የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጦር የውጭ ተዋጊዎች የተሳተፉበትን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ማክሸፉን ገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጦር በፕሬዚዳንት ፊሊክስ ታሺኬዲ ላይ የተቃጣውን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ማክሸፉን ገለጸ።
በዋና ከተማዋ ኪንሻሳ ሊደረግ የነበረው መፈንቅለ መንግሥት የውጭ ተዋጊዎችን እና የኮንጎ ዜጎችን ያሳተፈ እንደነበር ጦሩ አስታውቋል።
የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጦር ቃለ አቀባይ ብሪጋዲየር ጄኔራል ሲልቪን ኤኬንጌ በርካታ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን እና ሁኔታው መረጋጋቱን ለመንግሥታዊው አርቲኤንሲ ቴሌቪዥን ተናግረዋል።
እሁድ ማለዳ ታጣቂዎች የቀድሞ ኢታማዦር ሹም እና የፕሬዚዳንቱ የቅርብ አጋር በሆኑት ቪታል ካመርሄ ቤት ላይ ጥቃት ካደረሱ ከሰዓታት በኋላ ነው ጦሩ መግለጫውን የሰጠው።
የመከላከያ ሰራዊቱን የደንብ ልብስ የለበሱ ወደ 20 የሚጠጉ ታጣቂዎች የባለስልጣኑን መኖሪያ ቤት ማጥቃታቸውን እና የተኩስ ልውውጥ መደረጉን የዓይን እማኞች ተናግረዋል።
በመኖሪያ ቤታቸው ላይ በተፈጸመ ጥቃት ሁለት ጠባቂዎች እና አንድ ታጣቂ መገደሉን የባለስልጣኑ ቃለ አቀባይ እና በአገሪቱ ተቀማጭነታቸውን ያደረጉ የጃፓን አምባሳደር በኤክስ ላይ በለጠፉት ጽሁፎች ላይ አጋርተዋል።
ታጣቂዎቹ በከተማዋ ማዕከል የሚገኘውን እና ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግለትን የፕሬዚዳንቱን ጽህፈት ተቆጣጥረው እንደነበር ተዘግቧል።
የጃፓን አምባሳደር በዋና ከተማይቱ የሚገኙ ዜጎቻቸው በቤታቸው እንዲወሰኑ እና ወደ ውጭ እንዳይወጡ አስጠንቅቀዋል።
ፕሬዚዳንት ፊሊክስ ታሺኬዲ ስለ ሁኔታው እስካሁን ምንም አይነት ይፋዊ አስተያየት አልሰጡም።
የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት አጥቂዎቹ ቀደም ሲል ለግዞት ተዳርጎ ከነበረው ፖለቲከኛ ክርስቲያን ማላንጋ ጋር ግንኙነት ያላቸው የኒው ዛየር ንቅናቄ አባላት እንደሆኑ ነው።
ማላንጋ በሊንጋላ ቋንቋ “እኛ ወታደሮች ደክሞናል፤ ከቪታል ካሜርሄ እና ከፕሬዚዳንት ፌሊክስ ታሺኬዲ ጋር አንድ ላይ መቆም አንችልም” እያሉ የሚናገሩበትን ቪዲዮ ቢቢሲ ተመልክቷል።
ባለፈው ዓመት በታኅሣሥ ወር በተካሄደው አወዛጋቢ ምርጫ ፕሬዚዳንት ፊሊክስ ታሺኬዲ ለሁለተኛ ጊዜ ተመርጠዋል።
ፕሬዚዳንቱ የተመረጡት 78 በመቶ የሚሆነውን ድምጽ አሸንፈው እንደሆነ የተነገረ ሲሆን ከምርጫው ጋር በተያያዘ በተፈጠረ ሁከት ወደ 20 የሚጠጉ ሰዎች ተገድለዋል። ኮንጎ በወርቅ፣ አልማዝና ማዕድናት የበለጸገች ሃገር ብትሆንም ለዘመናት ይህን ሃብቷ እየተበዘበዘ በውጭ አገራት የሚቸበቸብ ሲሆን ህዝቧም ከድህነት አረንቋ መውጣት አልቻለም። በግጭቶች በምትናጠው ኮንጎ በርካታ የውጭ አገራት ኩባንያዎች ተሰማርተው ይገኛሉ።












