ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
“ወደ ኋላ የተመለስኩት ለትዝታችን፣ ወደፊት የሄድኩት ደግሞ ለብላቴናው ስንቅ ለመሆን ነው”- ወግዳይት
ወጣት ድምጻዊ ነው። ራሱን “ወግዳይት” ብሎ ይጠራል። በእርግጥ የመዝገብ ስሙ ሌላ ነው። በቅርቡ አሳላፊ ሲል የሰየመውን የሙዚቃ ሥራውን ለአድማጮቹ አቅርቧል።
ሙዚቃዬን የሠራሁት ለዛሬዎቹ ብላቴናዎች ነው የሚለው ወግዳይት፣ ወደኋለ እየተንደረደረ ወደፊት እየተመለከተ የሚጓዝ 14 የሙዚቃ ሥራውን አቅርቧል።
ቢቢሲ በሥራዎቹ ዙሪያ አጭር ቆይታ አድርጓል።
ቢቢሲ - ራስህን ወግዳይት ብለህ የምትጠራው ለምንድን ነው?
ወግዳይት - የሙዚቃ ሥራዎቼን እና ስብስቦቹን ወግ ነው የምላቸው። ሥራዎቼ ከእኔ የሕይወት ልምድ ጋር ለማዋሀድ የተፈጠሩ የጥበብ ግኝቶች ስለሆኑ ወግ እና ዳዊትን በማጣመር “ወግዳይት” ብየዋለሁ።
ቢቢሲ- ከዚህ በፊት በሙዚቃ ውስጥ ስምህን አልሰማንም ነበር።
ወግዳይት - በሙዚቃ እና በጥበብ ሥራዎች ውስጥ ከልጅነቴ ጀምሮ ነው ያለሁት። ከልጅነቴ ጀምሮ ግጥም እጽፍ ነበር። ዜማን እደርስ ነበር። ከዚያ እድሜዬ እየጨመረ ሲመጣ የምሠራቸውን ሥራዎች እንደ ቁምነገር መመልከት ስጀምር፣ ይህንን ነገር እንደ ቋሚ ሙያዬ አድርጌ መያዝ እንደምችል አሰብኩኝ።
ከዚያ በኋላ ነው ወደፊት የመጣሁት።...ስጀመር ዳያቶኒክ ነበር የምጫወተው። ከዚያ ወደራሴ ስመለስ፣ እንዴት ነው መጫወት ያለብኝ? ከእኔ ውስጥ ምን ይወጣል? ከአገሬ ሰው ጋርስ እንዴት አድርጌ ነው ልግባባ የምችለው? ብዬ ማሰብ ጀመርኩኝ።
በወቅቱ የመጣልኝ የማኅበረሰቤ ወግ ነው። ወግን ደግሞ ስናነሳ ባሕላዊ፣ መንፈሳዊ እና ታሪካዊ ወጎች አሉ። እነሱ እነሱን ከሕይወቴ ጋር ለማያያዝ ሞከርኩኝ።
ቢቢሲ - ሚዶ ሪከርድስን ከማግኘትህ በፊት ሌሎች ባንዶች ውስጥ ትሰራ ነበር?
ወግዳይት - ...ከሚዶ ሪከርድስ ጋር ከመገናኘታችን በፊት አምስት ዓመት ገደማ፣ ስቱዲዮ ውስጥ ከጀርባ ነበር የምሰራው።
ቢቢሲ- ስቱዲዮ ውስጥ ከጀርባ ነበርኩ ስትል፣ ዜማ እና ግጥም በመድረስ ነው ወይስ በማቀናበር?
ወግዳይት - ሙዚቃም እጫወታለሁ፣ አቀናብራለሁ፣ ብዙም የራሴን ነገር ይዤ እስክወጣ ድረስ መታየት አልፈልግም ነበር። ስቱዲዮ ውስጥ ግን ሥራዎቼን እሰራ።
ቢቢሲ- ለምን ነበር መታየት የማትፈልገው፣ አልችልም ብሎ መፍራት ነው ወይስ ጭምት መሆን?
