“ቤተሰቦቼ በዕድሜ እጥፍ ለሚበልጠኝ ሰው በከብት ለወጡኝ”-ያለ ዕድሜ ጋብቻ በኢትዮጵያ

የተሸፈነች ሙሽራ

የፎቶው ባለመብት, ERIC LAFFORGUE/ART IN ALL OF US

እናት የ13 ዓመት ታዳጊ ሳለች ነው በዕድሜ በእጥፍ ለሚበልጣት ሰው የተዳረችው።

ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ድርቅ ነው።

ድርቁ ያስከተለባቸውን ረሃብ መቋቋም የተሳናቸው ቤተሰቦቿ የእናትን የወደፊት ተስፋ ሰውተው በምትኩ በ17 ዓመት ከሚበልጣት ባሏ የቀንድ ከብት ተቀበሉ።

እናት፤ ብሩህ አዕምሮ ያላት፤ ትምህርቷን አጥብቃ የምትወድ እንደነበረች የሚያውቋት ይመሰክራሉ።

“ይህ የሆነው ከሁለት ወራት በፊት ነው። እኔ የማውቀው ነገር አልነበረም” ትላለች እናት።

“ቤተሰቦቼ ሊድሩኝ መስማማታቸውን ስሰማ ተቃወምኩ፣ ለመንኳቸው፣ አለቀስኩኝ. . . ግን ማንም ሊሰማኝ ፈቃደኛ አልነበረም።”

እናት በደቡብ ክልል ዳሰነች ወረዳ ነው የምትኖረው። የዘንድሮ ድርቅ ክፉኛ የመታት ዳሰነች ነዋሪዎች ለከፍ ድህነት ተጋልጠዋል።

እናት የስድስት እህትና ወንድሞቿ ታላቅ ናት። ድርቁ ከመምጣቱ በፊት ሁሉም ነገር ሰላም እንደነበር ታወሳለች።

“አባቴ ከ100 በላይ ከብቶች ነበሩት። እኔን ሊድረኝ ፈጽሞ ፈቃደኛ አይሆንም ነበር። ነገር ግን ከብቶች ውሃም ሆነ የሚበሉት ነገር ጠፋ። አንድ በአንድ ያሉን ከብቶች አለቁ። ይሄኔ ነው ባል የሚሆነኝ ሰው ማፈላለግ የጀመሩት።”

“ቤተሰቦቼ እኔና እህት ወንድሞቼን የሚያበሉት ሲያጡ በዕድሜ እጥፍ ለሚበልጠኝ ሰው ዳሩኝ። በጥቂት ከብቶች ለወጡኝ። ከብቶቹን ሸጠው ባገኙት ገንዘብ በቆሎና ስንዴ ገዝተው እህትና ወንድሞቼን ለማቆየት ወሰኑ።”

ይህ የእናት ታሪክ የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ (ዩኒሴፍ) በቅርቡ ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦች ልጆቻቸውን ያለ ዕድሜያቸው እየዳሩ ነው ሲል ባወጣው ሪፖርት ላይ የተጠቀሰ ነው።

ዩኒሴፍ ኢትዮጵያ ውስጥ ያላቻ ጋብቻ ለመጨመሩ እንደ ምክንያት የጠቀሰው ተፈጥሯዊ አደጋ እና ሰው ሰራሽ ችግር ነው።

ያለ ዕድሜ ጋብቻና ሰላም እጦት ምን አገናኛቸው?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አለሁበል አለማው የሄልዝና ሆልነስ ኢትዮጵያ መሥራችና ዳይሬክተር ናቸው።

ድርጅታቸው በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ያለዕድሜ ጋብቻ፣ ፆታዊ ጥቃት፣ ሴቶችን ማብቃት [Women Empowerment] እና መሰል ጉዳዮች ላይ እንደሚሠራ አቶ አለሁበል ይገልጣሉ።

ዳይሬክተሩ እንደሚሉት በተለይ የመንግሥት ለውጥ ከመጣ በኋላ የተከሰተውን አለመረጋጋት ተከትሎ ያለዕድሜ ጋብቻ እየጨመረ መጥቷል።

“ከዚያ በፊት ሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓቶችን ተገን አድርገው ነበር ጋብቻውን የሚፈፅሙት። አሁን ግን ቁጥጥር በመላላቱ በይፋ ሠርግ ሲደገስ ማየት ጀምረናል።”

