በቻድ የጋብቻ ጥያቄን በማይቀበሉ ሰዎች ላይ ቅጣት ተጣለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሰሜን ምስራቅ ቻድ ማንጋልሜ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የጋብቻ ጥያቄን የማይቀበሉ ሰዎች "አምቺሊኒ" በመባል የሚታወቀውን ቅጣት እንዲከፍሉ ተወሰነ።
የክልሉ ከፍተኛ እስላማዊ ምክር ቤት ጥያቄውን የማይቀበሉ ሴቶች ከ23 ዶላር እስከ 39 ዶላር እንዲሁም ወንዶች 15 ዶላር እንዲቀጡ ወስኗል።
ይህንን ውሳኔ በመቃወምም የቻድ ሴቶች መብት ሊግ ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ውሳኔውን እያወገዘ ይገኛል። ሊጉ ውሳኔው ለትዳር የመፈቃቀድ ነፃነት ለዜጎች ያጎናጸፈውን ብሄራዊ ህግ የሚጥስ በመሆኑ ህገወጥ ነው ሲልም ወቅሷል።
የእስልምና ምክር ቤቱ በበኩሉ ውሳኔው ቁርአንን መሰረት አድርጎ የተወሰደ ነው ብሏል። በቻድ ውስጥ ያለፈቃድ የሚደረግ ጋብቻ ከግዜ ወደ ግዜ እየተስፋፋ የመጣ ሲሆን ዕድሜያቸው ለትዳር ያልደረሱ ልጃገረዶች የልማዱ ተጠቂዎች ናቸው።
እ.ኤ.አ. በ2015 እድሜያቸው ያልደረሱ ልጆችን ለጋብቻ መስጠትን የሚከለክል ህግ ቢወጣም እድሜያቸው ከ20 አመት እስከ 24 ዓመት የሚሆናቸው ሴቶችውስጥ 60 በመቶው ያገቡት ገና በልጅነታቸው ነው ሲል የቻድ የስታስቲክስ ተቋም መረጃ ያሳያል።
ዩኒሴፍ ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያሳየው በዓለም ላይ በሁለቱም ፆታዎች 765 ሚሊዮን ህፃናት ያለ ዕድሜያቸው የሚጋቡ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 115 ሚሊየኖቹ ህፃናት ወንዶች ናቸው።
ምርምሩ የ82 ሃገራትን መረጃ የወሰደ ሲሆን፤ ከ20 እስከ 24 እድሜ ካሉ ወንዶች ውስጥ 4.5% ከ18 ዓመት በታች ያገቡ መሆናቸውን ያሳያል።
በሪፖርቱ መሰረት የላቲን አሜሪካና የካሪቢያን ደሴቶች በ8.3% በአንደኛነት ሲቀመጡ፤ የእስያና ፓስፊክ ሃገራት በ5.9 % ሁለተኛውን ሲይዙ፤ የመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት ከ2% ባነሰ ቁጥር በትንሽነቱ ይጠቀሳሉ።
በአንደኛነት የሴንትራል አፍሪካ ሪፐብሊክ በ27.9% ስትመራ፤ ኒካራጓ በ19.4%ና ማዳጋስካር በ12.9% ተከታትለው የሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።ያለዕድሜ ጋብቻ ከሚፈፀምባቸው ቁጥራቸው ከፍተኛ ከሆኑት ሃያ ሃገራት መካከል ሰባቱ ላቲን አሜሪካ ይገኛሉ።












