'ከማህፀን ጀምሮ ቀብድ የተከፈለባቸው' እና በ600 ዶላር ገደማ የሚሸጡት የኢንዶኔዢያ ሕጻናት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኢንዶኔዥያ ፖሊስ ከ2023 ጀምሮ በሲንጋፖር ቢያንስ 25 ጨቅላ ሕፃናትን ሸጧል የተባለውን ዓለም አቀፍ ሕገ ወጥ የሕጻናት አዘዋዋሪ ቡድን አገኘ።
ባለስልጣናት በዚህ ሳምንት በኢንዶኔዥያ በፖንቲያናክ እና ታንገርንግ ከተማ ከቡድኑ ጋር ግንኙነት ያላቸውን 13 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን፣ እንዲሁም አንድ ዓመት አካባቢ የሚሆናቸው በሕገወጥ መንገድ ሊዘዋወሩ የነበሩ ስድስት ሕጻናትን ማዳናቸውን ተናግረዋል።
የዌስት ጃቫ ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ዋና ዳይሬክተር ሱራዋን ለቢቢሲ ኒውስ ኢንዶኔዥያ እንደተናገሩት "ሕፃናቱ መጀመሪያ የተቀመጡት በፖንቲያናክ ሲሆን ወደ ሲንጋፖር ከመላካቸው በፊት የኢሚግሬሽን ሰነዶቻቸውን አስተካክለው ነበር።"
ቢቢሲ በጉዳዮ ላይ አስተያየት እንዲሰጥ የሲንጋፖር ፖሊስን እና የሲንጋፖርን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴርን የጠየቀ ቢሆንም ምላሽ አላገኘም።
ቡድኑ ዒላማ ያደረገው ልጃቸውን ማሳደግ አይፈልጉም ያላቸውን ወላጆች ወይም ነፍሰ ጡር እናቶችን ነበር።
ሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎቹ እንደ ዋትስአፕ የመሳሰሉ የግል መልዕክት መለዋወጫዎችን ከመክፈታቸው በፊት በፌስቡክ ግንኙነት እንደሚጀምሩ ፖሊስ ገልጿል።
ሱራዋን እንዳሉት "አንዳንድ ሕፃናት ገና በማኅፀን ውስጥ እያሉ ቀብድ የተከፈለባቸው ናቸው።"
"ከተወለዱ በኋላ ለወሊድ የወጡ ወጪዎች ይሸፈናሉ፤ ከዚያም የካሳ ገንዘብ ይከፈላል፤ ሕጻናቱም ይወሰዳሉ።"
ፖሊስ እንዳስታወቀው የቡድኑ አባላት በሕገወጥ መንገድ የሚዘዋወሩ ሕፃናትን የሚከታተሉ ቅጥረኞችን ጨምሮ፤ተንከባካቢዎች እና ያስጠለሏቸው ሰዎች፤እና ሌሎች እንደ የቤተሰብ ካርድ እና ፓስፖርት ያሉ የተጭበረበሩ ሰነዶችን እንደሚያዘጋጁ አስረድተዋል።
ሕፃናቱ ከእናቶቻቸው ከተወሰዱ በኋላ ከሁለት እስከ ሦስት ወራት ለሚደርስ ጊዜ ለተንከባካቢዎች ይሰጣሉ።
ከዛ በመቀጠልም ወደ ጃካርታ እና የልደት የምስክር ወረቀታቸው፣ፓስፖርታቸው እና ሰነዶቻቸው ወደሚዘጋጁበት እንደሚላኩ ፖሊስ ተናግሯል።
ሕጻናቱ እያንዳንዳቸው ከ11 ሚሊዮን የኢንዶኔዥያ ሩፒ ( 673 ዶላር) እስከ 16 ሚሊዮን የኢንዶኔዥያ ሩፒ መሸጣቸውን ጨምረው ገልጸዋል።
በቁጥጥር ስር ከዋሉት ሰዎች መካከል ጥቂቶቹ እንደሚሉት፣ ቡድኑ ቢያንስ 12 ወንድ እና 13 ሴት ሕፃናትን በአገር ውስጥ እና በውጭ ሽጧል።
