ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የወላይታ ሕዝብ የዘመን መለወጫ 'ጊፋታ' በዩኔስኮ የዓለም የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ ተመዘገበ
የወላይታ ሕዝብ የዘመን መለወጫ በዓል የሆነው ጊፋታ በዓለም የማይዳሰሱ ቅርሶች መዝገብ መካተቱን ዩኔስኮ አስታወቀ።
የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ዘንድሮ በማይዳሰሱ ቅርሶች መዝገብ ካካተታቸው የዓለም ቅርሶች መካከል አንዱ ጊፋታ መሆኑን በድረ ገጹ ባወጣው መረጃ አስታውቋል።
ይህንንም ተከትሎ በወላይታ እና አካባቢው የሚገኙ የብሔሩ ተወላጆች ወደ አደባባይ በመውጣት ደስታቸውን መግለጻቸውን የወላይታ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ሳሙኤል ተሰማ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
'ዮዮ ጊፋታ' ከመስከረም 8 እስከ 14 መካከል በሚውለው እሁድ ቀን የሚከበር የዘመን መለወጫ አውደ ዓመት መሆኑን አስተዳዳሪው ጨምረው አስረድተዋል።
20ኛው የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ተቋም በሕንድ፣ ኒው ደልሒ የማይዳሰሱ ቅርሶች ጥበቃ ኮሚቴ ጉባዔ እያካሄደ ሲሆን፤ ከተለያዩ አገራት የማይዳሰሱ ቅርሶችን መዝግቧል።
የቱሪዝም ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሳ፤ ዩኔስኮ ጊፋታን በመዝገቡ በማካተቱ ምስጋና አቅርበው "በወሊያ ቆዶ ዘመን መቁጠሪያ የሚከበር፣ ተወዳጅ ከሆኑ የወላይታ ሕዝብ ባህሎች አንዱ ነው" ማለታቸውን ፋና ዘግቧል።
"የጨረቃ፣ የፀሐይ እና የምድር እሽክርክሪት በአንድ ላይ ሲሆኑ" የሚከበረው ጊፋታ የአዲስ ዘመን ብስራት መሆኑን ጠቅሰዋል።
መጀመሪያ ወይም መነሻ የሚል ትርጓሜ ያለው ጊፋታ፤ ከቀደመው ወደ አዲሱ ዓመት ተስፋን ሰንቆ የመሸጋገር ተምሳሌት ነው።
"ጊፋታ በፆታ፣ በዕድሜ፣ በማኅበራዊ መደብ እና በሃይማኖት ሳይገደብ ሰዎችን ያሰባስባል" ሲሉ የቱሪዝም ሚኒስትሯ ገልጸውታል።
የወላይታ ዞን አስተዳዳሪ እንዲሁም የወላይታ ሶዶ ከተማ ከንቲባን ጨምሮ የተለያዩ የዞኑ አስተዳዳሪዎች ዛሬ ማለዳ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ከመስከረም አጋማሽ እስከ ጥቅምት መባቻ የሚከበረው ጊፋታ፤ የጨረቃ ዑደትን ተከትሎ የሚከናወን ሥነ ሥርዓት መሆኑ ይነገራል።
ባህላዊ ክንውኑ ከመካሄዱ በፊት ቤት እና አካባቢን ማጽዳት የተለመደ ሲሆን፤ በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ የወላይታ ተወላጆችም በዓሉን ለማክበር ወደ ቤተሰቦቻቸው መኖሪያ ይመለሳሉ።
