የጥላቻ ንግግሮች፣ የጅምላ እስር፣ ሆነ ተብሎ ረሃብ በመፈጠር ሰዎችን በጅምላ መቅጣት . . . እየተበራከቱ ነው” ብሏል።
የሙዚየሙን መግለጫ ተከትሎ በአሜሪካ የሚገኙት የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ኤምባሲዎች ሪፖርቱን አጥብቀው ተችተውታል።
የኢትዮጵያ ኤምባሲ የአሜሪካ ሆሎኮስት ሚሞሪያል ሙዚየም ያወጣው መግለጫ “ኃላፊነት የጎደለውና የአሸባሪው ህወሓት ቡድንን ፕሮፖጋንዳ ለማስተጋባት ያለመ” ነው ብሏል።
ኤምባሲው ሙዚየሙ “ያለ ማስረጃ የህወሓትን ድምጽ ከማስተጋባቱ በፊት” መሬት ላይ ያለውን እምነት የሚያሳይ መረጃ ማሰባሰብ ይኖርበታል ብሏል
ኤምባሲው ጨምሮም፤ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መመርመር እንዲያስችል መንግሥት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የጋራ ጥናት እንዲያደርጉ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ቁርጠኝነቱን አሳይቷል ብሏል።
በተመሳሳይ በአሜሪካ የኤርትራ ኤምባሲም የሙዚየሙን ሪፖርት በመቃወም ተመሳሳይ ይዘት ያለው መግለጫ አውጥቷል። "የህወሓት የስም ማጥፋት ፕሮፖጋንዳን ነው የደገመው" ያለው ኤምባሲው፤ ገለልተኛ ያልሆነ ምርመራ ሳያደርግ ያወጣውን ሪፖርት እንዲያነሳ ኤምባሲው ጠይቋል።