ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሐማስ ትልቅ ተስፋ በተጣለበት የዶሃ የሰላም ስምምነት አልሳተፍም አለ
አንድ ከፍተኛ የሐማስ ባለሥልጣን በጋዛ-እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነቱ ውስጥ ድርጅታቸው እንደማይሳተፍ ለቢቢሲ አረጋገጡ።
በዶሃ ዛሬ ሐሙስ ይፈጸማል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ስምምነት እስራኤል በጋዛ ላይ ጦርነት እንድታቆም እና ሐማስ ያገታቸውን እስራኤላዊያንን እንዲለቅ የሚያስችል ነበር።
ሐማስ ከዚህ ወዲያ ድርድሩ ውስጥ ለወጉ ያህል መሳተፍ ታክቶኛል ሲል ይፋ አድርጓል። የሰላም ድርድሩ እምነት የሚጣልበት እንዲሆን ግልጽ ፍኖተ ካርታ ያለው መሆን አለበት ብሏል፣ ሐማስ።
ፍኖተ ካርታው በግንቦት ወር በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የቀረበው እንዲሆን የጠየቀው ሐማስ እስራኤል ግን በየጊዜው ጦርነቱን ለመቀጠል አዳዲስ ቅድመ ሁኔታዎችን እያስቀመጠች፣ ሕዝባችንን እየጨረሰች ነው ሲል ከሷል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር በበኩላቸው የሐማስን ክስ አጣጥለዋል።
ያም ሆኖ በዶሃ ዛሬ የሚደረገው ንግግር ያለ ሐማስ ተሳትፎም ቢሆን እንደሚቀጥል ተነግሯል። በድርድሩ የግብጽና የኳታር አሸማጋዮች ይገኙበታል።
ተስፋ ተጥሎበት የነበረው የእስራኤልና ሐማስ ድርድር ከሳምንት በፊት የሐማሱ የፖለቲካ መሪ ኢስማኤል ሐኒያ በቴህራን መገደላቸውን ተከትሎ ነው ሊደናቀፍ የቻለው።
ሟቹ ኢስማኤል ሐኒያ ከሐማስ በኩል ዋናው ተደራዳሪ ነበሩ።
አሜሪካ በበኩሏ ይህን የሰላም ስምምነት ሐሳብ ቶሎ እንዲፈረም ማድረግ ኢራን እወስደዋለሁ እያለች ያለችውን የበቀል እርምጃ ለማስቆም ሁነኛ ሚና ይጫወታል ብላ ታምናለች።
ኢራን በማንኛውም ወቅት የኢስማኤል ሐኒያን ግድያ ለመበቀል በእስራኤል ላይ የአየር ጥቃት ልትሰነዝር እንደምትችል እየዛተች ነው።
የኳታሩ ጠቅላይ ሚኒስትር መሐመድ ቢን አቡዱረሕማን አልታኒ እና የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከን በስልክ ባደረጉት ውይይት ኢራን ጥቃት ሰንዝራ አካባቢውን ወደለየለት የትርምስ ቀጠና እንዳትቀይረው አበክረው አሳስበዋል።
ብሊንከን ከኳታሩ ጠቅላይ ሚኒስትር በተጨማሪ ከግብጹ አቻቸው በድር አብዱላቲ ጋር በስልክ መምከራቸውን ተዘግቧል።
ይህ በእንዲህ ሳለ ጆ ባይደንና ምክትላቸው ካማላ ሐሪስ በብሔራዊ ደኅንነት አማካሪዎቻቸው በኩል ስለ ሰላም ድርድሩ ማብራሪያ እንደተሰጣቸው ዋይት ሐውስ ገልጿል።
የእስራኤል በጋዛ የወሰደችው መጠነ ሰፊ ዘመቻ 40ሺህ ለሚጠጉ ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኗል። አሐዙ ከሐማስ ጤና ሚኒስትር የተገኘ ነው።
ሐማስ መስከረም መጨረሻ ድንገት ጥቃት ከፍቶ 1200 ሰዎችን ከገደለና 251 ሰዎችን አፍኖ ከወሰደ በኋላ ነበር እስራኤል በጋዛ ላይ የማያባራ ጥቃት መሰንዘር የጀመረችው።
ይህ ስምምነት ተፈጻሚ ሲሆን የጋዛ ነዋሪዎች ከጦርነቱ ፋታ ያገኛሉ ተስፋ ተደርጎ ነበር።
