ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሆንግ ኮንግ 11 ኪሎግራም ‘ኮኬይን’ በዊልቸር ውስጥ ተደብቆ ተያዘ
የሆንግ ኮንግ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ባለስልጣናት 11 ኪሎግራም ኮኬይን መሆኑ የተጠረጠረ አደንዛዥ ዕጽ በኤሌክትሪክ ዊልቸር መቀመጫ ስር ተደብቆ ማግኘታቸው ተገለጸ።
1.5 ሚሊዮን ዶላር የተገመተው ኮኬይን የተገኘው የ51 ዓመት ግለሰብ በጉምሩክ መፈተሻ በኩል ሲያልፍ ነው።
ግለሰቡ ከካሪቢያኗ ሴንት ማርቲን በፓሪስ በኩል ሆንግ ኮንግ ሲደርስ በቁጥጥር ስር ውሏል።
በአደገኛ ዕጽ ዝውውር ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ የዕድሜ ልክ እስራት ሊጠብቀው ይችላል ተብሏል።
የጉምሩክ ባለሥልጣናት እንደተናገሩት ተጠርጣሪው ዊልቸሩን ወደ ሃገር ውስጥ ለማስገባት የሞከረው ከያዛቸው ሁለት ሻንጣዎች በአንዱ ነው።
የጉምሩክ ሠራተኞች ጥርጣሬ ስለገባቸው ተጨማሪ ምርመራ አድርገዋል።
በዚህም በመቀመጫው ትራስ በመደገፊያው ውስጥ ኮኬይን ተሰግስጎ አግኝተዋል።
የሆንግ ኮንግ ተወላጅ ያልሆነው እና የመንቀሳቀስ ችግር ያለበት ግለሰቡ፤ የመኪና አከራይ ድርጅት ዳይሬክተር መሆኑን እና ዊልቸሩን ከጓደኛው መዋሱን ተናግሯል።
በጉዳዩ ዙሪያ ምርመራ መጀመሩ ተገልጿል።
የጉምሩክ ባለሥልጣኖች ድንበር ተሻጋሪ የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውርን ለመዋጋት "ከፍተኛ ተጋላጭ ከሆኑ አካባቢዎች" የሚመጡ ጎብኝዎች ላይ የሚደረገውን ፍተሻ እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል።
በአውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ በዊልቸር መቀመጫ ውስጥ አደንዛዥ እጽ ተደብቆ ሲገኝ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ባለፈው ህዳር የኒውዮርክ ባለስልጣናት 450 ሺህ ዶላር የሚያወጣ ኮኬይን በአንዲት ሴት ዊልቸር ወንበር ጎማዎች ውስጥ ተደብቆ በቁጥጥር ስር አውለዋል።
እአአ በ2022 በጣሊያኗ ሚላን ከተማ 1.6 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ኮኬይን በሞተር በሚሠራ ዊልቸር ወንበር ላይ ተደብቆ ተገኝቷል።