ከሶማሊያ ጋር የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷ ተቋርጦ የነበረው ኢትዮጵያ አዲስ አምባሳደር ሾመች

በሶማሊያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው የተሾሙት ሱሌይማን ደደፎ እና የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼኽ ማህመድ

የፎቶው ባለመብት, MFAEthiopia

የምስሉ መግለጫ, በሶማሊያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው የተሾሙት ሱሌይማን ደደፎ እና የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼኽ ማህመድ

ራሷን በነጻ አገርነት ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር በተደረሰ የባሕር ጠረፍ መግባቢያ ስምምነት ጋር በተያያዘ ከሶማሊያ ጋር የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷ ተቋርጦ የነበረው ኢትዮጵያ አዲስ አምባሳደር ሾመች።

አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ የሶማሊያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው መሾማቸውን እንዲሁም የሹመት ደብዳቤያቸውን ማክሰኞ ሐምሌ 29/2017 ዓ.ም. ለአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼኽ ማህሙድ ማቅረባቸውን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስታውቋል።

አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ የተሾሙት በሞቃዲሾ ተቀማጭነታቸውን አድርገው የነበሩት የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙክታር ሞሐመድ ዋሬ በ72 ሰዓታት ውስጥ አገሪቷን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ከተላለፈ ከዓመት በላይ በኋላ ነው።

ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በማቋረጥ ከአምባሳደሩ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ውሳኔ ያሳለፈችው ሶማሊያ በወቅቱ አዲስ አበባ ያሉትን አምባሳደሯን ጠርታ ነበር።

ኢትዮጵያ አዲስ አምባሳደር መሾሟን ተከትሎ ሶማሊያ አዲስ አምባሳደር ስለመሾሟ ወይም የቀድሞውን ስለመመለሷ የተገለጸ ነገር የለም።

ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼኽ ማህሙድ የኢትዮጵያን አምባሳደር የሹመት ደብዳቤን በተቀበሉበት ወቅት "የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት ለሶማሊያ መረጋጋት እና አገረ መንግሥት ግንባታ ለሰጡት ድጋፍ ምስጋናቸውን" ማቅረባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

በተጨማሪም "ሁለቱ እህትማማች አገራት በርካታ የጋራ እሴት ያላቸው መሆኑ፣ ሰላማቸው እና ልማታቸው በእጅጉ የተያያዘ መሆኑን" ፕሬዝዳንቱ መናገራቸውንም በመግለጫው ላይ ሰፍሯል።

ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ አምባሳደርን ለማባረር መወሰኑን አስመልክቶ የሶማሊያ መንግሥት የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ "በቅርቡ የተከሰቱ ሁኔታዎችን መሠረት በማድረግ እና የአገሪቱን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነትን መሠረት አድርጎ" በርካታ ዲፕሎማሲያው እርምጃዎችን መውሰዱን ገልጾ ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ጨምሮም ውሳኔው ኢትዮጵያ "በሶማሊያ ሉዓላዊነት እና የውስጥ ጉዳይ" ጣልቃ በመግባት ለወሰደቻቸው እርምጃዎች ምላሽ መሆኑን ገልጾ፣ እነዚህም ተግባራዊ የሚሆኑት "የሶማሊያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነትን ለማስጠበቅ" መሆኑን አመልክቶ ነበር።

በተጨማሪም ነጻ አገርነቷን ባወጀችው ሶማሊላንድ እና በከፊል ራስ ገዟ ፑንትላንድ ውስጥ የሚገኙት የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች በሰባት ቀናት ውስጥ እንዲዘጉ መወሰኑን በወቅቱ ተገልጾ ነበር።

ኢትዮጵያ ራሷን እንደ ነጻ አገር ካወጀችው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ካላገኘችው ሶማሊላንድ ጋር 20 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባሕር ጠረፍ ለማግኘት የፈረመችው የመግባቢያ ሰነድ ሶማሊያን በእጅጉ አስቆጥቶ በቀጠናው ከፍተኛ ውጥረትን ያስከተለ መሆኑ ይታወሳል።

ኢትዮጵያ በዚህ ስፍራ የባሕር ኃይል ሰፈር እንደምታቋቁም እና በምትኩ ለሶማሊላንድ ዕውቅና ትሰጣለች መባሉን ተከትሎም እንደ ግዛቷ አካል የምታያት ሶማሊያ ጉዳዩን ወደ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች እስከ መውሰድ አድርሷታል።

