ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት የሚያስችላትን ስምምነት ከሶማሊላንድ ጋር ተፈራረመች

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሊላንዱ ፕሬዝዳንት ሙሴ ባሂ

የፎቶው ባለመብት, EBC

የምስሉ መግለጫ, የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሊላንዱ ፕሬዝዳንት ሙሴ ባሂ

ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ኢትዮጵያን የባሕር በር ለማግኘት የሚያስችላትን የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

የመግባቢያ ሰነዱን የተፈራረሙት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሊላንዱ ፕሬዝዳንት ሙሴ ባሂ ናቸው።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ስምምነቱን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ፤ “የመግባቢያ ሰነዱ ኢትዮጵያ የባሕር በርን በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠቀም ያላትን ፍላጎት ዕውን ለማድረግ መንገዱን ይጠርጋል” ብሏል።

መግለጫው አክሎም ስምምነቱ የሁለቱን መንግሥታት የጸጥታ፣ ኢኮኖሚ፣ እና የፖለቲካ አጋርነት እንደሚያጠናክር አትቷል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አቶ ሬድዋን ሁሴን ኢትዮጵያ “በቀይ ባሕር ላይ በሊዝ ወታደራዊ ካምፕ ለማግኘት መንገድ የሚከፍት የትብብር ስምነነት” መፈራሟን በኤክስ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

ኢትዮጵያ በስምምነቱ መሠረት ወታደራዊ የጦር ሰፈር እንደምትገነባ ብሔራዊው የቴሌቪዥን ጣቢያ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዘግቧል።

ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ "በሊዝ የምታገኘው የባሕር በር" ለ50 ዓመታት እንደሚቆይ በብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያው ዘገባ ላይ ተጠቅሷል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መግለጫ የመግባቢያ ሰነዱን “አዲስ የትብብር ምዕራፍ የሚያመጣ” እና “[በአፍሪካ] ቀንድ ውስጥ ለክልላዊ ውህደት ትልቅ ጠቀሜታ አለው” ሲል አሞካሽቶታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኤክስ ገጻቸው ላይ ስለ ስምምነቱ ዝርዝር ባይገልጹም “ፈጣሪ ይመስገን እንጂ ሌላ ምን ሊባል ይችላል!” የሚል ጽሑፍ አስፍረዋል።

የ X ይዘትን ይለፉት
ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

የ X ይዘት መጨረሻ

ሶማሊላንድ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሌሎችም አገራት ይፋዊ ዕውቅና ያልተሰጣት ራስ ገዝ አገር ስትሆን፣ በኢትዮጵያ እና በሶማሊላንድ መካከል የተፈረመው ስምምነት ውስጥ ስለ ሶማሊያ ዕውቅና የተጠቀሰ ነገር የለም።

ሶላሚላንድ እአአ በ1991 ከሶማሊያ ከተገነጠለች ወዲህ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ለማግኘት እየተጣጣረች ትገኛለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከወራት በፊት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትን ሰብስበው ለኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት “የሕልውና ጉዳይ ነው” ካሉ በኋላ ስለ ጉዳዩ ከተለያዩ አቅጣጫዎች አስተያየቶች ሲሰነዘሩ መቆየታቸው አይዘነጋም።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ባዳረጉት እና ጥቅምት 02/2016 ዓ.ም. በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በተላለፈ 45 ደቂቃን የፈጀ ገለጻቸው “እምብዛም የማይደፈር” ባሉት የቀይ ባሕር ጉዳይ ላይ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለፈው ኅዳር 04/2016 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ የባሕር በርን በተመለከተ “ማንንም የመውረር ፍላጎት የለንም” ካሉ በኋላ “በቢዝነስ ሕግ ግን የማያወላዳ ምርጫ እንፈልጋለን” ማለታቸው ይታወሳል።

ጨምረውም የኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎት “በንግግርና በቢዝነስ ካልተፈታ ምን እንደሚያጋጥም መገመት አይችልም። ግን ኢትዮጵያ ወደ ኤርትራ፣ ወደ ጅቡቲ፣ ወደ ሶማሊያ፣ ወደ ኬንያ ወይም ወደ ሌላ ጎረቤቶቿ አንድ ጥይት የመተኮስ ፍላጎት የላትም። በሉአላዊነታቸው ላይም ጥያቄ የላትም” ማለታቸው አይዘነጋም።

የኢትዮጵያና የሶማሊላንድ ካርታ

የጠቅላይ ሚኒስሩ ንግግር የውይይት አጀንዳ ሆኖ ቆይቷል። በአካቢው አገራት ላይም ውጥረት የነገሰ ሲሆን ኤርትራ፣ ሶማሊያና ጅቡቲ ይህንን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ፍላጎት ውደቅ አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ንግግር አቋማቸውን በማስረገጥ "ኢትዮጵያ ወደብ የማታገኝ ከሆነ ጥፋት ሊከተል ይችላል" ሲሉ ተደምጠዋል።

ይህንን ንግግር ካደረጉ ከአንድ ወር ከ15 ቀናት በኋላ ነው ሶማሊላንድና ኢትዮጵያ ወደብን ጨምሮ “የአጋርነትና ትብብር ስምምነት” መፈራረማቸው የተሰማው።

በአፍሪካ ትልቅ ከሆኑ አገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ የባሕር በር የሌላት አገር የሆነችው ከ30 ዓመት በፊት ኤርትራ ነጻነቷን ማወጇን ተከትሎ ነው።

ከዚያ ጊዜ ጀምሮ አገሪቱ ለገቢ እና ለወጪ ንግድ የጂቡቲን ወደብን በመጠቀም ላይ ትገኛለች።