ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በብራዚሏ ሪዮ ዲ ጄኔሮ 132 ሰዎች የተገደሉበት እና ከፖሊስ ጋር በድሮን የታገዘ ፍልሚያ ያደረገው የወንጀል ቡድን
ማክሰኞ ዕለት በራዚሏ ሪዮ ዲ ጄኔሮ ውስጥ ድሆች የሚኖሩባቸው ሁለት አካባቢዎች ፖሊስ ባካሄደው መጠነ ሰፊ ዘመቻ የተነሳ ጎዳናዎቿ በእሳት እና በሞቱ ሰዎች አስከሬን ተሞልቶ ነበር።
በሰሜን ሪዮ ዲ ጄኔሮ የድሆች መኖሪያ በሆኑት አሉማኦ እና ፔናህ ፖሊስ እና የወንበዴ ቡድን አባላት ባካሄዱት ጦርነት ሊባል በሚችል ፍልሚያ 132 ሰዎች ሞተዋል።
የወንጀል ቡድኖቹ ፖሊስ ላይ በድሮን በመታገዝ ጥቃት ፈጽመዋል፤ ፖሊስም ከዚህ ቀደም ከወሰዳቸው እርምጃዎች ሁሉ የከፋው ነው የተባለውን ኃይል ተጠቅሟል።
የከተማዋ ፖሊስ በድሆች ወንበዴ ቡድኖችን ለመቆጣጣር በሚል በከተማው የሚያካሄደው ዘመቻ ያልተለመደ አይደለም።
በተለይ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ጉባዔዎች ከመካሄዳቸው በፊት እንደዚህ ዓይነት ወንበዴዎችን የመመንጠር ሥራ የተለመደ ነው። የአሁኑ የሚለየው ግን የሞቱት ሰዎች ቁጥር የአገሪቱን ፕሬዝዳንት ጨምሮ በርካቶችን ያስደነገጠ መሆኑ ነው።
ፖሊስ ዘመቻ የከፈተበት 'ኮማንዶ ቬርሜልሆ' የተባለው የወንበዴዎች ቡድን በብራዚል ለረዥም ዓመታት የቆየ አደገኛ የወንጀል ቡድን ነው።
ስሙ በፖርቹጋልኛ "ቀዩ ዕዝ" በመባል የሚታወቅ ሲሆን፣ ብራዚልን እስከ አውሮፓውያኑ 1985 ድረስ ካስተዳደራት አምባገነኑ ወታደራዊ መንግሥት ዘመን ከተመሠረተው ከግራ ዘመም የእስረኞች ድርጅት ጋር ይያያዛል።
ፖሊስ ማክሰኞ ዕለት በሰሜናዊ የሪዮ ዲ ጄኔሮ በፔናህ እና አሌማኦ መኖሪያ አካባቢዎች መካከል አሰሳውን የጀመረ ሲሆን፣ ቀስ በቀስ ወደ ሪዮ ዲ ጄኔሮ ከተማ ዋና ክፍል ተስፋፍቷል።
ሱቆች ከተለመደው ጊዜ ቀደም ብለው ተዘጉ። የባቡር መስመሮች በሰዎች ተጨናነቁ እንዲሁም የአውቶቡስ መቆሚያዎች ወደ ቤታቸው ለመድረስ በሚጣደፉ ሰዎች ተሞሉ።
በሪዮ ዲ ጄኔሮ ታሪክ ከፍተኛ ወድመት ያስከተለ ነው የተባለው የፖሊስ እርምጃ 100 ያህል የወንበዴ ቡድን አባላትን በቁጥጥር ሥር ለማዋል እና የኮማንዶ ቬርሜልሆ ቡድንን መስፋፋት ለመግታት ያቀደ ነበር።
በፖሊስ እና በወንጀለኛ ቡድኑ መካከል በተካሄደው የተኩስ ልውውጥ ከሞቱት 132 ሰዎች መካከል አራቱ የፖሊስ ባልደረቦች ናቸው።
ከ100 በላይ ጠመንጃዎች እንዲሁም 81 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
