ኢራቅ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ወንጀል ነው ስትል አዲስ ሕግ አወጣች

የኢራቅ ፓርላማ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን ከ10 እስከ 15 ዓመት በሚደርስ እስር የሚቀጣ አዲስ ሕግ አረቀቀ።

በአዲሱ ሕግ መሠረት ጾታቸውን የቀየሩ ሰዎች ከአንድ እስከ ሦስት ዓመት ሊታሰሩ ይችላሉ።

ሕጉ በአገሪቱ ሃይማኖታዊ እሴቶችን ለማስጠበቅ እንደሚረዳ ደጋፊዎቹ ተናግረዋል።

የመብት ተሟጋች ቡድኖች በበኩላቸው ኢራቅ በተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያን (ኤልጂቢቲኪው) ሰዎች ላይ ያላት የጥሰት መዝገብ ላይ የሰፈረ ተጨማሪ ጥቁር ነጥብ ነው ብለውታል።

አዲሱ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን የሚያበረታቱ ወይም ሴተኛ አዳሪነትን የሚያራምዱ፣ ጾታ ለመቀየር ቀዶ ህክምና የሚያደርጉ ዶክተሮችን፣ “ሆን ብለው” እንደ ሴት የሚሆኑ ወንዶች እና “በሚስት መለዋወጥ” ላይ የተሠማሩ ሰዎችም የእስር ቅጣት ይጠብቃቸዋል ተብሏል።

ከዚህ ቀደም የወጣው ረቂቅ በ1980ዎቹ መገባደጃ ላይ የወጣው የሴተኛ አዳሪነት ሕግን በማሻሻል በተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት የተሳተፉ በሞት እንዲቀጡ ጠይቆ ነበር።

ይሁን እንጂ ከአሜሪካ እና ከሌሎች ምዕራባውያን አገራት የገጠመውን ተቃውሞ ተከትሎ ተሻሽሏል።

የፓርላማ አባሉ አሚር አል-ማሙሪ ቅዳሜ ዕለት ለሻፋክ ኒውስ እንደተናገሩት አዲሱ ሕግ “ኢስላማዊ እና ማህበረሰባዊ እሴቶችን የሚቃረኑ ልዩ ጉዳዮችን ለመዋጋት ትልቅ እርምጃ ነው” ብለዋል።

ማሻሻያዎቹን ያቀረቡት የሕግ ባለሙያው ራድ አል-ማሊኪ በበኩላቸው ሕጉን የማጽደቁ ሥራ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር መሐመድ ሺአ አል-ሱዳኒ በአሜሪካ ጉብኝት ካደረጉ በኋላ ሆኖ እንዲራዘም ተደርጓል ብለዋል።

"በጉብኝቱ ላይ ተጽዕኖ እንዲፈጥር አልፈለግንም። የውስጥ ጉዳይ ነው እና በኢራቅ ጉዳዮች ላይ ምንም አይነት ጣልቃ ገብነት አንቀበልም" ሲሉ አል-ማሊኪ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያን በኢራቅ ባለሥልጣናት ኢላማ ሲደረጉ ቆይተዋል። እነሱን ለመቅጣት ሲባል ቀደም ሲል ሌሎች የሥነ ምግባር ሕጎች ይተገበሩ ነበር።

ሂዩማን ራይትስ ዎች እና ሌሎች የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችም በርካታ የአፈና፣ የማሰቃየት፣ የአስገድዶ መድፈር እና ግድያዎች መፈጸማቸውን ገልጸዋል።

ዋነኞቹ የኢራቅ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሚሰነዝሯቸውን ትችቶችን አጠናክረው በመቀጠል ቀስተ ደመና ባንዲራዎች በተቃውሞ ሰልፎች አቃጥለዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ሕጉ መፅደቁ ለሰብአዊ መብትና ነፃነት ጠንቅ ነው ብሏል።

“ሕጉ የኢራቅን ኢኮኖሚ የሚያቀዛቅዝ እና የውጭ ኢንቨስትመንትን የመሳብ አቅምን ያዳክማል" ሲል አክሏል።

"እንዲህ ያለው መድልዎ በኢራቅ ውስጥ ያለውን የንግድ እና የኢኮኖሚ ዕድገትን እንደሚጎዳ ዓለም አቀፍ የንግድ ጥምረት ቀደም ሲል አመልክቷል።”

የእንግሊዝ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሎርድ ዴቪድ ካሜሮን በበኩላቸው የሕጉ ማሻሻያዎች “አደገኛ እና አሳሳቢ” ሲሉ ገልጸዋቸዋል።

“ማንም በማንነቱ ምክንያት ዒላማ መሆን የለበትም” ሲሉ ኤክስ ላይ ጽፈዋል።

"የኢራቅ መንግስት የሁሉንም ሰዎች ሰብአዊ መብቶች እና ነጻነቶች ያለምንም ልዩነት እንዲያከብር እናበረታታለን" ብለዋል።