ዩክሬን እና ሩሲያ ለአዲስ የሰላም ድርድር ቀጠሮ መያዛቸውን ዜሌንስኪ ተናገሩ

ዜሌንስኪ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ሩሲያ እና ዩክሬን በመጪው ረቡዕ በኢስታንቡል አዲስ የሰላም ድርድር እንደሚያካሂዱ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ገለፁ።

ዜሌንስኪ "ዛሬ ከሩስተም ኡሜሮቭ (ከዩክሬን የፀጥታ ምክር ቤት ኃላፊ) ፣ ጋር ስለ እስረኛ ልውውጥ ዝግጅት እና በቱርክ ከሩሲያ ጋር ስላለው ቀጣይ ስብሰባ ተወያይቻለሁ" ሲሉ ሰኞ ዕለት ባደረጉት ንግግር ላይ ተናግረዋል።

"ኡሜሮቭ ስብሰባው ለረቡዕ እንደታቀደ ተናግሯል።"

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሞስኮ እና በኪዬቭ መካከል በ50 ቀናት ውስጥ የተኩስ አቁም ስምምነት መድረስ ካልተቻለ ሩሲያ ላይ "ከባድ" ማዕቀብ እንደሚጥሉ ከዛቱ ከቀናት በኋላ ዜሌንስኪ በሳምንቱ መጨረሻ አዲስ ውይይት እንዲደረግ ጠይቀዋል።

ሩሲያ የምትፈጽመውን ጥቃት አጠናክራ መቀጠሏን ተከትሎ ዋሽንግተን ለዩክሬን መከላከያ አዲስ የጦር መሳሪያ ለመስጠት ቃል ገብታለች።

ሞስኮ ይደረጋል ስለተባለው የሰላም ንግግር እስካሁን የተናገረችው ነገር የለም።

የቱርክ መንግሥት ቃል አቀባይ ረቡዕ በኢስታንቡል ውይይቱ እንደሚደረግ አረጋግጠው፣ ቦታው ከዚህ ቀደም በግንቦት እና ሰኔ ወር የተኩስ አቁም ለማድረግ ውይይት የተደረገበት እንደሚሆን ተናግረዋል።

የዚህ ሳምንት ንግግር ከሦስት ዓመታት በላይ የዘለቀው ጦርነትን ለማስቆም የሚደረግ ሌላ ሙከራ ይሆናል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ትራምፕ በዩክሬን ጦርነት የሰላም ስምምነት ላይ ለመድረስ ባለመቻሉ በቭላድሚር ፑቲን መበሳጨታቸው ይታወሳል።

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ለቢቢሲ በሩሲያው መሪ "አዝነዋል" ግን "ተስፋቸው አለመሟጠጡን" ተናግረው ነበር።

የዩክሬን ከፍተኛ ባለስልጣን ለኣዣንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደተናገሩት በኢስታንቡል የሚደረገው ንግግር ተጨማሪ የእስረኞች ልውውጥ ላይ እና በዜሌንስኪ እና ፑቲን መካከል ሊኖር ስለሚችል ስብሰባ ላይ ሊያተኩር ይችላል።

ሞስኮ ግን በቅርቡ ተጨባጭ ውጤት ላይ የመድረስ ዕድሉን ዝቅ አድርጋ አቅርባዋለች።

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ሰኞ ዕለት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ሊኖሩ ስለሚችሉ ተስፋዎች ሲናገሩ ሁለቱ ወገኖች "በተቃራኒ አቅጣጫ የቆሙ" እና "ብዙ ዲፕሎማሲያዊ ሥራ ይጠብቃል" ብለዋል።

ሩሲያ ባለፉት ሳምንታት በዩክሬን ከተሞች በሰው አልባ አውሮፕላኖች እና በሚሳዔሎች የምትፈጽመውን ጥቃት አጠናክራ በመቀጠል በሰላማዊ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሳለች።

በሰኔ መጀመሪያ ላይ ከተጠናቀቀው የመጨረሻው ዙር ንግግር በኋላ የዩክሬን ተደራዳሪዎች ሩሲያ ዳግም "ያለ ቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም" እንዲደረግ የሚለውን ሃሳብ ውድቅ ማድረጓን ተናግረዋል።

ኪየቭ እና የአውሮፓ አጋሮቿ እንዲሁም አሜሪካ የሚፈልጉት ያለምንም የቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ነው።

ሩሲያ በበኩሏ ዩክሬን ተጨማሪ ግዛት እንድትሰጣት እና ሁሉንም የምዕራባውያን ወታደራዊ ድጋፍን መቀበል እንድታቆም ጠይቃለች።

በወቅቱ ዜሌንስኪ ሞስኮን "ቀጣዩ ስብሰባ ውጤት አልባ እንዲሆን የተቻለውን ሁሉ እያደረገች ነው" ሲሉ ወንጅለዋታል።

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዩክሬንን የወረሩት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በየካቲት 2022 ነበር።

ሩሲያ አሁን እአአ በ2014 በኃይል የያዘችውን ደቡባዊ ክሬሚያን ጨምሮ 20 በመቶ የሚሆነውን የዩክሬን ግዛት ትቆጣጠራለች።