የጣልያን ምክር ቤት ሴቶችን መግደል በዕድሜ ልክ የሚያስቀጣ ወንጀል እንዲሆን ወሰነ

ሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት ተቃውሞ

የፎቶው ባለመብት, Corbis via Getty Images

የጣልያን ምክር ቤት ሴቶች ላይ ያነጣጠረ ግድያ በዕድሜ ልክ እስራት የሚያስቀጣ ወንጀል እንዲሆን በሙሉ ድምጽ ወሰነ።

ለምክር ቤቱ የቀረበው ረቂቅ ሕግ በሙሉ ድምጽ የጸደቀ ሲሆን፤ ፆታዊ ጥቃትን ለማስቆም የሚደረገው ትግል አካል ነው ተብሏል።

እአአ በ2023 ጂሊያ ሴሲቲን የተባለች የ22 ዓመት ሴት በቀድሞ ፍቅረኛዋ መገደሏ መላው ጣልያንን ያስደነገጠ ሲሆን፤ ግድያው ከመፈጸሙ በፊት ምክር ቤቱ ሴቶች ላይ ያነጣጠረ ግድያን (femicide) በተመለከተ ሕግ ለማውጣት ውይይት ጀምሮ ነበር።

የጂሊያ የቀድሞ ፍቅረኛ ፊሊፖ ቱርታ አስክሬኗን በሻንጣ አድርጎ ወንዝ ዳር ጥሎታል።

በቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ የጁሊያ እህት ኤሌና "ገዳዩ አውሬ አይደለም። የአባታዊ ሥርዓት ውጤት የሆነ ጤናማ ሰው ነው" ብላለች።

ግድያው በተፈጸመ በሁለት ዓመት ውስጥ ምክር ቤቱ ሕጉን አጽድቋል።

ጣልያን ሴቶች ላይ ያነጣጠረ ግድያን ወንጀል በማድረግ ከጥቂት አገራት አንዷ ሆናለች።

ረቂቁ የቀረበው በጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ሲሆን ቀኝ ዘመም ፓርቲያቸው እንዲሁም ተቃዋሚዎችም ድጋፍ ሰጥተውታል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የፆታዊ ጥቃት ሰለባ የሆኑ ሴቶችን ለመዘከር የሕዝብ እንደራሴዎች ቀይ ሪቫን እና ጃኬት ለብሰው በምክር ቤት ተገኝተዋል።

ከዚህ በኋላ ሴቶች በፆታቸው ምክንያት የሚፈጸምባቸው ግድያ ፌሚሳይድ የሚባል ይሆናል።

ሕጉን ካረቀቁት አንዷ የሆኑት ዳኛ ፓውላ ዲ ኒኮላ "ሴቶች ላይ ያነጣጠረ ግድያ በየአውዱ ይታያል" ብለዋል።

የ221 ሴቶች ግድያ እንደማሳያ ተወስዶ ነው ሕጉ የወጣው።

"ግድያው የተፈጸመው በቅናት ወይም በፍቅር ምክንያት ነው ማለት ነገሩን አዛብቶ መመልከት ነው። የአጥቂዎች ባህሪ ከበላይነት ስሜት የመነጨ መሆኑን በሕግ ውስጥ በማካተት ከአውሮፓ ቀዳሚ አገር ነን" ብለዋል ዳኛዋ።

ከአውሮፓ ኅብረት አገራት መካከል ሴቶች ላይ ያነጣጠረ ግድያን ወንጀል ያደረጉት ሳይፕረስ፣ ማልታ እና ክሮሺያ ናቸው።

ሴቶች ላይ ያነጣጠረ ግድያ ዓለም አቀፍ ስምምነት ያለው ትርጓሜ ስለሌለው ትክክለኛ አሐዝ ለማግኘት ያስቸግራል።

የጣልያን ሕግ "ጥላቻ፣ መድልዎ፣ ቁጥጥር፣ የበላይነት ማሳየት እና የፍቅር ግንኙነት ከተቋረጠ በኋላ ክትትልን" በወንጀልነት አካቷል።

አምና በጣልያን የተገደሉ ሴቶች ቁጥር ካለፉት ዓመታት በተወሰነ መጠን ያነሰ ሲሆን፤ ከ116 ግድያዎች መካከል 106 ያህሉ ፆታን ያማከሉ ናቸው።

የጂሊያ አባት ጂኖ ሴሲቲን ይሄ ሕግ ልጁን ከሞት ያድናል ብሎ ባያምንም ችግሩን ለመቅረፍ እንድ እርምጃ ነው ይላል።

"ቀኝ ዘመም ወይም ግራ ዘመም ፖለቲከኞችም ፌሚሳይድ የሚለውን ቃል መስማት አይፈልጉም ነበር። አሁን ግን መወያያ አጀንዳ መሆኑ ተስፋ ይሰጣል" ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።

ልጁ ከተገደለች በኋላ በስሟ መታሰቢያ ድርጅት በማቋቋም ስለ ፆታዊ ጥቃት ትምህርት ይሰጣል።

"ፊሊፖ ለምን ልጄን እንደገደላት ማወቅ እፈልጋለሁ። ተማሪ፣ ቤተሰቡ የሚወደው ልጅ እና ጤናማ ሰው ነበር።"

የወንዶች የበላይነት በሚስተዋልበት እንዲሁም ወንዶች ስሜታቸውን መቆጣጠር በማይችሉበት ማኅበረሰብ ውስጥ ፆታዊ ጥቃቶች እንደሚባባሱ ይናገራል።

ልጁ ከቀድሞ ፍቅረኛዋ ጋር መቀጠል ስላልፈለገች ነበር በስለት ወግቶ የገደላት። አባቷ በየትምህርት ቤቱ እና ዩኒቨርስቲው እየዞረ ትምህርት ይሰጣል።

"ሕይወታቸውን የሚመሩት መንገድ ካሳየናቸው እንደ ፊሊፖ አይሆኑም። ወንዳ ወንድ መሆን አለብን ብለው በዘልማዳዊ ዕሳቤ አይመሩም" ይላል።

የጣልያኑ ሕግ ሴቶች ላይ ያነጣጠረ ግድያን የሚተረጉመው ሰፊ በሆነ መንገድ መሆኑን በመግለጽ የተቹ ባለሙያዎችም አሉ።

ፕ/ር ቫለርያ ቶሬ እንደሚሉት፤ በጣልያን አብዛኞቹ ሴቶች የሚገደሉት በቀድሞ ወይም አሁናዊ ፍቅረኛቸው ስለሆነ ፆታን እንደ ምክንያት ማስቀመጥ ከባድ ነው።

"መንግሥት ችግሩን ለመቅረፍ እየሠራሁ ነው ለማለት ያወጣው ሕግ ነው። እኩልነት ማጣትን ለመቅረፍ በዋናነት የሚያስፈልገው የምጣኔ ሃብት ማሻሻያ ነው" ብለው ተከራክረዋል።

ሕጉን የሚደግፉም ሆነ የሚነቅፉ ተንታኞች፤ ሴቶች ላይ ያነጣጠረ ግድያ ከፆታዊ እኩልነት ማጣት የሚመነጭ ስለሆነ የተለያዩ እርምጃዎች መወሰድ እንዳለባቸው ይስማማሉ።

ጣልያን በዓለም አቀፍ የፆታ ክፍተት 85ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።