በዚህ ዘመቻ ላይ 2,500 የፖሊስ አባላት ተሰማርተው ነበር ተብሏል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ይህ የወንጀል ቡድን በብራዚል ግዛቱን እያስፋፋ መጥቷል። በቡድኑ ላይ ጥናቶችን የሠሩ ተቋማት እንደሚሉት ከሆነ በከተማዋ የሚንቀሳቀሱ ሌሎች የወንጀል ቡድኖች የሚቆጣጠሯቸው ስፍራዎች እያነሱ ሲመጡ፣ የቀዩ ዕዝ አባላት ግን በከተማዋ የሚያስተዳድሯቸው አካባቢዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ጨምረዋል።
ከ2022 እና 2023 ይህ የወንጀለኛ ቡድን የሚቆጣጠረው አካባቢ በ8.4 በመቶ ጨምሯል፤ ከዚህም በተጨማሪም በታጣቂዎች ላይ ከዚህ ቀደም አጥቶት የነበረውን የበላይነት መልሶ ማግኘት ችሏል።
በዚህም የተነሳ በሪዮ ከተማ ታጣቂዎች በሚቆጣጠሯቸው አካባቢዎች ያለው ቁጥጥር ወደ 51.9 በመቶ አድጓል።
ቡድኑ ከምሥረታ እስከ ቀውስ
የሪዮ ዲ ጄኔሮ በአመጽ የተሞሉ ጊዜያት ከኮማንዶ ቬርሜልሆ ምሥረታ ጋር የተያያዘ እና 50 ዓመታት የሚቆጠር ታሪክ ያለው ነው።
በአውሮፓውያኑ 1970ዎቹ የፖለቲካ እስረኞች ከከተማዋ ከ100 ኪሎ ሜትር በላይ ርቆ በሚገኘው ካንዲዶ ሜንዴስ ማረሚያ ቤት ከኮማንዶ ወንጀለኛ እስረኞች ጋር ተቀላቅለው ይታሰሩ ነበር።
እስከዚያን ጊዜ ድረስ በባንክ ዘረፋ እና መሰል ተግባራት ላይ ተሰማርተው የሚያዙት ወንጀለኞች መደበኛ ትምህርት ያልተማሩ ወይንም ጥቂት ፊደል የቆጠሩ በመሆናቸው ስለ መብቶቻቸው ምንም የሚያውቁት ነገር የለም።
በአብዛኛው ከመካከለኛው መደብ ከመጡት የፖለቲካ እስረኞች ጋር ሲሆኑ በእስር ቤት ቆይታቸው ወቅት የተሻለ ሁኔታ ለማድረግ በድርድሮች ላይ መሳተፍ ጀመሩ።
"ኮማንዶ ቬርሜሎ የተወለደው በእስር ቤቶች ውስጥ በብሔራዊ ደኅንነት ሕግ መሠረት ከታሰሩ ሰዎች ጋር አብረው በሚኖሩ ሰዎች ነው። መጀመሪያ ላይ 'ፋላንግ ዳ ሴጉራንካ ናሲዮናል' ተብሎ ይጠራ ነበር። ከዚያም 'ፋላንጅ ቬርሜልሃ' ተብሎ መጠራት ጀመረ። ከዓመታት በኋላ ጋዜጦች 'ኮማንዶ ቬርሜሎ' ሲሉ አዲስ የዳቦ ስም አወጡለት" ስትል የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሙያዋ ካሮላይና ግሪሎ ታብራራለች።
በስፓኒሽኛ "ቬርሜሎ" ማለት "ቀይ" ማለት ነው።
"የግራ ክንፍ የፖለቲካ እስረኞችን ማደራጀታቸው ሳይሆን ሁለቱም የሚያመሳስላቸው ነገር የባንክ ዘረፋ ነው። እነዚህ ወንጀሎች እንደ ብሔራዊ ደኅንነት ስጋት ተደርገው ይቆጠሩ ነበር፤ ምክንያቱም አምባገነናዊ አገዛዝን የሚቃወሙ ቡድኖች የፖለቲካ ተቃውሞዎችን ለመደገፍ ባንኮችን ዘርፈዋል። ስለዚህ በሕግ ሂደቱ ወቅት በተለየ ዓይን ታይተዋል። በዚህም የተነሳ የተለመዱ የባንክ ዘራፊዎች ወዳሉበት ተወስደው ነበር" በማለት የሚያብራሩት ደግሞ በግጭት አስተዳደር ላይ ጥናት ከሚሠራ ተቋም የመጡት ጃክሊን ሙኒዝ ናቸው።
