ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአርጀንቲናው ፕሬዝዳንት ሀገራቸው ከዓለም ጤና ድርጅት አባልነት እንድትወጣ አዘዙ
በፕሬዝዳንት ሃቪየር ሚሌይ የሚመራው የአርጀንቲና መንግሥት ሀገሪቱን ከዓለም የጤና ድርጅት አባልነት ለማስወጣት ማቀዱን አስታወቀ።
የአርጀንቲና የዓለም የጤና ድርጅትት ለቅቆ የመውጣት ዕቅድ የመጣው "በተለይም በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት በታዩ ጥልቅ የጤና አስተዳደር ልዩነቶች" ምክንያት እንደሆነ የፕሬዝዳንት ሚሌይ ቃል አቃባይ ማኑኤል አዶርኒ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ ሃቪየር ሚሌይ የአርጀንቲናን ከዓለም የጤና ድርጅት የመልቀቅ ሂደት ለማስጀመር በመጪዎቹ ቀናት ትዕዛዝ ይፈርማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የሀገሪቱ መገናኛ ብዙላን ተዘግቧል።
ይህ የፕሬዝዳንቱ ውሳኔ ይፋ የተደረገው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሀገራቸው ከዓለም አቀፉ የጤና ተቋም እንድትወጣ የሚያደርግ ሂደት የሚያስጀምር ትዕዛዝ ከፈረሙ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ነው።
ሁለቱ መሪዎች ከዚህ ቀደም አንዳቸው ለሌላኛቸው ያላቸውን አድንቆት ገልጸው ነበር። ፕሬዝዳንት ሚሌይ የትራምፕን በድጋሚ መመረጥ "በታሪክ ትልቁ ፖለቲካዊ መመለስ" ሲሉ ገልጸው የነበረ ሲሆን፣ ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ ሚሌይን "የእኔ ተወዳጅ ፕሬዝዳንት" ሲሉ ጠርተዋቸዋል።
የአርጀንቲናው ፕሬዝዳንት ሚሌይ ሀገራቸው ከዓለም የጤና ድርጅት እንድትወጣ ሲወስኑ በምክንያትነት የጠቀሱት ጉዳይ በአሜሪካም የተነሳ ነው። ሁለቱም ሀገራት ተቋሙ ለኮቪድ 19 ወረርሽኝ የሰጠውን ምላሽ እና ቻይና በዓለም አቀፉ የጤና ተቋም ላይ ያላትን ተፅዕኖ ጠቅሰዋል።
ከዚህ ውሳኔ ጋር በተያያዘ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ልዩነት ከአባልነት መልቀቃቸው በዓለም የጤና ድርጅት ላይ የሚያስከትለው ተፅዕኖ ነው።
አሜሪካ በብቸኝነት ለተቋሙ መዋጮ ከሚያደርጉ ሀገራት መካከል ከፍተኛ ገንዘብ በመስጠት ቀዳሚዋ ናት። አሜሪካ ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት 950 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ያዋጣች ሲሆን፣ ይህ ከተቋሙ አጠቃላይ በጀት 15 በመቶ የሚጠጋውን ይሸፍናል። የአሜሪካ ከአባልነት መልቀቅ በተቋሙ ላይ በተወሰነ መልኩ አስቸጋሪ የፋይናንስ ጥያቄዎችን ይፈጥራል።
አርጀንቲና በበኩሏ በዓመት 8 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ታዋጣለች። ይህ የገንዘብ መጠን በተቋሙ ላይ እምብዛም ልዩነት አይፈጥርም።
የአርጀንቲናው ፕሬዝዳንት አቃባይ ማኑኤል አዶርኒ፤ "እኛ አርጀንቲናውያን ዓለም አቀፍ ተቋም እንኳ ጤናችን ሉዐላዊነታችን ላይ ጣልቃ እንዲገባ አንፈቅድም" ሲሉ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።
ቃል አቀባዩ፤ ከዓለም የጤና ድርጅት አባልነት መውጣት አርጀንቲና ከፍላጎቶቿ ጋር የተጣጣሙ ፖሊሲዎችን እንድትተገብር እና ገንዘቧን ባመቻት መልኩ እንድታስተዳድር እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንት ሚሌይ ከሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ወይም ስምምነቶችም የመውጣት ዕቅድ ይኖራቸው እንደሆነ በጋዜጠኞች የተጠየቁት ቃል አቀባዩ፤ ግልፅ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
"ፕሬዝዳንቱ አርጀንቲናን ይበልጥ ነጻ ለማድረግ ቆርጠኛ ናቸው። እናም አርጀንቲና ከነጻነቷ ተቃራኒ ከሆኑ ማንኛውም አካላት ጋር ባላት ግንኙት፤ በአርጀንቲናውያን ሕይወት ውስጥ ጣልቃ እንዳይገቡ ለመከላከል የተቻለንን በሙሉ እናደርጋለን" ብለዋል።
አርጀንቲና ውስጥ የሚገኙ የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች ፕሬዝዳንት ሚሌይ፤ የትራምፕን ፈለግ ተከትለው ከፓሪስ የአየር ንብረት ስምምነት ይወጣሉ የሚል ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።