ለአንድ ዓመት ያህል በቃላት ጦርነት ሲወዛገቡ የነበሩት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የገቡበትን ውጥረት ለማርገብ በቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲብ ጣይብ ኤርዶዋን አደራዳሪነት ታኅሣሥ 2/2017 ዓ.ም. የአንካራ ስምምነት ተደርሷል።

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መህሙድ በአንካራ በተገናኙበት ወቅት የሶማሊያን የግዛት አንድነት የሚያረጋግጥ እንዲሁም ኢትዮጵያ የባሕር በር መዳረሻ የምታገኝበትን ስምምነት መድረስ የሚያስችል የቴክኒካል ድርድሮች እንደሚጀምሩ ተነጋግረው ነበር።

ልዩነታቸውን በድርድር ጠረጴዛ ለመፍታት ውሳኔ ላይ የደረሱት አገራቱ የመጀመሪያ ዙር የቴክኒክ ድርድር የካቲት 11/2017 ዓ.ም. በቱርክ መዲና አንካራ አድርገው ነበር።

ቀጣዩ የቴክኒክ ድርድርም ለመጋቢት 2017 ዓ.ም. ቀጠሮ ተይዞ የነበረ ቢሆንም አንዳንድ መገናኛ ብዙኃን ግን መሰረዙን ቢዘግቡም በይፋ የተባለ ነበር የለም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ማህሙድ ፊርማቸውን ባኖሩበት የአንካራ ስምምነት መሠረት፤ "ሶማሊያ በአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮ ስር ሆነው በአገሯ የተሰማሩትን የኢትዮጵያ ወታደሮች መስዋዕትነት ዕውቅና ትሰጣለች።"

ከዚህ በተጨማሪ ስምምነቱ "የሶማሊያን የግዛት አንድነት ባከበረ ሁኔታ ኢትዮጵያ አስተማማኝ የባሕር መተላላፊያ ማግኘቷ የሚኖረውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታን ሁለቱ አገራት ዕውቅና ይሰጣሉ" ሲል ያትታል።

መሪዎቹ ባለፈው አንድ ዓመት ተቀዛቅዞ የነበረውን "ግንኙነታቸውን ለማደስ በሁለቱ አገራት መዲናዎች በሚገኙ ዲፕሎማሲያዊ ተወካዮች በኩል ለማጠናከር እንደተስማሙ" በጋራ ባወጡት መግለጫ አትተዋል።

በሶማሊያ እና ኢትዮጵያ መካከል ያለው ውዝግብ በአንካራ ስምምነት መፈታቱን ተከትሎ ሶማሊያ የኢትዮጵያ ወታደሮችን በአዲሱ የአፍሪካ ኅብረት የድጋፍ እና የማረጋጋት ተልዕኮ (ኤዩሶም) ውስጥ ላለማካተት አሳልፋው የነበረውን ውሳኔ ቀልብሳለች።

ኢትዮጵያ ለኤዩሶም ተልዕኮ 2,500 ወታደሮችን ስታዋጣ፣ ኡጋንዳ 4, 500፣ 1,520 ጂቡቲ እንዲሁም ግብፅ 1 ,091 ወታደሮቻቸው በዚህ ተልዕኮ ውስጥ ተሰማርተዋል።

ኢትዮጵያ ሶማሊያ የግዛቴ አካል ናት ከምትላት እና እራሷን ነጻ አገር ነኝ ብላ ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የገባችውን የባሕር በር የመግባቢያ ስምምነት ካልሰረዘች ጦሯ በሰላም አስከባሪው ተልዕኮ ውስጥ እንደማይካተት የሶማሊያ ባለሥልጣናት ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል።

ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የገባችውን የባሕር በር መግባቢያ ስምምነትን በተመለከተ እስካሁን ያለችው ነገር የለም።

በምርጫ አሸንፎ ሥልጣን የያዘው ነጻነቷን ያወጀችው የሶማሊላንድ መንግሥት በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና በሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ መካከል ቱርክ ውስጥ የተደረሰውን ስምምነት በሚመለከት ሶማሊላንድ ሌላ አገር በመሆኗ ይህ ጉዳይ የሚመለከታት እንዳልሆነ ከዚህ ቀደም ማስታወቁ ይታወሳል።