ለምሳሌ በአማራ ክልል ሰቆጣና ሰሜን ጎንደር አካባቢ ትምህርት ባለመጀመሩ ቤተሰብ ልጆቹን መዳር ጀምሯል ይላሉ አቶ አለሁበል።

ከሌሎች መሰል ድርጅቶች ጋር በአጋርነት የሚሠሩት አቶ አለሁበል፣ በተለይ በትግራይ ክልልና ወደ ሰሜኑ የሚጠጋው የአማራ ክልል አካባቢ ያለዕድሜ ጋብቻ መጨመሩን ይጠቅሳሉ።

በትግራይ ክልል በቆላ ተምቤን፣ ደጉዓ ተምቤን፣ ሕንጣሎ ወጀራት እና ራያ ዓዘቦ ወረዳዎች ያለዕድሜ ጋብቻ በስፋት እንደሚፈጸም ከክልሉ የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።

አልፎም በኦሮሚያም የተወሰኑ ሥፍራዎች እንዲሁም በአፋርና ሶማሌ ይህ ባሕል እንደሚስተዋል ይገልጣሉ።

“ቤተሰብ ባለው የሰላም እጦት ተስፋ እየቆረጠ ልጆቹን ያለዕድሜያቸው እየዳረ ነው” ይላሉ።

በፈረንጆቹ 2011 የወጣ አንድ ጥናት ኢትዮጵያ ውስጥ ለሴቶች አማካይ የጋብቻ ዕድሜ 16.5 ነው ይላል።

ይህ ጥናት አክሎም በአገሪቱ ካሉ ሴቶች 40 በመቶው በ20ዎቹ ዕድሜያቸው ጋብቻ መፈፀማቸውን አስቀምጧል።

የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ (ዩኒሴፍ) በፈረንጆቹ 2016 ባወጣው ዘገባ የኢትዮጵያ መንግሥት ያላቻ ጋብቻን በአሥር ዓመት ሊያጠፋ አቅዷል ብሎ ነበር።

በዚህ ትንበያ መሠረት የኢትዮጵያ መንግሥት ያለእድሜ ጋብቻን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት 3 ዓመታት ይቀሩታል።

እውነታው ግን ወዲህ ነው ይላሉ ባለሙያው፤ ያላቻ ጋብቻ ከመጥፋት አሊያም ከመቀነስ ይልቅ በሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ቀውስ ታግዞ እየጨመረ መጥቷል።

አለመረጋጋት ከመስተዋሉ በፊት የመንግሥት አካላት ያለዕድሜ ጋብቻ እንዲቀንስ በየቀበሌው ይሠሩ እንደነበር በመጥቀስ፣ ፖሊስም ጥቆማ ሲደርሰው ሁኔታውን ይከላከል ነበር ብለዋል።

“ትምህር ቤቶች፣ የሴቶች ጉዳይ ቢሮዎች የድርሻቸውን ይወጡ ነበር። ከ2014-17 [በፈረንጆቹ] መጀመሪያ ድረስ መልካም ለውጥ ተመልክተናል። አሁን ግን ተመልሶ ከዚህ በፊት ከነበረውም ብሶ ተገኝቷል።”

በየቦታው ካለው ግጭት የተነሳ ሕፃናትና ታዳጊዎች ከቤት ጠፍተው ወደ ከተማ እየሄዱ እንደሆነ፣ አንዳንዶች ደግሞ የቤት ሠራተኞ ሆነው በመቀጠር ለመደፈር እየተጋለጡ እንደሆነ አቶ አለሁበል ይጠቁማሉ።

ያለ ዕድሜ ጋብቻ ከሰው ሠራሽ ችግር ጋር ብቻ ሳይሆን ከተፈጥሯዊ ቀውስ ጋር እንደሚያያዝ አቶ አለሁበል ያስረዳሉ።

“ድርቅና ሌሎች ተፈጥሯዊ አደጋዎችም ለችግሩ አስተዋፅዖ ያደርጋሉ” ይላሉ።

“አብዛኛው ማኅበረሰባችን ኑሮውን የመሠረተው እርሻ ላይ ነው። ድርቅ ገብቶ ይህ ከእጅ ወደ አፍ የሆነው ኑሮ ችግር ላይ ሲወድቅ የተሻለ ምርት አለበት ከሚባልበት አካባቢ ሰዎች ጋር ጋብቻ ይመስርታሉ” ሲሉ ይተነትናሉ።