ከዋና መሥራቾቹ አንዱ ዊሊያም ዳ ሲልቫ ሊማ፣ ፕሮፌሰሩ የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቶታል።
ሊማ "የኮማንዶ ቬርሜሎ ታሪክ" በተሰኘው መጽሐፉ ውስጥ ቡድኑ በእስር ቤቱ ውስጥ ያለውን ሁኔታ መልክ ለማስያዝ በሚል አብሮ የመኖር ደንቦችን በማውጣት መጀመሩን ገልጿል።
በአውሮፓውያኑ 1979 የምህረት ሕግ ጸድቆ የፖለቲካ እስረኞች ሲፈቱ፣ ሌሎቹ ግን እዚያው እስር ቤት ቀርተዋል። በእስር ቤቱ ውስጥ ያለው ማኅበራዊ ፍትሕ ለማስፈን የሚደረገው ትግል ያለ ቀድሞ የእስር ቤት አጋሮቻቸው ድጋፍ ተቀዛቀዘ።
የቀይ ፋላንጅ አባላት በሌላ መንገድ ራሳቸውን አደራጁ። ይህም በ1980 ከ100 በላይ እስረኞች ከእስር ቤት ማስመለጥ አስችሏቸዋል። ይህም የባንክ ሠራተኞችን ተስፋ አስቆረጠ። ቀይ ኮማንድ በመባል የሚታወቁት ግለሰቦች ከባንክ ዝርፊያ ባገኙት ገንዘብ ወደ ሌላ ንግድ ተሰማሩ፤ ኮኬይን ወደ መሸጥ ገቡ።
በሕገ ወጥ ንግድ ላይ የተሰማሩት የኮማንዶ ቬርሜሎ አባላት ሸቀጦቻቸውን ከሌሎች ቡድኖች የስርቆት ሙከራ መጠበቅ ነበረባቸው።
"ዕጾቹ ስለተሰረቁ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሄደው ሪፖርት ማድረግ አይችሉም። በሕጋዊ መልኩ የተገኘ የግል ንብረት ቢዘረፍ ውል የተዋዋሉበት ወይም የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ንብረቱን ለማስመለስ ያገለግላል። የሕገ ወጥ ንግድ ግን ስምምነቶችን ለማስፈጸም እና ሕገ ወጥ ኢኮኖሚውን ለመቆጣጠር የጦር መሳሪያዎች ይጠይቃል" ይላሉ ሙኒዝ።
በወንጀል ቡድኖቹ መካከል "የውስጥ መከፋፈል፣ ፉክክር፣ የግዛት ይገባኛል አለመግባባቶች ነበሩ። በዚህ አለመግባባት ደግሞ ተጠቃሚ የሆኑት የጦር መሳሪያ ነጋዴዎች እና የጦር መሳሪያ ማቅረብ የጀመሩ የፖሊስ መኮንኖች ነበሩ።
ይህ በፖሊስ ውስጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመቋቋም ራሱን የበለጠ የማስታጠቅ ፍላጎት ፈጠረ ሲሉ ግሪሎ ጨምረው አስረድተዋል።
በ1990ዎቹ በጦር መሣሪያ የታገዙ ግጭቶች በሪዮ ዴ ጄኔሮ ታሪክ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሰው ነበር።
በ1994 ከ100 ሺህ ነዋሪዎች መካከል 64.8 ግድያዎች ይፈጸሙ ነበር። ይህንንም በተጨባጭ ለማየት አሁን በከተማዋ ያለው የግድያ መጠን 24.3 ነው።
