ዜሌንስኪወደ አሜሪካ ተጉዘው ከፕሬዝዳንት ባይደን ጋር ሊገናኙ ነው ተባለ

የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ዛሬ ረቡዕ ታህሣሥ 12/2015 ዓ.ም. ወደ ዋሽንግተን ተጉዘው ከፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጋር ሊገናኙ ይችላሉ ተባለ።

ዜሌንስኪ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ከፈጸመች በኋላ ይህ የመጀመሪያው የውጭ አገር ጉዟቸው ይሆናል።

አንድ በስም ያልተጠቀሱ የመንግሥት ባለስልጣን ዜሌንስኪ ለአሜሪካ ኮንግረስ ንግግር ያደርጋሉ ሲሉ ለአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።

የፕሬዝዳንቱን የአሜሪካ ጉብኝት በተመለከተ እስካሁን ድረስ ከሁለቱ አገራት ይፋዊ ማረጋገጫ አልተሰጠም።

የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ትናንት ማክሰኞ የኮንግረስ አባላት ረቡዕ ከምክር ቤት እንዳይቀሩ ተናግረዋል ተብሏል።

“እባካችሁ ለዴሞክራሲ ልዩ ትኩረት ስለሚሰጥ እንድትገኙ” ሲሉ የምክር ቤት አባላት ዛሬ በምክር ቤት እንዲገኙ በጽሑፍ ማሳሰባቸው ዜሌንስኪ ለኮንግረስ ንግግር ሊያደርጉ ይችላሉ መባሉን የሚያጠናክር ሆኗል።

ዜሌንስኪ ከዚህ ቀደም የተለያዩ አገራት መሪዎችን እና ከፍተኛ ባለስልጣናትን በዩክሬን መዲና ኪዬቭ ተቀብለው ሲያነጋግሩ ነበር። በዩክሬን የተለያዩ ቦታዎች በመንቀሳቀስም ወታደሮቻቸውን ሲያበረታቱ ተይተዋል። ከዚህ በተጨማሪም በስልክ እና በቪዲዮ ጥሪ ከመሪዎች ጋር ሲነጋገሩ እና በተለያዩ ጉባኤዎች ላይ ንግግር አድርገዋል።

11 ወራት ገደማ ከሆነው ወረራ በኋላ ግን ይህ የአሜሪካው ጉብኝት የመጀሪያው የውጭ አገር ጉዟቸው ነው የሚሆነው።

ተንታኞች ይህ ጉዞ የዩክሬን እና የአሜሪካን ወዳጅነት ጥንካሬ የሚያሳይ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል ይላሉ።

በዚህ ጦርነት አሜሪካ ለዩክሬን ከፍተኛ የሆነ የጦር ድጋፍ ስታደርግ ቆይታለች።

እስካሁን ያሉት አሃዞች እንደሚያሳዩ ጦርነቱ ከተጀመረ አንስቶ አሜሪካ 18.5 ቢሊዮን ዶላር ለዩክሬን ድጋፍ አድርጋለች።

ከአሜሪካ በመቀጠል ጀርመን የ2.34 ቢሊዮን ዶላር ደጋፍ ስታደርግ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፖላንድ እና ካናዳ እንደ ቅድመ ተከተላቸው 1.9 ቢሊዮን፣ 1.82 ቢሊዮን እና 0.99 ቢሊዮን የጦር ድጋፍ አድርገዋል።

ፈረንሳይ፣ ቼክ ሪፓብሊክ፣ ስዊድን፣ ኢስቶኒያ እና ጣሊያን ከፍተኛ ሊባል የሚችል የጦር ድጋፍ ለኪዬቭ ካደረጉ አገራት ዝርዝር ውስጥ ይካተታሉ።

ይሁን እንጂ ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ አሁንም ዓለም አቀፉ ማሕብረሰብ አገራቸው ከሩሲያ ጋር ለምታደርገው ጦርነት ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል እየጠየቁ ነው።

ፕሬዝዳንቱ የዩክሬን ወርሃዊ ወጪ 5 ቢሊዮን ዶላር ነው ይላሉ።

ሩሲያ ዩክሬን ላይ ወረራ ከፈጸመች ወዲህ ቢያንስ 100ሺህ የሩሲያ ወታደሮች እንዲሁም 100ሺህ የዩክሬን ወታደሮች ሳይገደሉ ወይም ሳይቆስሉ እንደማይቀሩ የአሜሪካ ጦር ባለስልጣን ግምታቸውን ሰጥተው ነበር።

ከጦር ሠራዊት አባላት ሞት እና ጉዳት በተጨማሪ 40ሺህ ሰላማዊ ሰዎች ስለመገደላቸው ግምት አለ።

የተባበሩት መንግሥታት ደግሞ በሩሲያ ጨምሮ በመላው አውሮፓ 7.8 ሚሊዮን ዩክሬናውያን ተፈናቃዮችን ስለመመዝገቡ ገልጿል።

ይህ አሃዝ ግን ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው እዛው ዩክሬን ውስጥ የሚገኙትን አያጠቃልልም።