የሐሳን ናስራላህ ተተኪ የሄዝቦላህ መሪ መገደላቸውን የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ተናገሩ

የሐሰን ናስራላህ ተተኪ ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁት ግለሰብ መገደላቸውን የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ተናግረዋል።

የሊባኖሱ ሚሊሻ ቡድን ሄዝቦላህ ነባር መሪ የነበሩት ሐሰን ናስራላህ በእስራኤል ጥቃት የተገደሉት ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት ነበር።

የረጅም ጊዜ የሄዝቦላህ መሪ እና ተጽእኖ ፈጣሪ የነበሩት ሐሳን ናስራላህ ከተገደሉ በኋላ ቡድኑን የመምራቱን ኃላፊነት እንደያዙ የሚነገርላቸው ሐሻም ሳፌዲን በእስራኤል ኃይሎች መገደላቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ የመከላከያ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ፤ ሠራዊታቸው ከቀናት በፊት ሊባኖስ ውስጥ በፈጸመው ጥቃት ሳፌዲን “ተወግደዋል” ያሉ ሲሆን፣ ሄዝቦላህ በአሁኑ ጊዜ “በእጅጉ ተዳክሟል” ሲሉ አክለዋል።

በተጨማሪም የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት የሐሳን ናስራላህ ተተኪ የሆኑት የሄዝቦላህ ከፍተኛ መሪ ሐሻም ሳፌዲን “ሳይሞቱ አልቀሩም” በማለት ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ ለሊባኖስ ሕዝብ ባስተላለፉት መልዕክት አገራቸው በሄዝቦላህ የሚፈጸመውን ጥቃት በማስቆም ዜጎቻቸው በሰላም ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ “የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ” እንደሚያደርጉ እና እስራኤል ጦርነቱን እንደምታሸነፍ ተናግረዋል።

እስራኤል እየወሰደችው ባለው እርምጃ ዒላማቸው ሄዝቦላህ መሆኑን በመጥቀስም፣ የሊባኖስ ሕዝብ “አገሩን በራሱ ቁጥጥር ስር ማስገባት እንዳለበት” ካልሆነ ግን ሄዝቦላህ "በሕዝቡ ኪሳራ ውጊያውን እንደሚቀጥል” አሳስበዋል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የመከላከያ ሚኒስትር የሳፌዲንን መገደል ከመግለጻቸው ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ እስራኤል በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት በሚገኘው የሄዝቦላህ ማዕከል ላይ የአየር ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ ቡድኑ ከፍተኛ አመራሩ ከሆኑት ሐሻም ሳፌዲን ጋር ያለው ግንኙነት መቋረጡን የደኅንነት ምንጮች ለአልጀዚራ ገልጸው ነበር።

ነገር ግን ከቀናት በፊት የሄዝቦላህ የመገናኛ ብዙኃን ክፍል ባወጣው መግለጫ የሳፌዲን መገደልን በተመለከተ የሚሠራጩት ወሬዎች “ዋጋቢስ አሉቧልታዎች ናቸው” በማለት አጣጥሎ፣ ስለቡድኑ ትክክለኛ መረጃ የሚወጣው በመገናኛ ብዙኃን ቡድኑ በኩል መሆኑን አመልክቷል።

የታጣቂ ቡድኑ ሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ሊቀመንበር እና ከናስላራህ መገደል በኋላ የመሪነት ቦታውን ይይዛሉ የተባሉት ሐሻም ሳፌዲን ያሉበት ስፍራ ላይ ጥቃት የተፈጸመው ባለፈው አርብ መሆኑ ተነግሯል።

የእስራኤል ከፍተኛ ባለሥልጣናት የሄዝቦላህ ከፍተኛ አመራሩ መገደላቸውን በተመለከተ እርግጠኛ ሳይሆኑ ከቆዩ ከቀናት በኋላ ማክሰኞ ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የመከላከያ ሚኒስትሩ ሳፌዲን በአየር ኃይላቸው ጥቃት እንደተገደሉ የሚያረጋግጥ መግለጫ ሰጥተዋል።

የእስራኤል ጦር በሊባኖስ ግዛት ውስጥ ወረራ በማካሄድ ላይ ባለበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ በጽህፈት ቤታቸው በኩል ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት ላይ እንዳስታወቁት በጥቃቱ ሁለት የሄዝቦላህ ከፋተኛ አመራሮች ተገድለዋል።

“ሄዝቦላህ ያለውን አቋም አዳክመነዋል። ሐሳን ናስራላህን፣ የናስላራህ ተተኪ [ሳፌዲን] እና የተተኪውን ተተኪን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሽብርተኞችን አስወግደናል” ብለዋል። ነገር ግን ተገድለዋል ያሏቸውን የሁለቱን የናስራላህ ተተኪዎች በስም አልጠቀሱም።

ከኔታኒያሁ ቀደም ብሎ የእስራኤሉ የመከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላት የናስራላህ ተተኪ የሆኑት ሐሻም ሳፌዲን በሠራዊታቸው ጥቃት “ሳይወገዱ” አይቀሩም ብለው ነበር።

የእስራኤል መንግሥት ባለሥልጣናት ማክሰኞ ዕለት እንዳረጋገጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የናስራላህ “ተተኪ እና የተተኪው ተተኪ” ብለው የገለጿቸው የሄዝቦላህ ከፍተኛ ባለሥልጣናት የሆኑት ሐሻም ሳፌዲን እና ናይም ቃሲም እንደሆኑ ገልጸዋል።

ከማክሰኞ የእስራኤል መግለጫ በኋላ ሄዝቦላህ እስካሁን ስለከፍተኛ አመራሮቹ ሞት ማስተባበያም ሆነ ማረጋገጫ አልሰጠም።

የሄዝቦላህ መሪ ሐሳን ናስራላህ መስከረም 17/2017 ዓ.ም. በእስራኤል አየር ኃይል በተፈጸመ ጥቃት ከተገደሉ በኋላ ከናስራላህ ጋር ዝምድና ያላቸው ሳፌዲን እና ምክትል ዋና ፀሐፊው ናይምረ ቃሲም ቡድኑን እየመሩት እንደሆነ ይነገራል።

ለአንድ ዓመት ያህል ከደቡባዊ ሊባኖስ ወደ ሰሜናዊ እስራኤል ሮኬቶችን ሲተኩስ የቆየው ሄዝቦላህ፣ ከእስራኤል በኩል የከባድ መሳሪያ እና የአየር ድብደባ የአጸፋ ጥቃት ሲደርስበት ቆይቷል።

ከመስከረም አጋማሽ ጀምሮ እስራኤል የጥቃት አድማሷን በማስፋት የቡድኑ ይዞታዎች ናቸው የምትላቸውን ስፍራዎች በዋና ከተማዋ ቤይሩት ጭምር የአየር ድብደባዎችን እየፈጸመች ነው።

ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ደግሞ እግረኛ ሠራዊቷን ወደ ሊባኖስ ግዛት በማዝመት ወረራ እያካሄድች ሲሆን፣ እስካሁን ድረስ በመላዋ ሊባኖስ በተፈጸሙ ጥቃቶች ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች ተገድለዋል። በተጨማሪም ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ጥቃት በመሸሽ ለመፈናቀል ተዳርገዋል።