ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የ"ኢትዮጵያ ኢንሳይደር" መሥራቹ ተስፋለም ወልደየስ ለዓመቱ "የፕሬስ ነጻነት ጀግና" ሽልማት ተመረጠ
የ'ኢትዮጵያ ኢንሳይደር' የበይነ መረብ ሚዲያ መሥራች እና አርታዒ ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ የዘንድሮው "የፕሬስ ነፃነት ጀግና" ተሸላሚዎች ዝርዝር ውስጥ ተካተተ።
ዓለም አቀፉ የፕሬስ ኢኒስቲትዩት በየዓመቱ በሚያዘጋጀው በዚህ ሽልማት የዚህ ዓመት አሸናፊ ከሆኑት ሰባት ጋዜጠኞች መካከል ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ አንዱ ሆኖ ተመርጧል።
ይህንን ሽልማት የዓለም አቀፉ የፕሬስ ኢንስቲትዩት (IPI) እና ዓለም አቀፍ ሚዲያ ሰፖርት (IMS) የተባሉ ሁለት ተቋማት በትብብር የሚሰጡት ነው።
ዓለም አቀፍ ሽልማቱ ለመገናኛ ብዙኃን ነጻነት ያልተገደበ የዜና እና የመረጃ ፍሰት ሲሉ የግል ደህንነታቸውን ከፍተኛ ስጋት በመጣል ጉልህ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ጋዜጠኞች የሚሰጥ ነው።
ከተስፋለም ጋር ለዚህ የዓለም ፕሬስ ነጻነት ጀግና ሽልማት ሰባት የተለያዩ አገራት ጋዜጠኞች እና አርታዒያን ተመርጠዋል።
ጋዜጠኛ ተስፋለም ለሽልማቱ የተመረጠው "ለገለልተኛ ጋዜጠኝነት ባለው የማያወላውል ቁርጠኝነት" እንደሆነ ሸላሚዎቹ ባወጡት ይፋዊ መግለጫ ላይ አስታውቀዋል።
ተስፋለም "ለዚህ ታላቅ ሽልማት በመመረጤ ታላቅ ክብር ይሰማኛል" በማለት ደስታውን መግለፁ ' በድረ ገፁ ላይ ሰፍሯል።
እንዲሁም ሁለቱ ተቋማት እና ዓለም አቀፍ መራጭ ኮሚቴ "ለጥረቱ እውቅና በመስጠታቸው" ምስጋናውን አቅርቧል።
የኢትዮጵያ ኢንሳይደር በይነ መረብ ሚዲያ መስራቾች ከሆኑት መካከል አንዱ የሆነው ተስፋለም ወልደየስ "ከባለስልጣናት ለሚሰነዘር ቀጥተኛ የበቀል እርምጃ" ዒላማ ከመሆኑ ባሻገር በሥራው ምክንያት "የግል ሕይወቱን በተደጋጋሚ ለአደጋ እንዳጋለጠ" ሸላሚዎቹ በመግለጫቸው ጠቁመዋል።
ጋዜጠኛ ተስፋለም በ2006 ዓ.ም. "ሽብርተኝነትን በመደገፍ" በሚል ከተከሰሱ ሦስት ጋዜጠኞች እና "ዞን 9" በመባል ከሚታወቁት ስድስት ጦማሪዎች ጋር የፍርድ ሂደቱን ሲከታተል ቆይቷል።
ጋዜጠኛው አንድ ዓመት ከሦስት ወራት በወህኒ ቤት ከቆየ በኋላ ክሱ ተቋርጦ ተለቅቋል።
ከተፈታ በኋላ በጀርመን ሀገር በስደት ኖሯል። በመቀጠልም በዶቼ ቬሌ አማርኛ ክፍል ከሰራ በኋላ እአአ 2020 ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ 'ኢትዮጵያ ኢንሳይደር' የበይነ መረብ ሚዲያን ከሙያ ባልደረባው ጋር መስርቷል።
ዋና አዘጋጁ ተስፋለም ወልደየስ በመስከረም 2014 ዓ.ም. ለሦስት ቀናት እንዲሁም በነሐሴ 2017 ዓ.ም. ደግሞ ለአምስት ቀናት በእስር አሳልፏል።
"ይህ ክብር ለእኔ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ እና በስደት ላይ ለሚገኙ ብርቱ ጋዜጠኞች ጭምር ነው" ያለው ጋዜጠኛ ተስፋለም፤ ሽልማቱ "በየዕለቱ በዘፈቀደ በቁጥጥር ስር ለሚውሉ፣ ለሚታሰሩ፣ ማስፈራራት፣ ወከባ፣ ዛቻ ለሚገጥማቸው፣ ለሚከሰሱ እና ጥቃት ለሚፈጸምባቸው የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ድፍረት እና ለሙያቸው ያላቸው ታማኝነት ምስክር" እንደሚሆን መግለፁ በድረ ገፁ ላይ ሰፍሯል።
የኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች "የማይናወጥ ቁርጠኝነት እና ጥንካሬ" በሁለቱ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሽልማት ቦታ ማግኘቱን የገለጸው ተስፋለም፤ "ለሚያከናውኑት ጠቃሚ ሥራ እና ለሚፈታተኗቸው ተግዳሮቶች የበለጠ ትኩረት እንዲሰጥ ያደርጋል" የሚል ተስፋ እንዳለውም ገልጿል።
ለሽልማቱ መመረጡ የጋዜጠኝነት ስራውን ወደ ከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ እንዳነሳሳውም ተስፋለም ተናግሯል።
ተስፋለም ይህንን ሽልማት ሲቀበል ሁለተኛው ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ ነው።
በዓለም አቀፉ የፕሬስ ኢንስቲትዩት የፕሬስ ነጻነት ጀግና ሆኖ የተመረጠው የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ነበር።
ለዘንድሮው ሽልማት ከተመረጡ ጋዜጠኞች መካከል ሁለቱ በሥራቸው ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን ሁለቱ ደግሞ አሁንም በእስር ላይ የሚገኙ ናቸው።
በጋዛ የተገደለችው ፍልስጤማዊ የፎቶ ጋዜጠኛ ማርያም አቡ ዳጋ እና በሩሲያ እስር ቤት ሕይወቷን ያጣችው ዩክሬናዊት ጋዜጠኛ ቪክቶሪያ ራሺና፤ በሕይወት በሌሉበት ሽልማቱ የሚበረክትላቸው ይሆናል።
ጆርጂያዊቷ ዚያ አማግሎቤሊ እና በሆንግ ኮንግ የጋዜጣ አሳታሚው ጂሚ ላይ በእስር ቤት የሚገኙ የሽልማቱ አሸናፊዎች ናቸው።
የቀድሞው የዋሽንግተን ፖስት እና የቦስተን ግሎብ ጋዜጦች ማርቲን ባሮን እና ፔሩቪያዊው ጉስታቮ ጎሪቲም የዘንድሮው ሽልማት ተመራጮች ናቸው።
የዘንድሮው ተመራጮች ሽልማታቸውን የሚቀበሉት እነዚህ ጋዜጠኞች፣ አርታዒያን እና የመገናኛ ብዙኃን ሥራ አስፈጻሚዎች ዓለም አቀፍ ጥምረት የሆነው ዓለም አቀፉ የፕሬስ ኢንስቲትዩት (IPI) 75ኛ ዓመቱን በሚያከብርበት ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ነው።
ጉባኤው ከጥቅምት 13 እስከ 15/2018 ዓ.ም. በኦስትሪያ ዋና ከተማ ቪዬና ይካሔዳል።