በዚህ ስምምነት መሠረት ሁለቱ ተዋጊዎች ፊርማቸው እንዳኖሩ የሰብአዊ እርዳታ ወደ ጋዛ መግባት ይጀምራል። 111 በሐማስ የታገቱ ሰዎች ነጻ ይወጣሉ ተብሎ ተስፋ ተደርጎ ነበር።
ከጠቅላላ ታጋቾች ውስጥ 39 የሚሆኑት ሕይወታቸውን አጥተዋል።
በዛሬው የዶሃ ስብሰባ እስራኤል ተደራዳሪዎቿን እንደምትልክ የገለጸች ሲሆን ሐማስ ግን አዲስ ድርድር ውስጥ አልገባም፤ ባለፈው ግንቦት ወር በጆ ባይደን የቀረበው ሰነድ ተፈጻሚ እንዲሆን ነው ፍላጎቴ ብሏል።
ጆ ባይደን ባቀረቡት የሰላም ስምምነት ሐሳብ እስራኤል ከጋዛ ሰርጥ እንድትወጣ፣ በተለይ ደግሞ ጋዛን ከግብጽ ከሚያዋስናት ረዥሙ ፊላደልፊ ኮሪደር አካባቢ ጠቅልላ እንድትወጣ ይጠበቃል።
ከቀያቸው የተፈናቀሉ የሰሜን ጋዛ ነዋሪዎች ያለምንም ክልከላ ወደ ሥፍራቸው እንዲመለሱ እና ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ እንዲገባም ያስችላል።
ሐማስ እስራኤል ይህን ስምምነት ላለመፈረም ተጨማሪ ቅድመ ሁኔታዎችን እያስቀመጠች ነው ሲል ይወቅሳል።
በዚህ ግንቦት ወር መጨረሻ በጆ ባይደን በቀረበውና የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት እውቅና በሰጠው የሰላም ስምምነት ሐሳብ መሠረት በጋዛ ‘የተሟላ የተኩስ አቁም’ ለስድስት ሳምንታት ይደረጋል።
ከዚህ ሌላ የእስራኤል ወታደሮች ከአመዛኙ የጋዛ አካባቢ ለቀው ይወጣሉ። በምትኩ ሐማስ ካገታቸው ውስጥ ሴቶችና አዛውንቶች እንዲሁም የቆሰሉና የታመሙትን መርጦ ይለቃል።
እስራኤል በበኩሏ ያሰረቻቸውን ፍልስጤማዊያን ትፈታለች።
በሰላም ስምምነቱ ሁለተኛ ምዕራፍ ደግሞ ሐማስ የተቀሩትን ሁሉም ታጋቾች ይፈታል። ያልገደበ የሰብአዊ ድጋፉም ይቀጥላል።
በሦስተኛው ምዕራፍ ጋዛን መልሶ የማቋቋም ሥራዎች ይጀመራሉ።
ይህ ስምምነት ሊፈረም ቀነ ቀጠሮ ከተያዘ በኋላ ነበር እስራኤል ሌሎች አምስት 'ቅድመ ሁኔታዎችን ማስቀመጧ መዘገብ የጀመረው።
ኒውዮርክ ታይምስ እንደዘገበው አንድ ይህንኑ የሚያስረዳ ሰነድ እስራኤል ካስቀመጠቻቸው ተጨማሪ ቅድመ ሁኔታዎች አንዱ፣ ወታደሮች በጋዛ ሰርጥ ነዋሪ ከሚበዛባቸው ቦታዎች እንደሚለቁ፥ ነገር ግን ከፊላደልፊያ ኮሪደር እንደማይወጡ የሚያትት ነው።
ፊላደልፊያ ኮሪደር በጋዛና በግብጽ መካከል የሚገኝ ቁልፍ ቦታ ነው።
ቤንያሚን ናታንያሁ አዲስ የጨመርናቸው ቅድመ ሁኔታዎች የሉም፤ እነዚህ ግልጽ እንዲሆኑ ማብራሪያ የጠየቅንባቸው ነጥቦች ናቸው ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ሟቹን ኢስማኤል ሐኒያን የተኩት የሐማስ የፖለቲካ መሪ ያሕያ ሲንዋር የመስከረሙን መብረቃዊ ጥቃት የመሩ ሰው ናቸው፤ ለሰላም ስምምነቱ እንቅፋት የሆኑትም እርሳቸው ናቸው ስትል እስራኤል ትከሳለች።
በቴህራን የተገደሉትን ኢስማኤል ሐኒያን ደም ለመበቀል ኢራን ጥቃት ልትሰነዝር እንምትችል በተፈራበት በዚህ ወቅት ይህ ስምምነት ቢፈረም የኢራንን የበቀል እርምጃ ማስቀረት ይችላል ብለው ያምናሉ ምዕራባዊያን።
እስራኤል በበኩሏ ኢራን ዛቻዋን ተፈጻሚ ካደረገች በምላሹ አይቀጡ ቅጣት ይጠብቃታል ስትል ታስፈራራለች።