ወግዳይት - ጭምት መሆን ሊባል ይችላል፤ ልክ ወግዳይት የሚለው የገባኝ ዕለት፣ ወጉን የተረዳሁት ዕለት፣ ይህ ነገር በየምሽት ጭፈራ ቤቶች ዝም ብሎ የሚሰማ አይደለም። ይህ ነገር ለአገር፣ ለአፍሪካ እንዲሁም ለዓለም የሚሆን ስለሆነ መቆጠቡ ይሻላል ብዬ ነው የዘገየሁት።
ቀድሞ አውጥቶ ነገሩን ከማሰናከል፣ ቢታሽ እና በደንብ ጊዜ ቢወሰድበት የሥራ አጋሮች ብፈልግ ከዚህ የተሻለ ይሆናል ብዬ ነው የዘገየሁት። ይህ የገባኝ ዕለት ነው የትም ቦታ መጫወት፣ የትም ቦታ መታየት ያቆምኩት። ስለዚህ የነበረኝን ጊዜ መቶ በመቶ ራሴ ላይ ኢንቨስት አደረግኩት።
ቢቢሲ - ሚዶ ሪከርድስ ከዚህ ቀደም ፕሮዲዩስ ያደረጋቸው ሙዚቃዎች ውስጥ ያስተዋልናቸውን ስታይሎች አንተ ሙዚቃዎችም ውስጥ እንሰማቸዋለን። አንተ ከሌሎቹ ሥራዎች ጋር መመሳሰል መኖሩ ተሰምቶሀል?
ወግዳይት - አዎ፣ ሚዶ ሪከርድስ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ በተመሳሳይ ቀለም ውስጥ የሚገኙ ድምጻውያንን በአንድ ዓላማ ይዞ የቀረበ ነው። ስለዚህ አርቲስቶቹ እርስ በእርስ በሙዚቃቸው ቀለም እና ይዘት በየራሳቸው አገላለጽ ቢለዩም ግን 'ሳውንድ' ላይ ተመሳሳይ የሆነ ይዘት ላይ የሚያተኩሩ ቢሆኑም ይመሳሰላሉ።
ቢቢሲ - በአንተም ሆነ በሌሎቹ የሚዶ ሪከርድስ አርቲስቶች ላይ ወደኋላ መመለስ አብዝቶ ይታያል። ለምንድን ነው አንተ ያንን የፈለግከው።
ወግዳይት - ...እኔ ብዙ ጊዜ ‘ኢን ሰርች ኦፍ ሩትስ’ የሚል መንገድ አለ እላለሁ። ማንነትህን መለስ ብለህ በፈለግክ ቁጥር ወደ ፊት ረዥም ርቀት የምትስፈነጠርበት ብዙ ነው የሚሆነው። ልክ ቀስትን ወደኋላ በለጠጥከው ቁጥር ወደፊት በርቀት ማስወንጨፍ እንደምትችለው ማለት ነው።
እኛ ላለንበት የእድሜ ክልልም ወደ ኋላ መለስ ብለን ከአባቶቻችን የወረስነውን መመለከት፣ እኛም ደግሞ ወደፊት ለልጆቻችን፣ ወደፊት ለሚመጣው ትውልድ ማስተላለፍ የምንፈልገውን ነገር ለማወቅ ይረዳናል።
ነገሩ የዘመን ቅብብል እንደሆነ የአንድ ዘመን ብቃይ ብቻ እንዳልሆነ፣ በዘመን ቅብብል ውስጥ የሚገኝ የፈጠራ ሥራ፣ በዘመን ቅብብል ውስጥ የሚገኝ የጥበብ መንገድ፣ ሥልጣኔ ሁሉ ነገር በቅብብል የሚመጣ ነው።
የተቀበልነውን ነገር ደግሞ አድምቀን፣ ኮራ ብለን፣ አምነንበት እኛም ለሚቀጥለው ትውልድ ማስተላለፍ እንችላለን። የሚመጣው ትውልድ ደግሞ እኛን የሚያከብረው የሚያመሰግነው በአግባቡ ስናስተላልፍለት ነው። ስለዚህ ቅብብል መልካም ነው።
ቢቢሲ - ሥራዎችህ ውስጥ የምናየው መመለስ፣ ወደ ልጅነት ወደ ጋራ ትዝታ መመለስ ይታይበታል። ለምንድን ነው ወደ ጋራ ትዝታ እና ወደ ልጅነት መመለስ የፈለግከው? ተወዳጅነት ለማግኘት ወይስ የተለየ ማስተላለፍ የፈገግከው ነገር ኖሮ?
