አሜሪካ ከቻይና ጋር ወደ አዲስ ቀዝቃዛ ጦርነት ላለመግባት ቃል ገባች

የፎቶው ባለመብት, AFP
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከቻይናው አቻቸው ፕሬዘዳንት ዢ ጂንፒንግ ጋር ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ ከቻይና ጋር ''አዲስ የቀዝቃዛ ጦርነት'' እንደማይኖር ቃል ገቡ።
ፕሬዘዳንቱ አክለውም ቻይና ታይዋንን ትወራለች የሚል እምነት እንደሌላቸው ተናግረዋል።
ባይደን ዋይት ሃውስ ከገቡ በኋላ በሁለቱ ልዕለ ኃያላን መሪዎች መካከል የመጀመሪያው የፊት ለፊት ውይይት ነው ይህ በኢንዶኔዢያዋ ደሴት ባሊ የተደረገው ውይይት።
የሰሜን ኮሪያን ብሎም ሩሲያ ዩክሬንን የመውረር ጉዳዮችን በባሊ ደሴት ከሚካሄደው የቡድን 20 ስብሰባ ከመጀመሩ አንድ ቀን ቀደም ብለው መሪዎቹ ከተወያዩባቸው አጀንዳዎች መካከል ናቸው።
አገራቱ በዩክሬን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ መዋልን እንደሚቃወሙም ገልጸዋል።
ወዳጃቸውን ቭላድሚር ፑቲንን እንዲያግባቡ በባይደን የተጠየቁት ዢ ጂንፒንግ አገራቸው ለሰላም ያላትን ቁርጠኝነት የገለጹ ቢሆንም "ለተወሳሰበ ችግር ቀላል መፍትሄ የለም" ሲሉ አሳስበዋል።
ፕሬዘዳንት ባይደን ውይይቱን ተከትሎ በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ “ቻይና ሰሜን ኮሪያን በእርግጠኝነት ትቆጣጠራለች ማለት ከባድ ነው” ብለዋል።
ነገር ግን ቻይና ፒዮንግያንግ በሌላ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ሙከራ እንዳትሳተፍ የማሳመን "ግዴታ" አለባት ሲሉ ለሚስተር ዢ ነግረዋቸዋል።
የቻይናው ፕሬዘዳንት ወደ ባሊ ከገቡ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በአንድ ቅንጡ ሆቴል በተደረገው እና ለ 3 ሰዓታት በቆየው በዚሁ ውይይት የታይዋን ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረትን አግኝቷል።
ባለፉት ሳምንታት የአሜሪካ ባለስልጣናት ቻይና ታይዋንን ለመውረር እቅዷን ልታሰፋ እንደምትችል ሲያስጠነቅቁ ነበር።
ይህንን ተከትሎም ጋዜጠኞች ባይደን ይህ ይሆናል ብለው ያምኑ እንደሆነ ብሎም አዲስ የቀዝቃዛ ጦርነት እየፈነዳ ነው ብለው ያምኑ እንደሆነ ጥያቄ አቅርበውላቸዋል።
"አዲስ የቀዝቃዛ ጦርነት እንደማያስፈልግ ሙሉ በሙሉ አምናለሁ። ከዢ ጂንፒንግ ጋር ብዙ ጊዜ ተገናኝተን ተወያይተናል። በዚህም ሙሉ በሙሉ ተስማምተናል።" አክለውም
"ቻይና ታይዋንን ለመውረር ማሰቧን የሚያሳይ ተጨባጭ እና አሳሳቢ ሙከራ አላት ብዬም አላምንም'' ሲሉ ተናግረዋል።
"ቻይና ከታይዋን ጋር ያላት ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ መፈታት እንዳለበት እና ወደ እንደዛ ያሉ አማራጮች መሄድ የለብንም። የተናገርኩትን ሁሉ እንደተረዱኝ እርግጠኛ ነኝ እኔም እርሳቸው የተናገሩትን ተረድቻለሁ" ሲሉ ባይደን ተናግረዋል።
የቻይናው ፕሬዘዳንት በበኩላቸው አሜሪካ በታይዋን ጉዳይ ''ቃሏ እና ተግበሯን አብራ እንድታስኬድ'' ጠይቀዋል።












