እግር ኳስ ተጫዋቾች ድዳቸው ሥር የሚቀብሩት ጥቅል ምንድነው? ሕጋዊስ ነው?

በቅርቡ የተሠራ አንድ ጥናት እንደሚጠቁመው ከአምስት ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋቾች አንዱ ስኑስ የተባለውን ኒኮቲን [በሲጋራ ውስጥ ያለ] ንጥረ-ነገር ይጠቀማል።

በጥናቱ ከተካፈተቱ ተጫዋቾች መካከል ግማሹ ይህን አመል መተው እንደሚፈልጉ ይናገራሉ።

ሎፍቦሮ ዩኒቨርሲቲ ከፕሮፌሽናል ተጫዋቾች ማኅበር ጋር በመተባበር የሠራው ጥናት፣ ከአምስት ተጫዋቾች መካከል ሁለቱ ቢያንስ አንድ ጊዜ ይህን ንጥረ-ነገር እንደሞከሩት ያሳያል።

ዘገባው እንደሚጠቁመው ስኑስ የሚጠቀሙ ተጫዋቾች “ትክክለኛ ቁጥር” ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችል ሲሆን፣ በርካታ ተጫዋቾች ስማቸው ባይጠቀስ እንኳ የመጠቀም ሱስ እንዳለባቸው መናገር አይሹም።

በቅርቡ ይፋ የተደረገው ጥናት ስኑስ አጠቃቀምን በተመለከተ የተሠራ የመጀመሪያውና ትልቁ ጥናት ነው።

628 በእንግሊዝ ፕሪሚርዬር ሊግ እና በኢኤፍኤል ክለቦች የሚጫወቱ ወንድ ተጫዋቾች በጥናቱ የተካተቱ ሲሆን፣ 51 የሴቶች ሱፐር ሊግ ተጫዋቾችም ተሳትፈዋል።

ከወንዶቹ ተጫዋቾች መካከል 18 በመቶው አሁንም ስኑስ እንደሚጠቀሙ የተናገሩ ሲሆን፣ 42 በመቶው ደግሞ ቢያንስ አንድ ጊዜ እንደሞከሩት አምነዋል።

ከሴቶቹ መካከል ደግሞ 22 በመቶው አሁንም እንደሚጠቀሙ ሲናገሩ፣ 39 በመቶው ሞክረውት እንደሚያውቁ ገልጸዋል።

ከወንዶቹ ተጫዋቾች መካከል 48 በመቶው በሚቀጥለው ዓመት ይህን ድድ ውስጥ የሚቀበር ማስቲካ ለማቆም እንደሚፈልጉ አሳውቀዋል። ከሴቶቹ መካከል ደግሞ 9 በመቶው ናቸው የማቆም ፍላጎት ያላቸው።

የ16 ፕሮፌሽናል ክለቦች አቋም የተጠና ሲሆን የጤና ክፍል ሠራተኞችም ቃለ-መጠይቅ ተደርጎላቸዋል።

ስኑስ ምንድነው?

ስኑስ የትምባሆ ምርት ሲሆን ልክ እንደባለገመዱ ሻይ ቅጠል ታሽጎ የሚመጣ ነው። ከከንፈር ሥር የሚቀበረው ይህ ማስቲካ ኒኮቲን ወደ ደም ባንቧ ይለቃል።

ስኑስ ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ገበያ ላይ እንዲውል ባይፈቀድለትም መጠቀም ግን በሕግ አያስቀጣም። ነገር ግን ትምባሆነት የሌላቸው ንጥረ-ነገሮች ግን ሕጋዊ ናቸው።

አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች ትምባሆ ያለውን ስኑስ ከመጠቀም ይልቅ ኒኮቲን አዘል ጥቅል መጠቀም ይመርጣሉ። ነገር ግን ኒኮቲን አዘል ጥቅሎችንም ስኑስ እያሉ ነው የሚጠሯቸው።

እግር ኳሰኞች ለምን ስኑስ ይጠቀማሉ?