ወግዳይት - ተወዳጅነት ለማግኘት ብቻ ሳይሆን ላስተላልፍ የፈለግኩት ነገር በመኖሩ ጭምር ነው። ላስተላልፍ የፈለግኩት ምንድን ነው? እኔ እንደ አንድ ወጣት በልጅነቴ የተሰሩብኝ በርካታ ነገሮች አሉ። ልጅ እያለሁ ያዳመጥኳቸው ያሬዳዊ ዜማዎች፣ የተጫወትኳቸው እንቆቅልሾችን ሳስታውስ የዛሬ ብላቴናስ ይህንን ዕድል ያገኝ ይሆን? ብዬ ወደ ታናናሾቼ ተመለከትኩኝ።
አሁን ካለው ጋር ሳስተያየው እኔ ያደግኩበት ከእኔ በፊት የነበሩትም ከኖሩበት አንጻር የአሁኑ ትውልድ ልምድ ትንሽ ራቅ ይላል። አሁን ያለው ትውልድ በዘመናዊው ዓለም አብዝቶ የመቃኘት ነገር አስተውላለሁ። ልጆች ሲያድጉ በፈረንጅ የልጆች ሙዚቃ ጨዋታ ነው። የሚማሩትም የፈረንጆቹን መማሪያ ነው።
እና እኔ ለዛሬው ልጅ፣ ለብላቴናው ስንቅ የማቀርብለት እንዴት ነው? ብዬ ሳስብ አዲስ ለሚመጣው ትውልድ የነበረንን ትውፊት ስለማውጋት ነው። ወጣቱን በትዝታ የመመለስ ዓላማ የላቸውም እነዚያ ሙዚቃዎች። ለአዲሱ ትውልድ ስለ ያሬድ ማውጋት እና እንቆቅልሽን ስለመንገር ናቸው። ስለዚህ ለብላቴናው ስንቅ ለእኛ ደግሞ ትዝታ ይሆነን ዘንድ ታስበው የተሰሩ ናቸው።
ልጆቻችን፣ እህት ወንድሞቻችን በዚያ ነገር እየቃኙ ስለማሳደግ፣ በልጅነታቸው ስለ ዝሙት ስለ እርኩሰት እንዳይሰሙ በሚደረገው ጥረት ውስጥ አስተዋጽኦ ለማድረግ ጭምር ነው።
ቢቢሲ - ስለዚህ ሥራዎችህን በአጠቃላይ ወደ ኋላም የመመለስ ወደፊትም የመስፈንጠር ናቸው ማለት እንችላለን?
ወግዳይት - በትክክል ወደ ኋላ የተመለስኩት ለትዝታችን ቅብብል ነው፤ ወደፊት ደግሞ የሄድኩት ለብላቴናው ስንቅ እንዲሆን ነው። በዚህም እኛ የደረስንበትን መረዳት እጅጉን አድምቆ እንዲረዳ እና አዲስ የሕይወት ቅኝት እንዲኖረው ማድረግ።
ቢቢሲ- “ፈልቀሽ የተገኘሽ ከሹበርት ትራስ፣ ከቤትሆቨን ናላ ከሞዛርት መንፈስ...” ይህን ግጥም ከጋሽ ከበደ ሚካኤል የወሰድከው ነው። የጋሽ ከበደን ግጥም መዝፈን የፈለግክበት ምክንያት ምንድን ነው?
