አሜሪካ እና ቻይና ተጨማሪ ታሪፍን ለማስወገድ የንግድ ስምምነት ቀነ ገደባቸውን አራዘሙ

ኮንቴነሮች የጫነች መርከብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አሜሪካ እና ቻይና የታሪፍ ጭማሪው ተግባራዊ መሆን ከመጀመሩ ከሰዓታት በፊት የንግድ ሥምምነታቸውን እስከ ሕዳር10 ድረስ አራዘሙ።

የዓለማችን ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆኑት ሁለቱ አገራት በጋራ ባወጡት መግለጫ በጥር ወር መጀመሪያ ላይ እያንዳንዳቸው በሚያስገቧቸው ምርቶች ላይ የሦስት አሃዝ ታሪፍ ለመጣል ያስተላለፉትን ውሳኔ ለተጨማሪ 90 ቀናት ማራዘማቸውን ገልፀዋል።

ሁለቱ አገራት ባለፈው ወር ያጠናቀቁትን ውይይት "ገንቢ" በማለት ጠርተውታል።

የቻይናው ከፍተኛ ተደራዳሪ በወቅቱ እንደተናገሩት ሁለቱ አገራት ስምምነቱን ለማስቀጠል እንደሚጥሩ የገለፁ ሲሆን፤ የአሜሪካ ባለስልጣናት በበኩላቸው ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የመጨረሻውን ይሁንታ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ተናግረው ነበር።

ሰኞ ዕለት ዶናልድ ትራምፕ የታሪፍ ስምምነቱን ለማራዘም ፕሬዚዳንታዊ ትዕዛዝ ፈርመዋል።

በዚህ ስምምነት መሠረት ዋሽንግተን በቻይና ምርቶች ላይ ለመጣል አቅዳው የነበረው የ145 በመቶ ታሪፍ እንዲሁም በምላሹ ቤጂንግ በአሜሪካ ምርቶች ላይ የ125 በመቶ ታሪፍ ለመጣል የያዘችውን እቅድ ለጊዜው እንዲዘገይ አድርገዋል።

በስምምነቱ መሠረት አሜሪካ ከቻይና በሚገቡ ምርቶች ላይ 30 በመቶ ታሪፍ የጣለች ሲሆን ቻይና ግን በአሜሪካ ምርቶች ላይ የ10 በመቶ ታሪፍ ብቻ ጥላለች።

የተራዘመው ስምምነት በአገራቱ መካከል ያለውን "የንግድ ሚዛን መዛባትን ለመፍታት" እና "ፍትሃዊ ያልሆነ የንግድ ልምዶች" ላይ ለሚደረገው ድርድር ተጨማሪ ጊዜ ይሰጣል ሲል ዋይት ሐውስ ገልጿል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እአአ በ 2024 አሜሪካ ከማንኛውም የንግድ አጋሯ ካላት የበለጠ ከቻይና ጋር ወደ 300 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የንግድ ጉድለት እንዳላት ተጠቅሷል።

መግለጫው የሚያደረጉት ንግግር የአሜሪካን ላኪዎች ወደ ቻይና የሚልኳቸውን ምርቶች ለማሳደግ እና የብሔራዊ ደህንነት እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ለመፍታት ያለመ ነው ብሏል።

በዋሽንግተን የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ ቃል አቀባይ "በቻይና እና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል ሁለቱም አገራት የሚያሸንፉበት ትብብር ትክክለኛው መንገድ ነው፤ መጨቆን እና ማገድ የትም አያደርስም" ብለዋል።

በመግለጫው ላይ ቻይና አሜሪካ ያላትን "ምክንያታዊ ያልሆነ" የንግድ እገዳ እንድታነሳ፣ በሁለቱም በኩል ኩባንያዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እና የዓለም ሰሚኮንዳክተር ምርቶችን መረጋጋትን ለማስጠበቅ በጋራ እንድትሰራ ጠይቃለች።

በአሜሪካ እና በቻይና መካከል ያለው የንግድ ውዝግብ በሚያዚያ ወር ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር።

ትራምፕ ከተለያዩ አገራት ወደ አሜሪካ የሚገቡ ምርቶች ላይ አዳዲስ ታሪፎችን ከጣሉ በኋላ ቻይና ከፍተኛ የተባለው ታሪፍ ተጥሎባታል።

ቤጂንግ በአፀፋው በአሜሪካ ምርቶች ላይ የራሷን ታሪፍ የጣለች ሲሆን፣ ይህም በሁለቱ አገራት መካከል የንግድ ጦርነትን በመቀስቀስ ወደ ሦስት አሃዝ ከፍ ያለ ታሪፍ ለመጣል እንዲዝቱ አድርጓቸዋል።

ሁለቱ ወገኖች በግንቦት ወር የተወሰኑትን እርምጃዎች ወደ ጎን ለመተው ተስማምተው ነበር።

ያ ስምምነት ወደ አሜሪካ የሚገቡት የቻይና ምርቶች ከጥር ወር መጀመሪያ ጋር ሲነፃፀር የ30 በመቶ ተጨማሪ ታሪፍ እንዲጣልባቸው አድርጓል።

ሁለቱ ወገኖች የቻይናን ብርቅዬ ማዕድናት ስለመጠቀም፣ የሩሲያ ነዳጅ ዘይት ግዢን እና የአሜሪካ ቺፖችን ጨምሮ የተራቀቀ ቴክኖሎጂ ሽያጭ ላይ ቻይናን ጨምሮ የተጣለው እገዳን በሚመለከት እየተወያዩ ነው።