“ኢትዮጵያ በኤርትራም ሆነ ጅቡቲ ላይ ጥይት የመተኮስ ፍላጎት የላትም ” ጠ/ሚ ዐቢይ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

የፎቶው ባለመብት, Office of the Prime Minister-Ethiopia

ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት በጎረቤቶቿ ላይ ወረራ የመፈጸም ፍላጎት እንደሌላት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ኅዳር 04/2016 ዓ.ም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ የባህር በርን በተመለከተ “ማንንም የመውረር ፍላጎት የለንም” ካሉ በኋላ “በቢዝነስ ህግ ግን የማያወላዳ ምርጫ እንፈልጋለን” ሲሉ ተናግረዋል።

ጨምረውም የኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎት “በንግግርና በቢዝነስ ካልተፈታ ምን እንደሚያጋጥም መገመት አይችልም። ግን ኢትዮጵያ ወደ ኤርትራ፣ ወደ ጅቡቲ፣ ወደ ሶማሊያ፣ ወደ ኬንያ ወይም ወደ ሌላ ጎረቤቶቿ አንድ ጥይት የመተኮስ ፍላጎት የላትም። በሉአላዊነታቸው ላይም ጥያቄ የላትም” ሲሉ ተናግረዋል።

ፋላጎቷን ለማሳካት ግን የኢትዮጵያ አየር መንገድን እና ህዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎች አማራጮችን በጋራ ለመጠቀም ዝግጁ መሆኗን አንስተዋል።

“አየር መንገድን እንጋራ ማለት እንዴት ጦርነት ሊሆን ይችላል?” ሲሉም ጠይቀዋል።

“ማንንም አንወርም፣ የመውረር ፍላጎት የለንም። ረሃቡ ሳይመጣ፣ ችግሩ ሳይመጣ ተወያይተን መፍትሄ እናበጅ ነው ያልነው። ችግሩ ከመጣስ ህግ አይሰራም ያኔ። እኛ ምግብ ማስገባት ቸግሮን ከራበን የሚይዘን ህግ አይኖርም። ያገኘነውን በልተን ህልውናችንን እናስቀጥላለን” ሲሉ ተናግረዋል።

ይህ ጥያቄ እንዲመለስ የዓለም መንግስታትም ሊያግዙ ይገባል ካሉ በኋላ በዚህ ጉዳይ መወያየት የሚፈልጉ ጎረቤት ሀገራትን በማንኛውም ጊዜና ቦታ ለማነጋገር የመንግሥታቸውን ዝግጁነት ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን የገነባችው የሱዳንን ሉአላዊነት ‘ለመዳፈር አይደለም’ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀይ ባህርም በዚህ መልኩ ሊታሰብ ይገባዋል ብለዋል።

ከ 30 ዓመት በፊት የ 2 ወደብ ባለቤት እንደነበረች ያስታወሱት ዐቢይ አሁን በአንድ ወደብ ላይ መመርኮዟ የህዝብ ቁጥሯ ሲጨምር ለሌሎች ኃገራትም ከፍተኛ ስጋት ይሆናል ብለዋል።

የወደብ ጉዳይ “ሁሌ ያስጨንቀኛል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ይኼ እኮ 120 ሚሊዮን ህዝብ ነው። ከቸገረው፣ ከራበው አይሞት መቼም። ይሞክራል ” ሲሉ ተግረዋል።

ከጅቡቲ ህዝብና መንግሥት [ወደብን በተመለከተ] ምንም አይነት ስጋትም ጥርጣሬ የለንም ብለዋል- ዐቢይ።

ቀጥለውም በጅቡቲ ወታደራዊ ሰፈር የገነቡ ኃያላን ሀገራት “ድንገት ቢታኮሱ” ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ምርቶች አደጋ ሊገጥማቸው ይችላል ሲሉ ተናግረዋል።

“በሌሎች ግጭት ምክንያት ለአንድ ሳምንት ነዳጅ ባይኖር አስቡት። ማዳበሪያ ካልገባ አስቡት” ሲሉ ጠይቀዋል።

ጨምረውም ይህ አይነት ችግር ቢያጋጥም “120 ሚሊዮን ህዝብ ምን እንደርገዋለን ነው ጭንቀታችን ብለዋል።”

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደብን በተመለከተ ኤርትራ፣ ኬንያና ጅቡቲ ከዚህ ቀደም በጎበኙበት ወቅት መነጋገራቸውን እና “መጠየቃቸውን” ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በሌሎች ሀገራት ‘እወረራለሁ’ የሚል ስጋት እንደሌላት ጠቅሰው “ኢትዮጵያን የመጠበቅ ከበቂ በላይ አቅም አለን” ሲሉም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሌሎችም ጉዳዮች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በአማራ ክልል ስላለው ሁኔታ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በዛሬው ንግግራቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲደነገግ ምክንያት የነበረው ግጭት የፈጠረው ስጋት መቀልበሱን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ዓመት ማብቂያ ላይ በአማራ ክልል የተጣለው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በክልሉ መረጋጋትን አምጥቷል ብለዋል።

ጨምረውም አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የክልሉን መንግስት ከመፍረስ ታድጎታል ብለዋል።

