በደቡብ አፍሪካ 20 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ አደንዛዥ ዕጽ እና ማምረቻው ተያዘ

የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ ክሪስታል ሜታምፌታሚን የተሰኘ አደንዛዥ ዕጽ ማምረቻ ላብራቶሪ 20 ሚሊዮን ዶላር ከሚያወጣ ዕጽ ጋር በአገሪቱ ምስራቃዊ ክፍል በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ።

"የሰሜን አሜሪካ ዜጎች" ናቸው የተባሉ አምስት ሰዎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ሁለት ሌሎች "የምዕራብ አፍሪካ አገራት ዜጎች" ይሆናሉ የተባሉ ደግሞ መሸሻታቸውን ፖሊስ አስታውቋል።

ፖሊስ ከመግለጫው ጋር አያይዞ ይፋ ያደረገው ምስል የአደንዛዥ ዕጽ ማምረቻ የኢንዱስትሪ ቁሳቁሶች ከሚዛን እንዲሁም አደንዛዥ ዕጽ ከተሞላባቸው ሳህኖች ጋር ይታያሉ።

እአአ በ2022 ይፋ የሆነ ሪፖርት ደቡብ አፍሪካን በዓለም ላይ ካሉ ክሪስታል ሜትን የሚጠቀሙ በርካታ ሰዎች ካሉባቸው አገራት መካከል አንዷ ብሏታል።

የተባበሩት መንግሥታት በበኩሉ መልክዓ ምድሯ እና "የድንበር ጥበቃው ልል መሆኑ" ለሕገ ወጥ ዕፆች መተላላፊያነት ምቹ አድርጓታል ብሏል።

አርብ ዕለት ከጆሀንስበርግ ደቡብ ምዕራብ 225 ኪሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ቮክስረስት በሚገኝ የእርሻ ቦታ ባለ ፋብሪካ ላይ በተደረገ ፍተሻ ፖሊስ ጥይት የተሞላ ጠብመንጃ በቁጥጥር ስር አውሏል።

የፋብሪካው ተቆጣጣሪ ከሦስት ጥይት የተሞሉ ጠብመንጃዎች ጋር በቁጥጥር ስር ውሏል።

ፖሊስ ከነዋሪዎች " ከቅጥር ግቢው [ከእርሻ ቦታው አካባቢ] የሚመጣ ለየት ያለ የኬሚካል ሽታ መኖሩን እና ያልተፈቀደ ዕጽ ማማረቻ መሆኑ ላይ ጥርጣሬ ያጫረ" ጥቆማ ከደረሰው በኋላ ፍተሻ ማድረጉን ተናግሯል።

ኮሚሽነር ሜጀር ጄነራል ምክህዋናዚ "ከፖሊስ ጋር በትብብር መስራት እና መረጃ መስጠት የቀጠሉትን ማኅበረሰብ አባላት ማመስገን እንፈልጋለን። በመረጃ ላይ የተመሰረተ ዘመቻ ቀጣይነት ያለው ነው። እንዲሁም እኛ እንደ ፖሊስ ሕገወጥ አደንዛዥ ዕጽ ንግዱን ለማፈራረስ የምንችለውን ሁሉ ከማድረግ ወደ ኋላ አንልም" ብለዋል።

ባለፈው ዓመት በአገሪቱ ገጠራማ አካባቢ ሁለት የሜክሲኮ ዜግነት ያላቸው እና ሁለት ደቡብ አፍሪካውያን አደንዛዥ ዕጽ በማምረት ስራ ላይ ተሰማርተው በቁጥጥር ስር ውለዋል።