ሁቲዎች በቀይ ባሕር አንዲት የጭነት መርከብ ላይ በፈጸሙት ጥቃት ከባድ ጉዳት አደረሱ

የፎቶው ባለመብት, EPA
በብሪታኒያ የተመዘገበች ግዙፍ የጭነት መርከብ ከየመን ሁቲ አማጺያን በተተኮሰ ሚሳኤል ከባድ ጉዳት ከደረሰባት በኋላ መርከበኞቿ መርከባቸውን ጥለው መሸሻቸው ተነገረ።
የደኅንነት ተቋማት እንዳሉት መርከቧ በሚሳኤል የተመታችው በኤደን ባሕረ ሰላጤ ላይ ወደ ባብ ኤል ማንደን ሰርጥ እየተጠጋች ሳለ ነው።
የሁቲ ታጣቂዎች ወታደራዊ ቃል አቀባይ እንዳለው መርከቧ “እጅግ አውዳሚ የሆነ ጉዳት” ስለደረሰባት የመስመጥ አደጋ ተጋርጦባታል።
የዩናይትድ ኪንግደም የባሕር ትራንስፖርት ባለሥልጣናት እንዳረጋገጠው መርከቧ ላይ ከባድ ፍንዳታ ከደረሰ በኋላ የመርከቧ ሠራተኞች ከመርከቧ እንዲወርዱ ተደርጓል።
ጥቃቱ በኢራን ይደገፋሉ የሚባሉት ሁቲዎች አስካሁን ከፈጸሙት ሁሉ ከባድ ጉዳትን ያደረሰ ነው ተብሏል። ይህም የሁቲዎችን ጥቃት ለማስቆም ጥረት እያደረጉ ያሉት ምዕራባውያን ስኬታማ ለመሆን ገና ብዙ እንደሚቀራቸው አመልካች ነው።
በእስራኤል እና በሐማስ መካከል ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ሁቲዎች ለፍልስጤማውያን ያላቸውን ድጋፍ ለማሳየት ከኅዳር አጋማሽ ጀምሮ በቀይ ባሕር በኩል በሚያቋርጡ የንግድ እና የምዕራባውያን የጦር መርከቦች ላይ በሚሳኤል እና በድሮን ጥቃት እያፈጸሙ ይገኛሉ።
ጥቃቱም የዓለም የባሕር ላይ ንግድ 12 በመቶው በሚዘዋወርበት በወሳኙ የቀይ ባሕር መስመር የሚያቋርጡ የግዙፍ የጭነት መርከብ ኩባንያዎች መስመራቸውን እንዲቀይሩ አስገድዷል።
የሁቲዎችን ጥቃት ለማስቆምም አሜሪካ እና ብሪታኒያ በምዕራብ የመን ውስጥ በሁቲዎች በተያዙ አካባቢዎች ያሉ ኢላማዎችን በአየር መደብደብ ከጀመሩ አንድ ወር ሆኗቸዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም የባሕር ትራንስፖርት ንግድ አገልግሎት ድርጅት ጥቃቱ የተፈጸመባት መርከብ የየመን የቀይ ባሕር ወደብ ከሆነችው ሞቻ 65 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ችግር እንዳጋጠማት የሚያመልክት ሪፖርት የተቀበለው እሁድ ምሽት ላይ ነው።
ሰኞ ጠዋት ደግሞ በመርከቧ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ሠራተኞቿ ከመርከቧ ላይ ወርደው መሸሻቸውን ወታደራዊ ባለሥልጣናት አሳውቀዋል።
የባሕር ላይ ጉዞ ደኅንነት ተቋማት ባወጡት መረጃ መሠረት መርከቧ በሁለት ሚሳኤሎች ተመትታ ጉዳት ከደረሰባት በኋላ ባለችበት ቦታ ላይ መልህቋን ጥላ ቆማለች።
የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥትም ወደ መርከቧ ውሃ እየገባ መሆኑን እና ሠራተኞቿ በሙሉ ከመርከቧ ወርደው ደኅንነትታቸው ወደሚጠበቅ ስፍራ መወሰዳቸውን አረጋግጧል።
የሁቲ ወታደራዊ ቃል አቀባይ ያህያ ሳሪ ሰኞ ጠዋት ባወጣው መግለጫ፣ የሁቲ ባሕር ኃይል በርካታ ሚሳኤሎችን በኤደን ባሕረ ሰላጤ ላይ ስትጓዝ በነበረች የብሪታኒያ መርከብ ላይ መተኮሱን አስታውቋል።
ዝርዝር መረጃ ሳይሰጥም “መርከቧ አደገኛ ጉዳት ደርሶባት ሙሉ ለሙሉ ለመቆም ተገዳለች። በዚህም ሳቢያ የመስመጥ አደጋ ተጋርጦባታል። የመርከቧ ሠራተኞችም ጉዳት ሳይደረስባቸው እንዲወጡ አድርገናል” ብሏል።
በቀይ ባሕር ላይ የሚቀዝፉ ግዙፍ የጭነት መርከቦች ከሁቲ ታጣቂዎች በሚሰነዘርባቸው ጥቃት ስጋት ላይ ስለወደቁ የጉዞ መስመራቸውን ቀይረው ተጨማሪ በርካታ ቀናትን የሚፈጀውን ረጅም የባሕር ላይ ጉዞ መስመር እየመረጡ ነው።
በዚህም በቀይ ባሕር በኩል ወደ አውሮፓ የሚጓዙ መርከቦች ወደ ታች ወደ ደቡብ አፍሪካ በማቅናት አፍሪካ ዞረው ለመጓዝ በመገደዳቸው ወጪቸው መጨመሩ ተነግሯል።















