በሁቲ አማጺያን ጥቃት ከተፈጸመባቸው መካከል የመጀመሪያዋ መርከብ ሰመጠች

የፎቶው ባለመብት, EPA-EEE/REX/SHUTTERSTOCK
የየመን ሁቲዎች አማጺያን በቀይ ባሕር በኩል በሚያቋርጡ መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸም ከመጀመሩ ከወራት በኋላ የመጀመሪያዋ ግዙፍ መርከብ ሰመጠች።
በብሪታኒያ የተመዘገበችው የጭነት መርከብ ማዳበሪያ ጭና በቀይ ባሕር በኩል ለማቋረጥ ስትሞክር ነበር ከሁለት ሳምንት በፊት በኤደን ባሕረ ሰላጤ ላይ በሁቲ ታጣቂዎች ሚሳኤል ተመትታ የቆመችው።
የየመን መንግሥት ባለሥልጣናት እንዳስታወቁት ሪቢይማር የተባለችው መርከብ ጥቃት ከተፈጸመባት በኋላ ውሃ ወደ ውስጧ እየገባ ለቀናት በባሕሩ ላይ ስትዋልል ቆይታ ሰምጣለች።
በኢራን የሚደገፉት ሁቲ አማጺያን ካለፈው ኅዳር አንስቶ በቀይ ባሕር የሚያቋርጡ መርከቦችን ዒላማ ማድረግ ከጀመሩ ወዲህ ይህች መርከብ ጥቃት ከተፈጸመባቸው መካከል በመስመጥ የመጀመሪያዋ ሆናለች።
የሰመጠችው መርከብ ማዳበሪያ ጭና እየተጓዘች ሳለ ነው በሁቲዎች ሚሳኤል የተመታችው። የመርከቧ መስመጥ በቀይ ባሕር ላይ “የተፈጥሮ አካባቢ ጉዳትን” የሚደቅን ነው ሲሉ ባለሙያዎች ተናግረዋል።
ሩቢይማር የተባለችው ይህች መርከብ በኤደን ባሕረ ሰላጤ በኩል ባብ ኤል መንደብ አቅራቢያ ሳለች ነው በየመን ሁቲ አማጺያን በተተኮሱ ሁለት ሚሳኤሎች የተመታችው።
ከአስር ቀናት በፊት የብሪታኒያ መንግሥት መርከቧ ላይ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ ወደ ውስጧ ውሃ እየሰረገ መሆኑን እና 24 የመርከቧ ሠራተኞችን ማትረፍ መቻሉን ገልጾ ነበር።
ከአንድ ሳምንት በፊት ቢቢሲ ያገኘው ምሥል ላይ የተወሰነ የመርከቧ ክፍል በውሃ ተውጦ ቀሪው ክፍል በውሃ ላይ እየተንሳፈፈ ያሳይ ነበር።
የመርከቧ ባለቤቶች በወቅቱ መርከቧ ተጎትታ በአቅራቢያ ወደሚገኘው የጂቡቲ ወደብ እየተወሰደች መሆኗን፣ ነገር ግን ልትሰምጥ እንደምትችል አመልክተው ነበር።
መርከቧ በብሪታኒያ ተመዝግባ በአንድ የሊባኖስ ተቋም አማካይነት ስትንቀሳቀስ የቆየች ናት። ጥቃቱ በተፈጸመባት ጊዜም አሞኒየም ናይትሬት የተባለውን ማዳበሪያ ጭና እንደነበር ተነግሯል።
በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እውቅና ያለው የየመን መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር አህመድ ቢን ሙባራክ፣ የመርከቧን መስመጥ “አጋጥሞ የማያውቅ የአካባቢ አደጋ ነው” ሲሉ ገልጸውታል።
በዓለም ዙሪያ ላሉ የውሃ አካላት ደኅንነት የሚከራከረው የአካባቢ ጥበቃ ተከራካሪው ግሪን ፒስ በበኩሉ የአሞኒየም ናይትሬት ማዳበሪያው ወደ ባሕሩ መግባት “ከውሃ በታች ባለው ሥነ ምኅዳር ላይ ከፍተኛ ተጽእኖን ይፈጥራል” ብሏል።
ሁቲዎች በጋዛ ውስጥ ላሉ ፍልስጤማውያን ያላቸውን ድጋፍ ለማሳየት ካለፈው ኅዳር ጀምሮ በቀይ ባሕር እና በኤደር ባሕረ ሰላጤ በኩል በሚያቋርጡ ከእስራኤል ጋር ግንኙነት አላቸው ባሏቸው መርከቦች ላይ ጥቃት እየፈጸሙ ነው።
ለዚህም ምላሽ አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም የመን ውስጥ በሚገኙ የሁቲ ይዞታዎች ላይ ተከታታይ የአየር ጥቃቶችን ፈጽመዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩናይትድ ኪንግደም የባሕር ላይ ንግድ ተቋም ቅዳሜ ዕለት እንዳሳወቀው፣ ከየመኗ ወደብ ሞካህ በስተ ምዕራብ አንዲት መርከብ ላይ ጥቃት እንደተፈጸመ ሪፖርት ደርሶታል።
ጨምሮም “የመርከቧ ሠራተኞች መልህቋን እንድትጥል አድርው በወታደራዊ ባለሥልጣናት ከመርከቧ እንዲወጡ ተደርገዋል” ብሏል።
የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ “እራስን ለመከላከል በተወሰድ እርምጃ” ከየመን በኩል በሁቲዎች ሊተኮስ ተዘጋጅቶ የነበረ ከምድር ወደ አየር የሚወነጨፍ ሚሳኤልን መምታቱን አሳውቋል።
ወታደራዊ ማዘዣው ሊወነጨፍ የነበረው ሚሳኤል በአሜሪካ አውሮፕላን ላይ አሳሳቢ ስጋትን ደቅኖ እንደነበር አመልክቷል።
የአማጺያኑ ጥቃት የዓለም የባሕር ላይ ንግድ 12 በመቶው በሚዘዋወርበት በወሳኙ የቀይ ባሕር በኩል የሚያቋርጡ የግዙፍ የጭነት መርከብ ኩባንያዎች መስመራቸውን እንዲቀይሩ አስገድዷል።
ምንም እንኳን በአሜሪካ የሚመራው የባሕር ኃይል ጥምረት አገራት በሁቲ ዒላማዎች ላይ የአየር ጥቃት መፈጸም ከጀመሩ አንድ ወር ቢያልፋቸውም፣ አማጺያኑ አሁንም በመርከቦች ላይ ከባድ ጥቃቶችን የመፈጸም አቅም እንዳላቸው አሳይተዋል።
ሁቲዎች በቀይ ባሕር ላይ በሚተላለፉ የምዕራባውያን መርከቦች ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት የሚያቆሙት፣ እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ውስጥ በሐማስ ላይ የምታካሂደውን ወታደራዊ ዘመቻ ስታቆም መሆኑን አሳውቀዋል።