ወግዳይት - ይህንን የጋሽ ከበደ ሚካኤልን ግጥም የሰማሁት አንድ የኪነጥበብ ምሽት ላይ ታድሜ በነበረበት ወቅት ነው። በውስጤ እኔ ስለሙዚቃ መጻፍ እፈልግ ነበር። እንዳልኩ እኔ ትኩረት አድርጌ የምሠራው የዛሬ ትውልድን በኢትዮጵያዊ ወግ መቃኘት ነው።
ስለዚህ ስለ ሙዚቃ ስለ አምባሰል፣ ስለ ባቲ፣ ስለ አንቺሆዬ፣ ስለትዝታ ልጽፍ ፈለግኩ እና እስቲ ከዚህ በፊት ስለሙዚቃ የተጻፈ ምን አለ? ስለኢትዮጵያ ሙዚቃ ምን ተጽፏል? ብዬ በማገላብጥበት ጊዜ ያንን ነገር አገኘሁኝ።
ስለዚህ ወግ ቅብብል በመሆኑ፣ ከበፊቱ ወስጄ እኔም የራሴን ጨምሬበት፣ ወደፊት ለሚመጣው ትውልድ ደግሞ ስንቅ ይሆናል ያልኩትን ዋና የወግ ስብስብ የሚመጥን የግጥም ሥራ ነው ያገኘሁት። ያንን ከአባቶቻችን የተቀበልኩትን እኔ ደግሞ ለቀጣዩ ትውልድ ብላቴናው ብዬ አስተላለፍኩት።
ቢቢሲ- በድምጽህ ውስጥ ባሕሩ ቀኜን፣ ያሬዳዊ ዜማን እንሰማለን። ከዚያ ደግሞ ከዘመኑ ሂፕ ሃፕ ጋር፣ ሬጋ ጋር ቀይጠህ እናደምጣለን።...ለመሆኑ በየዘመኑ ካሉ ሙዚቀኞች የእነማን አድናቂ ነህ?
ወግዳይት - በየዘመኑ በጣም ድንቅ የሚባሉ ሰዎች አሉ። ለአብነት ያክል አስናቀች ወርቁን እወዳለሁ፣ ሙሉቀን መለሰን፣ ቴዎድሮስ ታደሰን፣ ባሕሩ ቀኜን፣ ተሾመ ምትኩን...በርካታ ኢትዮጵያውያን ሙዚቀኞችን እወዳለሁ።
ቢቢሲ - የሙዚቃ ሥራዎችህ ውስጥ ሞቅ ያለ ሙዚቃ ብዙ አይሰማም። ሞቅ ያለ ሙዚቃዎችን በሥራዎችህ ማካተት ያልፈለግክበት ምክንያት አለ?
ወግዳይት - እንደ ደራሲ እንደ ፀሐፊ ምን ያስፈልጋል? ብለህ እንጂ አድምጭ ምን ይፈልጋል? ብለህ አትሰራም። እኔም ውስጥ የተሰማኝ በዚህ ሰዓት መስተዋድድ [የሚያዋድድ ነገር] ነው፤ ፍቅር ነው።
በዚህ ሰዓት ያስፈለገኝ ነገር ወግ ነው። በዚህ ሰዓት ለሰው ልጅ የሚያስፈልገው እርጋታ ነው ብዬ ስላሰብኩኝ ረጋ ባሉ የድምጽ ቅኝቶች ላይ ለመጫወት ሞክሬያለሁ።
ምናልባት ደግሞ የሕይወት አጋጣሚ መጫወት እና መዝናናትን ከጋበዘን አሼሼ እንላለን። (ሳቅ)
ቢቢሲ- ወደፊት አሁን ለአድናቂዎችህ ይዘህ ከመጣኸው የተለየ የስታይል ለውጥ አደርጋለሁ ብለህ ታስባለህ ማለት ነው?
ወግዳይት - በትክክል። ቀጣይ ፕሮጀክት አለኝ። ቀጣዩ ፕሮጀክት አሁን ካሉት የሙዚቃ ስብስቦች ይዘት ለየት ያለ እና ወጣ ያለ ነገር ነው። እርሱም የራሱን ዓላማ እና ቀለም ይዞ የሚመጣ ስብስብ ነው። ስለዚህ በትክክል ይቀየራል።