“መቀናጆ የሚባል የጉልበት ሥራ አለ። ወላጆች ልጆቻቸውን ወደዚህ ሥራ ሲያስገቡ ትምህርት ይቋረጣል። ትምህርት ሲቋረጥ ልጆቹ ተስፋ ይቆርጣሉ። በዚህ ጊዜ የጋብቻ ጥያቄ ይቀርብላቸዋል። እንደዚህ ነው ያለ ዕድሜያቸው የሚዳሩት።”

አቶ አለሁበል ከልምዳቸው በመነሳት እንደሚናገሩት አብዛኛዎቹ ሴቶች ከ14 አስከ 17 ባለው ዕድሜያቸው ነው የሚዳሩት።

“ብዙዉን ጊዜ ታዳጊ ሴቶች የወር አበባ የሚመለከቱት በዚህ ዕድሜ ስለሆነ ወላጆች ሴት ልጆቻቸው ከጋብቻ ውጭ ሊወልዱ ይችላሉ፤ አልያም የአካባቢውን ባሕልና ወግ ሊጥሱ ይችላሉ በማለት ወደ ትዳር ይገፏቸዋል።”

ባለሙያው አክለውም ሴቶች ብቻ ሳይሆን ወንዶችም ያለዕድሜያቸው ጋብቻ እንዲመሠርቱ እንደሚደረግ ይናገራሉ።

“ሴቶች የበለጠ ተጋላጭ መሆናቸው እርግጥ ነው። ነገር ግን ወንዶችም ያለዕድሜያቸው ይዳራሉ።”

ወንዶች በተለይ ከ14 አስከ 21 ባለው ዕድሜያቸው ለዚህ እንደሚጋለጡ ባለሙያው ያስረዳሉ።

“ቤተሰብ ወንድ ልጅ ‘ሚስት ካገባ ጥሎ አይሄድም። ለሚስቱ ሲል ይሠራል። ቤተሰብንም ያግዛል’ ብለው በማሰብ ወደ ትዳር እንዲያገቡ ያደርጓቸዋል።”

ባለሙያው አክለውም “ወንድ ልጅ በባሕሉ መሠረት በዕድሜ የምታንስ ሚስት ማግባት ስላለበት ታዳጊ ሚስት ነው የሚያገባው።”

አቶ አለሁበል ያለአቻ ጋብቻና ያለዕድሜ ጋብቻ ያላቸውን ልዩነት እንዲህ ያስረዳሉ።

“ያለ ዕድሜ ጋብቻ ወንዱም ሴቷም ያለ ዕድሜያቸው ሲዳሩ ነው። ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ማለት ነው። ያለአቻ ጋብቻ ደግሞ ሴቷ ከ18 በታች ወንዱ ደግሞ ዕድሜው በጣም ከፍ ያለ ሲሆን ነው” ይላሉ። 

ያለ ዕድሜ ጋብቻ በኢትዮጵያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

"በ29 ዓመቴ አያት ሆንኩ"

መቀመጫውን አዲስ አበባ ያደረገው የአፍሪካ ድንቃ ድንቅ መዝጋቢ ተቋም ከሰሞኑ በዕድሜ ትንሿ ላላት አያት እውቅና ሰጥቷል።

የ29 ዓመቷ ሪሃና ሞሐመድ በ29 ዓመቷ የአራት ልጆች አያት መባሏ አነጋጋሪ ሆኗል።

የከሚሴ ከተማ ነዋሪዋ ሪሃና ሞሐመድ በ13 ዓመቷ አግብታ በ14 ዓመቷ የመጀመሪያ ልጇን፤ በ15 ዓመቷ ደግሞ ሁለተኛ ልጇን ተገላገለች።

ሪሃና፤ ሁለተኛ ልጇን ልክ እንደሷ በ13 ዓመቷ ነው የዳረቻት። ልጇም በ14 ዓመቷ እናት ሆነች፤ እናቷን ደግሞ አያት አደረገቻት።