ኮማንዶ ቬርሜሎን ለማዳከም መንግሥት መሪዎቹን ወደ ተለያዩ እስር ቤቶች ቢያዘዋውርም ውጤቱ የተገላቢጦሽ ነበር።
ኮማንዶ ቬርሜሎ ርዕዮተ ዓለሙን ለሌሎች እስረኞች በማስተማር የበለጠ ጥንካሬን አግኝቶ በመጨረሻም በሪዮ ዴ ጄኔሮ ዋና የወንጀል ቡድን ለመሆን በቃ።
በዘመናዊ ዓለም ውስጥ መስፋፋት
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኮማንዶ ቬርሜሎ በሪዮ ብቻ ተገድቦ መቀመጥ አቆመ።
"ኮማንዶ ቬርሜሎ የድሆች መንደሮች የሚቆጣጠሩ በርካታ ቡድኖች አሉት። አንዳቸውም ቢሆኑ ከቡድኑ ጋር ሽርክና ከመፍጠር ውጪ በራሳቸው አቅም ያላቸው አይደሉም። ኮማንዶ ቬርሜሎ በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲያድግ ያደረገው ያ ነው" ያለው ደግሞ ስለየወንጀል ቡድኖች መጽሐፍ የጻፈው ጋዜጠኛ ራፋኤል ሶሬስ ነው።
እንደ እርሱ ገለጻ፣ ባለፉት ስድስት ዓመታት ውስጥ ኮማንዶ ቬርሜሎ በ25 ግዛቶች ያለውን ቁጥጥር ሲያሳድግ ከዚህ በፊት ግን በ10 ግዛቶች ብቻ ይንቀሳቀስ ነበር።
ግሪሎ" በከተማዋ የነበረው የወንጀል ቡድን የተስፋፋው ፒሲሲ የተባለው ቡድን አዛዥ እና የኮማንዶ ቬርሜሎ አዛዥ ወደ ፌደራል ማረሚያ ቤቶች ሲዛወሩ ነው።
የፌደራል መንግሥቱ በተለያዩ የአገሪቱ ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ ቀንደኛ የወንጀል ቡድን መሪዎችን ወደ አንድ ስፍራ አምጥቶ ማሰሩን በጣም "ምርጥ ሃሳብ ነው ብሎ ነበር ያሰበው" በማለት የመንግሥት እርምጃ ይተቻሉ።
የኮማንዶ ቬርሜሎ መስፋፋት አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን ይፈልጋል። የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር የወንጀል ተግባሩ ማዕከል ሆኖ ቆይቷል። በተለይም እንደ አማዞን ያሉ የድንበር አካባቢዎችን በመቆጣጠር አንጃው እና ፒሲሲ የሚቆጣጠሯቸውን አካባቢዎች እያስፋፉ መጥተዋል።
ነገር ግን ትርፉ ከአደንዛዥ ዕጽ ብቻ የሚገኝ አይደለም። የብራዚል የሕዝብ ደኅንነት መድረክ ባደረገው ጥናት መሠረት የተደራጁ ወንጀሎች በ2022 ወደ 273.3 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ከወርቅ፣ ከነዳጅ፣ ከመጠጥ እና ከትንባሆ ሕገወጥ ግብይት አግኝተዋል።
የጦር መሣሪያ አቅርቦት መንገዱም ተለውጧል። እስከ ጥቂት ዓመታት ድረስ ሕገወጥ የአደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪዎች ራሳቸውን የሚያስታጠቁት በሁለት መንገድ ነበር። ከፓራጓይ ከሚገኝ ሕገወጥ ሽያጭ ወይም የጦር መሳሪያን ከአገሪቱ የፀጥታ ኃይሎች ወደራሳቸው በማዞር።
