አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም በየመን የሁቲ ይዞታዎች ላይ የአየር ጥቃት ፈጸሙ

የጦር አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, ROYAL AIR FORCE

የአሜሪካ እና የዩናይትድ ኪንግደም ተዋጊ አውሮፕላኖች በየመን ውስጥ በሚገኙ 18 የሁቲ ይዞታዎች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚኒስቴር ፔንታገን አስታወቀ።

ሁለቱ አገራት በጋራ ተመሳሳይ ጥቃት ሲፈጽሙ ይህ ለአራተኛ ጊዜ ሲሆን፣ ኢላማ ያደረጉትም የሁቲ መጋዘኖችን፣ የድሮን እና የአየር ጥቃት መከላከያ መዋቅሮችን እንዲሁም ታጣቂዎቹ የሚንቀሳቀሱበትን ሄሊኮፕተር መሆኑን አሜሪካ አሳውቃለች።

ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) በበኩሏ የምዕራባውያን አገራቱ እርምጃውን የወሰዱት የሁቲ ታጣቂዎችን ጥቃት የፈጸም አቅምን “የበለጠ ለማዳከም” ነው ብላለች።

በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች ለባሕር ንግድ እንቅስቃሴ ወሳኝ በሆነው በቀይ ባሕር በሚንቀሳቀሱ በመርከቦች ላይ ጥቃቶችን ሲፈጽሙ ቆይተዋል።

የየመን ዋና ከተማ ሰንዓን ጨምሮ ሰፊ የአገሪቱን ግዛት የሚቆጣጠሩት ሁቲዎች ጋዛ ውስጥ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት ለፍልስጤማውያን ያላቸውን ድጋድ ለማሳየት የእስራኤል እና የምዕራባውያን የሚሏቸውን መርከቦች ኢላማ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

በቀይ ባሕር ላይ ሁቲዎች በሚፈጽሙት ጥቃት ምክንያት ታላላቅ የመርከብ ጭነት አጓጓዥ ኩባንያዎች የጉዞ መስመራቸውን በመቀየራቸው፣ በዓለም ንግድ ላይ የአቅርቦት መስተጓጎል ከመፍጠሩ በላይ የዋጋ ጭማሪም አስከትሏል።

ካርታ

የዩኬ እና የአሜሪካንን ጥቃት በተመለከተ ፔንታጎን ባወጣው የጋራ መግለጫ፣ የቅዳሜው ጥቃት “ከመሬት በታች ያሉ የጦር መሳሪያ እና የሚሳኤል ማከማቻዎች፣ የድሮን መዘዣ፣ የአየር ጥቃት መከላከያ እና የራዳር ማዕከሎች እንዲሁም ሄሊኮፕተር” ላይ ጥቃት መፈጸሙን አሳውቋል።

“አስፈላጊ እና ተመጣጣኝ ነው” በተባለው በዚህ ጥቃት በየመን የተለያዩ ክፍሎች ውስጥ በሚገኙ ስምንት ቦታዎች ላይ ባሉ 18 ኢላማዎች ላይ መፈጸሙንም አሜሪካ መከላከያ መሥሪያ ቤት አመልክቷል።

ኢላማዎችን ብቻ ነጥሎ ለመምታት በተወሰደው እርምጃ “ሁቲዎች በዚህ ወሳኝ በሆነው የባሕር እንቅስቃሴ መስመር በዓለም አቀፍ ንግድ፣ በባሕር ኃይል መርከቦች እና በመርከቦች ሕይወት ላይ የሚደቅኑትን ስጋት በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነስ ያለመ ነው።”

መግለጫው ጨምሮም “ከኅዳር ወር አንስቶ ሁቲዎች ከ45 በላይ በሚሆኑ የንግድ እና የባሕር ኃይል መርከቦች ላይ ጥቃት በመፈጸም ለዓለም አቀፉ ምጣኔ ሀብት፣ ለአካባቢው ደኅንነት እና መረጋጋት አደጋ በመሆናቸው ዓለም አቀፍ ምላሽ ሊሰጣቸው ይገባል” ብሏል።

የቅዳሜ ምሽቱ ጥቃት የተፈጸመውም “ከአውስትራሊያ፣ ከባህሬን፣ ከካናዳ፣ ከዴንማርክ፣ ከኔዘርላንድስ እና ከኒውዚላንድ” በተገኘ ድጋፍ አማካይነት ነው ተብሏል።

ጥቃቱ ከተፈጸመ ከአጭር ጊዜ በኋላ የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን “የዓለም ወሳኝ በሆነው የባሕር መስመር ላይ የሚደረግን ነጻ የሰዎች እና የንግድ እንቅስቃሴ ለመጠበቅ አሜሪካ አስፈላጊ የሆነውን እርምጃ ከመውሰድ አታመነታም” ሲሉ ተናግረዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም የመከላከያ ሚኒስትር ግራንት ሻፕስ በበኩላቸው “የሰዎችን ሕይወት እና የባሕር ላይ ነጻ እንቅስቃሴ ደኅንነትን የመጠበቅ ኃላፊነት ስላለብን አየር ኃይላችን የመን ውስጥ ባሉ ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ በተፈጸመው ጥቃት ውስጥ ተሳታፊ ሆኗል” ብለዋል።

ከዚህ ጥቃት ቀደም ብሎ የአሜሪካ ጦር ሠራዊት እንዳስታወቀው ጥቃት ለመፈጸም የተዘጋጁ ናቸው ያላቸውን ሰባት የሁቲ ተንቀሳቃሽ ፀረ መርከብ ሚሳኤሎችን ማውደሙን አስታውቆ ነበር።