ለዘመን መለወጫ የተጣሉ ይታረቃሉ። በዓሉ በሚከበርበት ዋነኛ ቀን ወዳጅ ዘመድ ተሰባስቦ ጥሬ ሥጋ መመገብ የተለመደ ነው።
ከበዓሉ በፊት ዛፍ ይተከላል። የተጣሉ ታርቀው እና ወዳጅነታቸውን አድሰውም ወደ አዲስ ዓመት ይሻገራሉ።
በዓሉ ላይ አረጋውያን ምርቃት ያቀርባሉ። ምሽት ላይ በእሳት ዙርያ ተሰባስቦ መዝፈን እና መደነስም የሥነ ሥርዓቱ አካል ነው።
10 ቀናት የሚቆየው ጊፋታ የሚጠናቀቀው በፈረስ ግልቢያ፣ በሙዚቃ እና በአረጋውያን ምርቃት መሆኑን ዩኔስኮ በድረ ገጹ አስፍሯል።
የቱሪዝም ሚኒስትሯ ሰላማዊት፤ በዩኔስኮ በቅርስ መዝገብ ውስጥ መካተት ለወላይታ ሕዝብ እና ለኢትዮጵያ በአጠቃላይም "ትርጉም እንደሚሰጥ" ገልጸዋል።
"ባህሉን ለመጠበቅ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያጠናክር ነው" ሲሉም አክለዋል።
ኢትዮጵያ በዩኔስኮ ካስመዘገበቻቸው የሚዳሰሱ ቅርሶች መካከል የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ የፋሲል ግቢ እና የጎንደር ሐውልቶች፣ የአክሱም ሐውልት፣ የታችኛው አዋሽ ሸለቆ፣ የጥያ ትክል ድንጋዮች፣ የታችኛው ኦሞ ሸለቆ፣ የሐረር ጀጎል ጥንታዊ ከተማ፣ የጌዴኦ ባሕላዊ መልክዓ ምድር፣ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ እና የኮንሶ መልክዓ ምድር ይጠቀሳሉ።
በማይዳሰሱ ቅርሶች ዝርዝር ከተካተቱት ውስጥ ደግሞ የመስቀል በዓል፣ ፍቼ ጫምባላላ፣ የገዳ ሥርዓት እና የጥምቀት በዓል ይገኙበታል።
ዩኔስኮ ከጊፋታ በተጨማሪ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ባህላዊ እና ታሪካዊ ክንውኖችን መዝግቧል።
የኬንያ መንፈሳዊ ዳንስ (ሙዋዚንዲካ)፣ የፓናማ ባህላዊ የቤት ግንባታ፣ የኡዝቤኪስታን ባህላዊ ሙዚቃ መሣሪያ ኮባይዝ አሠራር እና አጨዋወት፣ የየመን ባህላዊ የማኅበረሰብ ስብስብ (ሀደርሚ)፣ የቺሊ የቤተሰብ ሰርከስ፣ የቆጵሮስ ወይን (ኮማንዳሪያ)፣ የግብፅ ባህላዊ ምግብ (ኮሻሪ) እንዲሁም የአልባኒያ ሙዚቃ (ለሀታንም) አጨዋወት ይገኙበታል።
በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ መዝገብ ውስጥ የሚካተቱ የማይዳሰሱ እና የሚዳሰሱ ቅርሶች ዓለም አቀፍ ዕውቅና ከማግኘታቸው በተጨማሪ እንዳይጠፉ ጥበቃ ይደረግላቸዋል።
የቱሪዝም ፍሰት እንዲጨምር፣ ቅርሶቹ እንዲጠኑ እና በዓለም እንዲተዋወቁም በር ይከፍታል።
አገራት በዓለም አቀፍ መዝገብ እንዲሰፍር የሚፈልጉትን ቅርስ ለዩኔስኮ ካቀረቡ በኋላ የተቋሙን መስፈርቶች ማሟላታቸው የታመነባቸው ይመዘገባሉ።
ተቋሙ ካስቀመጣቸው መስፈርቶች መካከል የቅርሶቹ ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ውክልና ይጠቀሳል።
የቅርስ ማኅበረሰባዊ ውክልናን ጨምሮ ዩኔስኮ ካስቀመጣቸው 10 መስፈርቶች ቢያንስ ስድስቱን ማሟላት ይጠበቅባቸዋል።