የትምህርት ማስረጃቸውን ያጭበረበሩት የናይጄሪያ ሚኒስትር ሥራቸውን ለቀቁ

የፎቶው ባለመብት, Nigeria Ministry of Science,Technology and Innovation/ Facebook
የናይጄሪያ የፈጠራ፣ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ኡቼ ናጂ የትምህርት ማስረጃቸውን በፎርጂድ አሠርተዋል የሚል ክስ ከቀረበባቸው ከቀናት በኋላ ሥራቸውን ለቅቀዋል።
ሚኒስትሩ ሥራቸውን የለቀቁት አንድ ጋዜጣ ባደረገው ምርመራ በ2023 ለሹመት ሲቀርቡ ለፕሬዝዳንት ቦላ ቲኑቡ ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ማቅረባቸውን ካጋለጠ በኋላ ነው።
የፕሬዝዳንቱ ቃል አቀባይ ባዮ ኦናንግዋ ማክሰኞ ዕለት የሚኒስትሩን መልቀቅ በኤክስ ገፃቸው ላይ ያረጋገጡ ሲሆን፤ ሚኒስትሩ "የፖለቲካ ተቀናቃኛቸው የስም ማጥፋት ዒላማ" መደረጋቸውን በመጥቀስ ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ የቀረበባቸውን የማጭበርበር ክስ ሐሰት መሆኑን የተናገሩ ሲሆን፤ ከናይጄሪያ ዩኒቨርስቲ በማይክሮባዮሎጂ/ባዮኬሚስትሪ መመረቃቸውን በተደጋጋሚ አስታውቀዋል።
ፕሪሚየም ታይምስ በተባለው ጋዜጣ ለሁለት ዓመታት የተደረገው የምርመራ ዘገባ መውጣቱን ተከትሎ ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ክሱ በናይጀሪያ ሕዝባዊ ቁጣ ቀስቅሷል።
ባለፈው ሳምንት ዩኒቨርስቲው በ1985 ሚኒስትሩ ተመረቅኩ ባሉት በባችለር ኦፍ ሳይንስ ለመመረቃቸው ማህደር የለንም ብሏል።
የዩኒቨርስቲው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ ለጋዜጣው ናጂ በ1981 በዩኒቨርስቲው መመዝገባቸውን፤ ነገር ግን ትምህርታቸውን እንዳላጠናቀቁ እና ይህንንም የሚያረጋግጥ ድግሪ አለመውሰዳቸውን ተናግረዋል።
የአገሪቱ ብሔራዊ የወጣቶች አገልግሎት በበኩሉ ሚኒስትሩ በ2023 ያቀረቡትን አስገዳጅ የትምህርት ማስረጃን ማረጋገጥ እንዳልቻለ ገልጿል።
የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የሆኑት አቲኩ አቡበከር በጉዳዩ ላይ ገለልተኛ እና ግልፅ ምርመራ እንዲደረግ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፤ ሚኒስትሩ ለፈፀሙት ማጭበርበር ከሥራቸው መባረር እና ለሕግ መቅረብ አለባቸው ብለዋል።
"ናይጄሪያዊያን ሕይወታቸው እና ሀብታቸው ስለሚመሩ ሰዎች እውነቱን ማወቅ ይገባቸዋል" ሲሉ አክለዋል።
በናይጄሪያ ሚንስትሮች ከሥራ መታገድ ወይም መባረራ ያልተለመደ ሲሆን፤ ናጂ ፕሬዝዳንት ቲኑቡ በ2023 ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ኃላፊነታቸውን የለቀቁ ሁለተኛው ሚኒስትር ናቸው።
ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ የሰብዓዊ ጉዳዮች እና የድህነት ቅነሳ ሚኒስትር የነበሩት ቤታ ኢዱ በሙስና ቅሌት ምክንያት ሕዝባዊ ቁጣ በመቀስቀሱ ከሥራ ታግደዋል። የ37 ዓመቱ ሚኒስትር የቀረበባቸውን የሙስና ክስ አስተባብለዋል።
የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ቡሃሪ በስምንት ዓመት የሥልጣን ቆይታቸው ሁለት ሚኒስትሮችን ብቻ ከሥራ አባርረዋል።