ዛሬ የራሳቸውን ዘመናዊ መሳሪያ መገጣጠም እና በስፋት ለማምረት የሚችሉ ሕገ ወጥ ኩባንያዎችን ይጠቀማሉ።
በነሐሴ ወር የፌደራል ፖሊስ በሪዮ ምዕራብ ዞን ሪዮ ዳስ ፔድራስ ውስጥ ድብቅ የጦር መሳሪያ መገጣጠሚያ ፋብሪካን አግኝቶ አራት ዘመናዊ የማምረቻ ማሽኖችን በቁጥጥር ሥር አውሏል።
በተደራጀ መልኩ የሚንቀሳቀሱት የወንጀል ቡድኖች እነዚህን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ብቻ አይደለም የሚጠቀሙት። ማክሰኞ ዕለት ቡድኑ ከፖሊስ ጋር ሲጋጭ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በመጠቀም ቦንቦችን በመጣል ያለውን አቅም አሳይቷል።
ሌላው በላንጌያኒ የሚያነሳው ሃሳብ እነዚህን መሳሪያዎች ለመገጣጠም የሚያስፈልጉ ቁሶች በቀላሉ መገኘታቸውን ነው።
በዣየር ቦልሶናሮ የፕሬዝዳንትነት ዘመን የነበረውን የመሳሪያ ቁጥጥር ለማላላት የሚያስችሉ ፖሊሲዎች በመውጣታቸው፣ የጦር መሳሪያ መገጣጠሚያ ፋብሪካዎች ተስፋፍተዋል።
የሚካሄዱ ዘመቻዎች ብቁ አለመሆን
መረጃዎች እንደሚያሳዩት መንግሥት ከፍተኛ ወጪ በማውጣት የሚወስዳቸው የኃይል እርምጃዎች የሚጠበቀውን ውጤት አላመጡም።
ኮማንዶ ቬርሜሎ በሪዮ ዲ ጄኔሮ የሚቆጣጠራቸውን አካባቢዎች እያሰፋሲመጣ ፖሊስ በበኩሉ ከፍተኛ እርምጃ እየወሰደ ግጭቶች እየተበራከቱ ነው።
የታጠቁ ቡድኖችን በሚያሳየው ካርታ መሠረት በአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎች ቁጥጥር ስር ባሉ አካባቢዎች የሚፈጠሩ ግጭቶች ሚሊሻዎች በሚቆጣጠራቸው አካባቢዎች ጋር ሲነጻጸር በ3.71 ከፍ ያለ ነው። ግጭቶች በሚፈጠርባቸው 60 በመቶ በሚሆኑት አካባቢዎች ደግሞ ፖሊስ ይሳተፋል።
የክሮስ ፋየር ኢንስቲትዩት የምርምር ዳይሬክተር ቴሪን ሁሴክ "መንግሥት ታጣቂዎችን ወይንም አደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪዎችን ለመበተን በሚወስደው እርምጃ መካከል ቀጥተኛ ግንኙነት አይታየኝም። በአንድ ወቅት በቁጥጥራቸው ሥር የገቡ አካባቢዎችንም ለቅቀው በመንግሥት ስር ሲሆንም አናይም" ብለዋል።
አክለውም "የተመለከትነው ትንሽ ተጨማሪ ቦታ ሲቆጣጠሩ ወይም እርስ በርሳቸው ሲጋጩ ነው፤ ነገር ግን መንግሥት 'ይህ አካባቢ ደኅንነቱ የተጠበቀ አልነበረም፣ አሁንም እንደዚያው ነው' ሊል አልቻለም። እየባሰበት ሲሄድ እና የዕዝ ለውጥ ሲኖር ብቻ ነው የምናየው፣ እና መንግሥት ለአስርት ዓመታት በወንጀለኛ ቡድኖች የበላይነቱ የተወሰደበትን ቦታ መልሶ መቆጣጠር አልቻለም።"