ስኑስ ተጠቅመው አቋማቸው ከጨመረ 45 ወንድ ተጫዋቾች መካከል 29 በመቶው፤ ከ11 ሴት ተጫዋቾች መካከል ደግሞ 55 በመቶው የአእምሮ ጤናቸው እና ዝግጁነታቸው እንደተሻሻለ ይናገራሉ።

ከ84 ወንዶች መካከል 56 በመቶው ይህ ጥቅል የአእምሮ መረጋጋት እንደሚሰጣቸው ሲናገሩ ከ11 ሴቶች መከካል 36 በመቶው ተመሳሳይ ምላሽ ሰጥተዋል።

ተጫዋቾች አብዛኛውን ጊዜ ስኑስ የሚጠቀሙት ከልምምድ እና ከጨዋታ በኋላ ነው። የክለቦች የጤና ባለሙያዎች ተጫዋቾቹ ስኑስ የሚጠቀሙት እንደ “ጭንቀት ማቅለያ” መንገድ ነው ይላሉ።

ጥናቱ እንደጠቆመው ተጫዋቾች አንዳንድ ጊዜ ይህን ጥቅል የሚቀጠሙት የምግብ ፍላጎታቸውን ለመግታት ሲሆን፣ አዳዲስ ጀማሪዎች ደግሞ ልምድ ካላቸው ተጫዋቾች ጋር ለመመሳሰል በሚል ይህን ጥቅል ይወስዳሉ።

ከወንድ ተጫዋቾች መካከል 56 በመቶው ስኑስ መጠቀም የጀመሩት ልምድ ካላቸው ጋር ለመሳሰል ነው ሲሉ 73 በመቶው ሴቶችም ተመሳሳይ ምላሽ ይሰጣሉ።

አሉታዊ ጎኑ ምንድነው?

ይህ ንጥረ ነገር በጤና ላይ የራሱ ተጽእኖ እንዳለው የሚያሳዩ ማስረጃዎች አሉ። በተጨማሪም ለልብ ህመም ሊያጋልጥ እንደሚችል ጥናቶች ይጠቁማሉ።

ሌሎች ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ደግሞ ስኑስ መጠቀም አፍ አካባቢው ቁስለት እና የትንፋሽ መለዋወጥ ሊያመጣ ይችላል።

በአውሮፓውያኑ መጋቢት 2023 የፕሮፌሽናል ተጫዋቾች ማኅበር ባወጣው መግለጫ፣ ስኑስ የሚጠቀሙ ተጫዋቾች ቁጥር እየጨመረ የመጣ መሆኑ እንዳሳሰበው ገልጦ፤ አንዳንድ ተጫዋቾች ሱስ ውስጥ በመግባታቸው እርዳታ እያገኙ እንደሆኑ ጠቅሷል።

በጥናቱ ከተካተቱ ተጫዋቾች መካከል 53 በመቶ ወንዶች እና 86 በመቶ ሴቶች የኒኮቲን ጥገኝት እንዳለባቸው ይናገራሉ። ማለትም ሳይስቡት ስኑስ ማሰኘት፣ ሲያቆሙት ደግሞ ጭንቀት፣ ምቾት ማጣት እና እረፍት አልባ መሆን ይታይባቸዋል።

ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት ወንዶች ስኑስ የሚያገኙት ከሱቅ እንደሆነ ጠቁመዋል። ከግማሽ በላይ የሚሆኑ ሴቶች ደግሞ ከበይነ-መረብ ላይ እንደሚገዙት ይናገራሉ።

ጥናቱ ምናልባት ይህ ምርት ከአበረታች መድኃኒቶች ጋር ከተደባለቀ ለተጫዋቾች አደጋ ሊያመጣ እንደሚችል ይገልጣል።

አክሎ ክለቦች ይህ ጥቅል ጥቅም ላይ እንዳይውል ያወጡት ክልከላ ብዙም ውጤታማ አይደለም። ስለዚህ በግለሰብ ደረጃ ድጋፍ ማድረግ እና ማቆም የሚፈልጉ ተጫዋቾችን አለማግለልን ይመክራል።