በጃካርታ ትምህርት ቤት ውስጥ በሚገኝ መስጊድ ላይ በደረሰ ፍንዳታ ከ50 በላይ ሰዎች ተጎዱ

በኢንዶኔዢያ መዲና ጃካርታ ትናንት በመስጊድ ላይ በደረሰ ፍንዳታ ከ50 በላይ ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገለጸ።

በትምህርት ቤት ውስጥ በሚገኝ መስጊድ ላይ ለደረሰው ፍንዳታ የ17 ዓመት ተማሪ ተጠያቂ እንደሆነ ይፋ ተደርጓል።

በጃካርታ በሚገኘው ካሌፓ ዳዲግ አካባቢ በደረሰው ፍንዳታ በብዛት የተጎዱት ተማሪዎች ናቸው። አብዛኞቹ ተማሪዎች ሰውነታቸው ላይ ቃጠሎ እንደደረሰባቸው እና ፍንዳታውን አድርሷል የተባለው ተጠርጣሪም እንደተጎዳ ተገልጿል።

የኢንዶኔዢያ የፖሊስ ኃላፊ ሊስታዮ ሲጊት ፕራባዎ ምርመራ እየተካሄደ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

"ተጠርጣሪው እንዴት ጥቃቱን እንደፈጸመ ለማወቅ ምርመራ ጀምረናል" ብለዋል።

ፍንዳታውን ተከትሎ ሌሎች ተቀጣጣይ ነገሮችን ለማሰስ ቦምብ አምካኝ ቡድን ወደ ትምህርት ቤቱ ተልኳል።

አንድ ተማሪ ለኢንዶኔዢያ ብሔራዊ ቴሌቭዥን ጣቢያ እንደገለጸው፤ ፍንዳታውን አድርሷል የተባለው ተማሪ ቤት ውስጥ ቦምብ ሠርቶ ወደ ትምህርት ቤት ወስዷል።

ሌሎች ተማሪዎች ተጠርጣሪውን ያንጓጥጡት እንደነበረም ገልጿል።

ከፍንዳታው በኋላ መሬት ላይ ተኝቶ የተገኘ ሌላ ተማሪ በበኩሉ ተጠርጣሪው "ብቸኛ" እንደሆነ እና ነውጠኛ የሆኑ ምሥሎችን ይሠራ እንደነበር ተናግሯል።

በትምህርት ቤቱ የምትሠራ ምግብ አብሳይ ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደገለጸችው፤ ከፍንዳታው በኋላ ትምህርት ቤቱ በነጭ ጭስ ታፍኗል።

"ልባችን በፍጥነት እየመታ ነበር። መተንፈስም ተሳነን" ስትልም የነበረውን ሁኔታ ገልጻለች።

የጃካርታ ፖሊስ ከፍተኛ ኦፊሰር በትምህርት ቤቱ ሁለት መሣሪያ የሚመስሉ ቁሶች መገኘታቸውን አረጋግጠዋል።

የኢንዶኔዢያ ብሔራዊ ቴሌቭዥን ጣቢያ አንታራ ያሳየው ምሥል አንድ ሰብማሸን ሽጉጥ እና ሌላ የእጅ ሽጉጥ እንደተገኘ ይጠቁማል።

ሰብማሽን ሽጉጡ ላይ "14 ቃላት ለአጋርታ" እና "ብሬንተር ታረንት እንኳን ወደ ገሀነም መጣህ" የሚሉ ጽሑፎች ይነበባሉ።

በሥፍራው ሽጉጥ ለማስቀመጥ የሚውል አረንጓዴ ቀበቶም ተገኝቷል።

ስሙ በሽጉጡ ላይ የተጻፈው ብሬንተር ታረንት እአአ በ2019 በኒው ዚላንድ ክራይስትቸርች ኢስላሚክ ማዕከል ላይ የጅምላ ተኩስ መክፈቱ ይታወሳል።

በጥቃቱ 51 ሰዎች ሲገደሉ ሌሎች በርካታ ሰዎችም ተጎድተዋል።

አንድ ትምህርት ቤቱን የጎበኙ ባለሥልጣን በበኩላቸው ለሲኤንኤን እንደተናገሩት፤ የተገኙት ሽጉጦች "እውነተኛ ሽጉጥ ሳይሆኑ መጫወቻ ናቸው" በማለት አስተባብለዋል።

የኢንዶኔዢያ የፖሊስ ኃላፊ ሊስታዮ ሲጊት ፕራባዎ፤ ምርመራ እየተካሄደ ስለሆነ ፍንዳታው "የሽብር ጥቃት" ተደርጎ መወሰድ የለበትም ብለዋል።

በሙስሊሞች ብዛት ኢንዶኔዢያ ከዓለም ቀዳሚ አገር ናት።