ሪሃና በፍቅር አሊያም በፍላጎት ሳይሆን በቤተሰብ ግፊት ነበር በዕድሜ ከሚበልጣት ሰው ጋር ትዳር የፈፀመችው። ቢሆንም መልካም የሚባል ሰው ስለገጠማት ደስተኛ መሆኗን ለአንድ የአገር ውስጥ የመዝናኛ ፕሮግራም ተናግራለች።

የ29 ዓመቷ አያት ይህን ትበል እንጂ በርካታ ያለዕድሜያቸው የሚዳሩ ታዳጊ ሴቶች ከብዙ ነገር እንደሚስተጓጎሉ ይናገራሉ።

የአበባን ታሪክ ማንሳት እንችላለን።

ጊዜው ኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ተስፋፍቶ ብዙዎች ቤታቸው ተከርችመው የሚከርሙበት ወቅት ነበር።

በደቡብ ጎንደር የምትኖረው አበባ በወረርሽኙ ምክንያት ትምህርቷን አቋርጣ ቤተሰቦቿን እያገዘች ቀኖቿን ትገፋ ነበር።

የትምህርት ቤቷ ቅጥር ግቢ በሩን ለተማሪዎች ክፍት አድርጎ ተማሪዎችን የሚቀበልበትን ቀን በናፍቆት ትጠብቅ የነበረችው አበባ ለአንድ በዕድሜ ለሚበልጣት ባለፀጋ ልትዳር ሆነ።

ያለፈቃዷ ሃብት አለው ለተባለው ግለሰብ ስትዳር፣ በሚሰጣት ጥሎሽ የቤተሰቦቿ ሕይወት እንዲለወጥ ተፈረደባት።

በሴቶች ጉዳይ ላይ የሚሠሩ ድርጅቶች ይህን ሰምተው ባደረጉት ርብርብ አበባን መታደግ ቻሉ። አበባም ሐኪም የመሆን ሕልሟን ለማሳካት ወደ ትምህርቷ ተመለሰች።

በ2012 በአማራ ክልል ብቻ 1700 ያለዕድሜ ጋብቻዎች መፈፀማቸውን የክልሉ የሕፃናትና ሴቶች ጉዳይ ቢሮ አስታውቆ ነበር።

“ባሕልም ተጠያቂ ነው”

ዩኒሴፍ ልክ እንደሌሎች አገራት ኢትዮጵያም ኮሮናቫይረስ ካስከተለው ኢኮኖሚያዊ ጫና አልተረፈችም ይላል።

ይህ ጫና ከድርቅና በየአካባቢው ከሚከሰቱ ግጭቶች ጋር ተደማምሮ ሕፃናት ያለዕድሜያቸው እንዲዳሩ አስተዋጽዖ ማበርከቱን ይገልጣል።

“በአንድ ዓመት ብቻ በድርቅ በተጠቁ ክልሎች ያለአቻ ጋብቻ በሁለት እጥፍ ጨምሯል” ይላል የዩኒሴፍ ሪፖርት።

የሶማሌ፣ የኦሮሚያ እና የደቡብ ክልሎች በድርቅ መመታታቸውን ተከትሎ በፈረንጆቹ ከጥር እስከ ሚያዚያ 2022 ባለው ጊዜ ብቻ ያለ አቻ ጋብቻ 119 በመቶ መጨመሩን የመንግሥት መረጃዎች ያመለክታሉ።

“ይህ ባሕል በሁሉም ክልሎች ይስተዋላል” ይላሉ የሥርዓተ-ፆታ ተሟጋቿ ማርታ ታደሰ።

“ድርቅና ግጭት ኢኮኖሚያዊ ችግር ያስከትላሉ። አንዳንድ ቤተሰቦች እንደ ጊዜያዊ መፍትሄ የሚወስዱት ዕድሜያቸው ለትዳር ያደረሱ ሴት ልጆቻቸውን መዳር ነው።”

ማርታ፤ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ ችግሮች ከሚያመጡት መዘዝ ባለፈ ባሕልም የራሱ አስተዋጽዖ እንዳለው ያወሳሉ።