“በጉልበት የክልል መንግሰትን እናፈርሳለን ብለው የተነሱ ኃይሎች ነበሩ” ያሉት ዐቢይ የፌዴራሉ መንግሥት ወደ ክልሉ መግባትና የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ “የክልሉን መንግሥት ከመፍረስ አደጋ ታድጓል” ሲሉ ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት የመጨረሻ ወራት ተቀስቅሶ በፋኖ ታጣቂዎች እና በመከላከያ ወታደሮች መካከል እየጠነከረ እና ጋብ እያለ ሲካሄድ የቆየው ውጊያ ባለፈው ሳምንት በብዙ አካባቢዎች በከፍተኛ ሁኔታ መስፋፋቱ ተነግሯል።

ባለፈው ሳምንት አስተያየታቸው ለቢቢሲ የሰጡ ነዋሪዎች በክልሉ አንዳንድ አካቢዎች በታጣቂዎችና በመንግሥት ኃይሎች መካከል ከባድ ውጊያ እንደተደረገ ጠቅሰዋል።

የአማራ ክልል አካባቢዎች ያሉት ነዋሪዎች በምዕራብ እና ምሥራቅ ጎጃም፣ በሰሜን ሸዋ እንዲሁም በማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች “ከፍተኛ ጦርነት እየተካሄደ ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

ባለፈው ሳምንት ማክሰኞና ረቡዕ ደግሞ የፋኖ ታጣቂዎች የላሊበላ ከተማን አብዛኛውን ክፍል ይዘው እንደነበረ ተነግሯል።

ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው የፓርላማ ውሎ በክልሉ የነበረው ስጋት መቀልበሱን ተናግረዋል።

“ነገር ግን የተሟላ ሰላም አልመጣም። ተጨማሪ ውይይት፣ ተጨማሪ ስራ ያስፈልጋል። ያኔ የነበረው ስጋት ተቀልብሷል። የተሟላ ሰላም እንዲመጣ ግን ተጨማሪ ስራ ያስፈልጋል” ብለዋል።

በሌላ በኩል በሀገሪቱ የተለያዩ አካቢዎች ያሉ ችግሮችን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲናገሩ ባለፉት አምስት ዓመታት “በእኛ ዕቅድና መሻት ያደረግነው ጦርነት የለም” ያሉ ሲሆን “አልሞት ባይ ተጋዳይ ሆነን ተከላክለናል” ሲሉ ተናግረዋል

አሁን ግራ ቀኝ በሚደረጉ ትግሎች መንግሥትን ማሸነፍ አይቻል ሲሉ አክለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው መስከረም ማብቂያ ላይ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ለሁለቱ ምክር ቤቶች ያቀረቡትን የፌደራል መንግሥቱን ዕቅድ በተመለከተ ያደረጉት ንግግር ላይ ማብራሪያ ለመስጠት ፓርላማ በተገኙበት ወቀት ነው ይህንን ያሉት።

‘በአማራና ትግራይ ያሉ አወዛጋቢ አካባቢዎችን ችግር ለመፍታት ህዝበ ውሳኔ ጠቃሚ ነው ብለን እናምናለን’

በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአማራና ትግራይ ያሉ አወዛጋቢ አካባቢዎችን ችግር ለመፍታት መንግሥታቸው “በድፍረት” እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

“የፌዴራል መንግስት በትግራይና በአማራ ክልል ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ፤ አንዱ ተደስቶ ሌላኛው አኩርፎ ቀጣይ ግጭት እንዳይፈጠር ህዝበ ውሳኔን ማዕከል ያደረግ አካሄድ ብንከተል ጠቃሚ ነው ብሎ ያምናል” ብለዋል።

ይህንን የመፍትሄ ሀሳብ የሁለቱ ክልል አስተዳዳሪዎች በጋራ እንደተወያዩበት የጠቀሱት ሲሆን “[የፌዴራል መንግሥቱ] አቅጣጫ አስቀምጧል፤ እየሰራበት ይገኛል” ሲሉ አመላክተዋል።

ጨምረውም “ህዝቡን አወያይተናል። የህዝቡንም ምላሽ እናውቃለን። ነገር ግን ይህ መፍትሄ ብቸኛ ስላልሆነ የአማራና የትግራይ ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች ተወያይተው ዘላቂ ሰላም የሚያመጣ መፍትሄ አለን ካሉ በደስታ እንቀበላለን” ሲሉ ተናግረዋል።

የመንግሥታቸው ፍላጎት ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ ማድረግ እንደሆነም አንስተዋል። በተጨማሪም የሚመጣው የመፍትሄ ሃሳብ ህግን የተከተለ መሆን እንዳለበት ጠቅሰዋል።

“በህገመንግስቱ አግባብ መሰረት. . .ዘላቂ ሰላም የሚያረጋግጥና የህዝብን ውሳኔ ያከበረ አቅጣጫ እንከተላለን ብለን እናምናለን” ብለዋል።

“መፍትሄ ሳናመጣ ግን የመጣውን መፍትሄ ግን የማንቀበል ከሆነ ግን ወደ ሰላም አይወስድም” ሲሉም ተደምጠዋል።