ፈረንሳይ የተሰነዘረባትን የፀረ ሴማዊነት ክስ ተከትሎ የአሜሪካ አምባሳደርን ጠራች

በፈረንሳይ የአሜሪካ አምባሳደር ቻርለስ ኩሽነር

የፎቶው ባለመብት, MOHAMMED BADRA/EPA/Shutterstock

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ፈረንሳይ፤ እየጨመረ የመጣውን ፀረ ሴማዊነት ለማስቆም አልቻለችም በሚል የቀረበባትን ክስ ተከትሎ በፓሪስ የሚገኙትን የአሜሪካ አምባሳደር ቻርለስ ኩሽነር ማብራሪያ እንዲሰጡ እንደምትጠራ አስታወቀች።

አምባሳደር ኩሽነር አይሁዳዊ ሲሆኑ ልጃቸውም ጃሬድ ኩሽነርም የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን ሴት ልጅ ኢቫንካን ትራምፕን አግብቷል።

አምባሳደሩ ፈረንሳይን ያስቆጣውን አስተያየት የሰጡት በዎል ስትሪት ጆርናል ጋዜጣ ላይ ለፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በጻፉት ይፋዊ ደብዳቤ ነው።

ከቀናት በፊት እስራኤል በፈረንሳይ ላይ ያቀረበችውን ትችት በመደገፍ ደብዳቤውን የጻፉት ኩሽነር፤ የጋዛ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ፈረንሳይ ውስጥ የአይሁድ ጥላቻ በከፍተኛ መጠን መጨመሩን ተናግረዋል።

የአገሪቱ የውጭ ጒዳይ ሚኒስቴር ይህንን ክስ ተከትሎ ባወጣው መግለጫ፤ "ተቀባይነት የሌለው" ሲል የጠራውን "የቅርብ ጊዜ ውንጀላዎች" ፈረንሳይ "አጥብቃ ትቃወማለች" ብሏል።

ኩሽነርም ሰኞ ዕለት ለማብራሪያ እንደሚቀርቡ አክሏል።

አምባሳደሩ በደብዳቤያቸው፤ ማክሮን በእስራኤል ላይ የሚሰነዝሩትን ትችት እንዲቀንሱ የጠየቁ ሲሆን "በፈረንሳይ ሕይወት ውስጥ የረጅም ጊዜ ጠባሳ" ሲሉ የገለጹትን የፀረ ሴማዊነት ጉዳይ በምሳሌዎች ዘርዝረዋል።

"ፈረንሳይ ውስጥ አይሁዳውያን በመንገድ ላይ ሳይደበደቡ፣ ምኩራቦች ወይም ትምህርት ቤቶች ጉዳት ሳይደርስባቸው ወይም የአይሁዳውያን የንግድ ተቋማት ሳይዘረፉ አንድም ቀን አያልፍም። የራሳችሁ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር በቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ውስጥ እንኳ ፀረ ሴማዊ ድርጊቶች እንደተፈጸሙ ሪፖርት አድርጓል" ሲሉ ወቅሰዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በተጨማሪም ጉዳዩን ለመቅረፍ ከማክሮን እና ከሌሎች የፈረንሳይ መሪዎች ጋር "ከፍተኛ እቅድ ለማውጣት" ዝግጁ መሆናቸውን አክለዋል።

የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ፤ ከ1961 የቪየና ኮንቬንሽን ጀምሮ አምባሳደሮች በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት እንደማይፈቀድላቸው አጽንኦት ሰጥቷል።

የኩሽነር ደብዳቤ፤ በእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ባለፈው ሳምንት ለማክሮን በጻፉት ደብዳቤ ያነሷቸውን አስተያየቶች የሚያስተጋባ ነው።

ኔታንያሁ በደብዳቤያቸው፤ የፈረንሳዩ መሪ ለፍልስጤም መንግሥት ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲሰጠው በመጠየቅ ለፀረ ሴማዊነት አስተዋጾ አበርክቷል በማለት ከስሰዋል።

ኔታንያሁ ይህንን ያሉት ፈረንሳይ በመስከረም ወር ለፍልስጤም አገርነት በይፋ እውቅና ለመስጠት እንዳቀደች ይፋ ማድረጓን ተከትሎ ነው።

ማክሮን ይህንን እቅድ ይፋ ባደረጉበት ወቅት፤ "ሀገረ ፍልስጤምን መገንባት፣ ኅልውናውን ማረጋገጥ እንዲሁም ከወታደራዊ ኃይል ነጻ መደረጉን እና ለእስራኤል እውቅና መሰጠቱትን በማረጋገጥ ለመላው መካከለኛው ምሥራቅ ደኅንነት አስተዋጽዖ ማበርከት አለብን። ሌላ አማራጭ የለም" ብለው ነበር።

ፕሬዝዳንቱ ከዚህ ቀደም ፀረ-ሴማዊነት ከፈረንሳይ እሴቶች ጋር የሚቃረን መሆኑን በመግለጽ ተችተው ነበር። ከጋዛ ጦርነት ጋር በተያያዙ ለተፈጠሩ ፀረ ሴማዊ ክስተቶች በሰጡት ምላሽም ምኩራቦችን እና ሌሎች የአይሁድ ማዕከሎችን ለመጠበቅ የሚወሰደውን የደኅንነት እርምጃ ጨምረዋል።

መስከረም 26/2017 ዓ.ም. በደቡባዊ እስራኤል በሐማስ በተፈጸመው እና 1200 ሰዎች ተገድለው 251 ከታገቱበትን ጥቃት ወዲህ የተነሳው ጦርነት ወደ ሁለተኛ ዓመቱ እየጠጋ ነው።

በዚህ ጊዜ ውስጥ እስራኤል በፈጸመቻቸው ጥቃቶች ከ60,000 በላይ ሰዎች እንደተገደሉ የሐማስ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

ባለፈው ሳምንትም ጋዛ ከተማ ውስጥ ረሃብ መከሰቱ ተረጋግጧል።

'ዘ ኢንተርግሬትድ ፉድ ሴክዩሪቲ ፌዝ ክላሲፊኬሽን' የተባለው ዓለም አቀፍ ኢኒሺየቲቭ፤ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎች "በከፍተኛ መጠን" "ረሃብ፣ ድህነት እና ሞት" እንደተጋረጠባቸው አስታውቋል።

እስራኤል በበኩሏ በቀጣናው ረሃብ ተከስቷል መባሉን በመካድ፤ ሪፖርቱን "የለየለት ውሸት" ስትል ገልጻዋለች።