በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ህፃናት ደብዛቸው ጠፍቷል

የፎቶው ባለመብት, ICRC
በአፍሪካ 25 ሺህ የሚሆኑ ህፃናት ጠፍተዋል ተብሎ እንደሚገመት የአለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ አስታወቀ።
ኮሚቴው አለም አቀፍ የመጥፋት ቀንን በማስመልከት ባወጣው ሪፖርት ሁኔታው ልብ የሚነካ እንደሆነም ገልጿል።
ይህ አኃዝ በአህጉሪቱ ጠፍተዋል ተብሎ ከሚታመነው ጠቅላላ ቁጥር 40 በመቶውን እንደሚያሳይ ተቋሙ አስታውቋል።
የህጻናት መጥፋት ለብዝበዛ፣ ለጥቃት እንዲሁም ለአዕምሮ ጭንቀት እንደሚዳርጋቸው ስጋቱን ገልጿል።
ኮሚቴው በአፍሪካ ደብዛቸው የጠፉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሲሆን በዚህ አመትም 64 ሺህ ደርሷል ብሏል።
ለበርካታ ሰዎች የመጥፋት መንስኤዎቹም ጦርነት፣ አስከፊ ስደት እና እስራት ናቸው።
በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ከ35 በላይ ግጭቶችና ጦርነቶች አሉ።ይህንንም ተከትሎ ህጻናትን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ድንበር አቋርጠዋል።
በርካቶችም ለደህንነታቸውና ነገን የተሻለ ህይወት በማለም ፈታኝ የሚባሉትን የሰሃራ በረሃና የሜድትራንያን ባህርን ያቋርጣሉ።
በነዚህ አስቸጋሪ ስፍራዎች ላይ የሚደረጉ ጉዞዎች ከፍተኛ አደጋን የጋረጡ ሲሆን ፤ በርካቶችም የት እንዳሉ ሳይታወቅ ደብዛቸው ጠፍቷል።
ተቋሙ በአፍሪካ ያለ ወላጅ፣ አሳዳጊ የመጡ ከ5ሺህ በላይ ህፃናትን መዝግቧል። ሆኖም ባለፈው ዓመት ከ1ሺህ 200 በላይ ቤተሰቦችን መልሶ ማገናኘት አስችሏል።
የአፍሪካውያን መጥፋትን ለመከላከል እና የጠፉ ሰዎችን እጣ ፈንታ በተመለከተ በተሻለ ሁኔታ መረጃን ለቤተሰቦቻቸው ለማቅረብ እና የበለጠ ወጥ እና ውጤታማ አካሄድን ለማስተዋወቅ ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ከአፍሪካ ህብረት ጋር በመተባበር በጠፉ ስደተኞች ላይ ያተኮረ የፖሊሲ ስብሰባ ነሐሴ 24፣ 2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ አካሂዷል።
ዓለም አቀፍ የመጥፋት ቀን በዓለም ዙሪያ የሚከበረው የጠፉ ሰዎችን እንዲሁም ቤተሰቦቻቸው በማያውቁበት ሁኔታ በአስከፊ ሁኔታ በእስር ላይ ያሉ ሰዎችን በመዘከርና ግንዛቤ በመፍጠር ነው።