“ሴት ልጅ ጡቷ ማደግ ሲጀምር፣ ቁመት ስትጨምር፣ ቤተሰብ 'ደርሳለች' ብሎ ያስባል። ብዙውን ጊዜ ብዙ ልጆች ያሏቸው ቤተሰቦች ልጆቹ ራሳቸውን ችለው ትምህርት ቤት መመላስ ሲጀምሩ እነሱን የሚደግፉበት አቅም ስለሌላቸው ይድሯቸዋል።”

በዩኒሴፍ የልጆች ጥበቃ ባለሙያዋ ዘምዘም ሽኩር በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ።

ኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት ያላቻ ጋብቻን ቢያንስ በአንድ ሦስተኛ መቀነስ መቻሏን የሚያነሱት ባለሙያዋ፣ በአማካይ ሴት ልጆች ትዳር የሚይዙበት ዕድሜ ከ16.5 ወደ 17.1 ከፍ ብሎ እንደነበር ይገልጣሉ።

ነገር ግን ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች ያላቻ ጋብቻ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን እሳቸውም ማስተዋላቸውን ይጠቅሳሉ።

“በተለያዩ ቦታዎች ግጭቶች አሉ። በዚህ ምክንያት ያላቻ ጋብቻ መንግሥታዊም ሆኑ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ አልሆነም። ሕይወት ማዳን ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ሆኗል።”

በከረዩ የምታገባ ሴት እግር ላይ አምባር ሲታሰር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የእናት ዕጣ ፈንታ?

ማርታ፤ ሴቶች ያለ ዕድሜያቸው መዳራቸው ትምህርታቸውን ከማስተጓጎሉም በላይ ለፊስቱላ፤ ከፍ ሲልም ለሞት ሊዳርጋቸው እንደሚችል ይገልጣሉ።

“ልጅቷ 'ቤተሰብ ስለተቸገረ ነው የዳረኝ' ብላ ስለምታስብ የቤት ውስጥ አሊያም ፆታዊ ጥቃት ሲደርስባት መናገር ትፈራለች። ደፍራ ብትናገርም ቤተሰቧ 'አማራጭ የለሽም፤ አርፈሽ ቁጭ በይ' ነው የሚሏት።”

ዩኒሴፍን ጨምሮ እንደ አቶ አለሁበል ያሉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጉዳዩ ትልቅ ትኩረት እንዲሰጠው እየጣሩ ነው።

ግንዛቤ ማስጨበጥ መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን ደግመው ደጋግመው ያነሳሉ።

“ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ብንሠራም። ሁሉንም ቤተሰብ መድረስ፣ ሁሉንም ማሳመን ጊዜ የሚፈልግ ነው” ይላሉ የዩኒሴፍ ባለሙያዋ ዘምዘም።

ኢትዮጵያ ያላቻ ጋብቻ የሚፈፅሙም ሆኑ የሚያስፈፅሙ አካላት በወንጀል ይጠየቃሉ ብትልም፣ ሕጉ ምን ያህል ተግባራዊ ሆኗል? የተወሰዱ እርምጃዎችስ ምን ያህል ስኬታማ ናቸው? የሚሉ ጥያቄዎች እንዳሏት የምትናገረው ማርታ፤ ጉዳዩ ከመንግሥት ትኩረት ይሻል ስትል ታሰምራለች።

“አብዛኛዎቹ ያለዕድሜ ጋብቻዎች በሽምግልና፣ በይቅርታ፣ በቤተ ክርስትያን ነው የሚፈቱት። እነዚህ ዓይነት ክፍተቶች ስላሉ ነው ዘላቂ የሆነ ለውጥ የማይመጣው።”

በኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት ወራት ያለ አቻ ጋብቻ መጨመሩን ተከትሎ ከትምህርት ገበታቸው የቀሩ ሴት ልጆች ቁጥር ሦስት እጥፍ ማደጉን ዩኒሴፍ ይጠቅሳል።

የ13 ዓመቷ እናት ዕጣ ፈንታም ሆኗል።

“[ባለቤቴ] ትምህርቴን እንድቀጥል ፈቃደኛ ባለመሆኑ አቋርጫለሁ” ትላለች።

“መማር በጣም እፈልጋለሁ። ሕልሜ ዶክተር መሆን ነው። አሁን ግን ወጥ እየሠራሁ፣ ቤት እያፀዳሁ፣ ውሃ እየቀዳሁ ነው የምውለው።”