በኒው ጀርዚ ሰማይ ላይ የታዩት ምስጢራዊ ድሮኖች የኢራን እንዳልሆኑ ፔንታገን አስታወቀ

ፔንታገን በአሜሪካዋ ኒው ጀርዚ ግዛት አካባቢ የታዩት ድሮኖች ከኢራን የጦር መርከብ የተነሱ እንዳልሆኑ አስታውቋል።

በቅርብ ሳምንታት በኒው ጀርዚ ሰማይ ላይ በርካታ ድሮኖች የታዩ ሲሆን አንዳንድ ድሮኖች ወታደራዊ ካምፖች እና የተመራጩ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ጎልፍ መጫወቻ አካባቢ ታይተዋል።

የአሜሪካ ኮንግረስ አባል የሆኑት ጄፍ ዳን ድሩ "ከፍተኛ አመኔታ ካላቸው" ምንጮቼ ሰማሁ ብለው ድሮኖቹ ከኢራን ጋር ግንኘነት እንዳላቸው ተናግረው ነበር።

የኒው ጀርዚው ሪፐብሊካን ለፎክስ ኒውስ በሰጡት ቃለ-ምልልስ ድሮኖች አትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ ከሚገኝ የኢራን የጦር አውሮፕላን የተነሱ ናቸው ብለዋል።

"መርከቧ የምትገኘው በዩናይትድ ስቴትስ ምስራቃዊ ጠረፍ አካባቢ ነው። ወደ ምናየው እና የምንሰማው ነገር ሁሉ ድሮኖች ለቀዋል" ሲሉ የኮንግረስ አባሉ ረቡዕ ተናግረው እንደነበር ይታወሳል።

"ከፍተኛ አመኔታ ካላቸው ምንጮቼ ያገኘሁት መረጃ ነው። በቀላሉ የምወስደው ጉዳይ አይደለም።"

አክለው አሜሪካ ድሮኖቹ ተኩሳ እንድትጥላቸው ምክረ ሐሳብ ሰጥተዋል።

ነገር ግን የፔንታገን ምክትል ፕሬስ ሴክሬታሪ ሳብሪና ሲንግ የሰውየው አስተያየት ውሀ የሚያነሳ አይደለም ሲሉ አጣጥለውታል።

ረቡዕ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት ሳብሪና "በዩናይትድ ስቴትስ ምስራቃዊ ጠረፍ ምንም ዓይነት የኢራን የጦር መርከብ የለም። ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ድሮኖችን እየተኮሰ ያለ መርከብም የለም" ብለዋል።

አክለው ፔንታገን በመጀመሪያ ዙር ምርመራ ድሮኖቹ "ከውጭ ሀገር አሊያም ከሌላ ቦታ የመጡ አለመሆናቸውን" ማወቅ ችሏል ይላሉ።

ቫን ድሩ ከፔንታገን ምላሽ በኋላ በቀጣዩ ቀን ፎክስ ኒውስ ላይ ድጋሚ ቀርበው "እውነታው እየተነገረን አይደለም" ብለዋል።

ፔንታገን "የአሜሪካ ሕዝብ እንደ ሞኝ ነው የሚመለከተው" ሲሉ የመከላከያ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን ወርፈዋል።

ሌላኛው የኒው ጀርዚ ሴናተር ዲሞክራቱ ሪቻርድ ብሉሜንታል "አስፈላጊ ከሆነ" ድሮኖች ተመትተው ይጣሉ ማለታቸውን አሶሲየትድ ፕሬስ ዘግቧል።

የብሔራዊ ደኅንነት ቃል አቀባይ የሆኑት ጆን ኪርቢ "የተባሉት ድሮኖች ብሔራዊ አደጋ ስለመደገናቸው ምንም ማስረጃ የለም" ሲሉ ከዋይት ሐውስ መግለጫ ሰጥተዋል።

አክለው አብዛኛዎቹ ድሮን እየተባሉ ሪፖርት የሚደረጉ በራሪዎች ሰዎች የሚያበሯቸው አነስተኛ አውሮፕላኖች ናቸው ብለዋል።

መብረር በማይፈቅድባቸው ቦታዎች እስካሁን ምንም የድሮን በረራዎች አልታዩም።

ኪርቢ ጨምረው ኮንግረሱ የድሮን ቁጥጥርን በተለመከተ ጠበቅ ያለ ሕግ እንዲያወጣ አሳስበዋል።

በሌላ በኩል በኒው ዮርክ ከተማ ብሮንክስ በተባለው ሥፍራ በርካታ ድሮኖች ሐሙስ ዕለት ሲበሩ መታየታቸውን አንድ የፖሊስ መኮንን በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ ተናግረዋል።

በቅርቡ ዩናይትድ ኪንግደም በሚገኙ የዩናይትድ ስቴትስ አየር ኃይል ጣቢያዎች አካባቢ ድሮኖች ምንነታቸው ያልታወቁ ድሮኖች መታየታቸው አይዘነጋም።

ኤፍቢአይ ኒው ጀርዚ አካባቢ ፒካቲኒ አርሰናል በተበላው ወታደራዊ የምርምር ጣቢያ እና ቤድሚኒስተር በተባለችው ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው የትራምፕ ጎልፍ መጫወቻ አካባቢ የታዩትን ድሮኖች እየመረመረ እንደሆነ አስታውቋል።

የዩኤስ ፌዴራል አቪየሽን አስተዳደር ደግሞ በቤድሚኒስተር እና በፒካቲኒ አካባቢ ለጊዜው ድሮን ማብረር የሚከለከል እግድ አውጥቷል።