አብዛኛዎቹ ከኢንዶኔዥያ ምዕራብ ጃቫ ግዛት ከተለያዩ ወረዳዎችና ከተሞች የመጡ ናቸው።
የኢንዶኔዥያ ፖሊስ ሐሙስ ዕለት እንዳስታወቀው "አፋጣኝ ተግባራቸው" በሲንጋፖር ውስጥ ያሉ ሕጻናቱን በጉዲፈቻ የወሰዱ ሰዎችን ማግኘት ነበር ።
ሱራዋን ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት "ከሄዱት ሕፃናት ጋር መረጃውን እናመሳክራለን፣ ስለዚህ ማን ከአገር እንደወጣ፣ እነማን አብረዋቸው እንደነበሩ፣ መቼ እንደሄዱ እና በጉዲፈቻ የተቀበሏቸው እነማን እንደሆኑ እናውቃለን"።
ፖሊስ ያሰባሰበው አብዛኛው መረጃ እንደሚያመለክተው ሕፃናቱ ዜግነታቸውን ቀይረዋል፤ ባለሥልጣናቱ አሁንም ፓስፖርታቸውን እየፈለጉ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሱራዋን ቀደም ሲል ለቢቢሲ ኢንዶኔዥያ እንደተናገሩት ሕፃናቱ የተገኙት በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች እና በወላጆች መካከል በተደረገ ስምምነት ሲሆን እስካሁን አንድም በአፈና የተወሰደ ሕጻን የለም።
ልጃቸው እንደታገቱ የገለጹ ወላጆች ይህን ያደረጉት ደላላው መክፈል ባለመቻሉ ነው ብለዋል።
ቢያንስ አንዳንድ ወላጆች በገንዘብ ችግር ምክንያት ልጆቻቸውን ለመሸጥ ተስማምተው ሊሆን ይችላል ተብሎ ይገመታል። እነሱም በወንጀል ሊከሰሱ ይችላሉ ሲሉ ሱራዋን ተናግረዋል።
"በወላጆች እና ወንጀለኞች መካከል ስምምነት እንደነበረ ከተረጋገጠ በልጆች ጥበቃ ወንጀሎች እና በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ሊከሰሱ ይችላሉ" ሲሉ አብራርተዋል።
የኢንዶኔዥያ ፖሊስ በውጭ አገር የሚገኙትን የሕገ ወጥ ሕጻናት አዘዋዋሪ ቡድን አባላትን እና ገዥዎችን ለመያዝ ከኢንተርፖል እና ከሲንጋፖር ፖሊስ እርዳታ ጠይቋል።
"የሚፈለጉትን ወንጀለኞችን እንዘረዝራለን" ሲሉ ሱራዋን አብራርተዋል።
"በተጨማሪም ኢንተርፖል ወንጀለኞቹ ያሉበትን እንዲጠቁመን ወይም በእነዚያ አገራት ያሉ የሕግ አስከባሪ አካላት በቁጥጥር ስር እንዲያውሏቸው እንጠይቃለን።"
የሕጻናት ዝውውር ቡድን በተለምዶ ተስፋ አስቆራጭ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ያሉ ሴቶችን ዒላማ ያደረገ ነው ሲሉ የኢንዶኔዥያ የሕፃናት ጥበቃ ኮሚሽን ኮሚሽነር አይ ራህማያንቲ ተናግረዋል።
"ለምሳሌ፣ በጾታዊ ጥቃት፣ በባሎቻቸው የተከዱ፣ወይም በድንገተኛ ግንኙነት ያረገዙ ሴቶች" ሲሉ ለቢቢሲ ኢንዶኔዥያ ተናግረዋል።
በሕክምና ድንገተኛ አደጋዎች እና በአስገድዶ መድፈር ምክንያት ከሚመጡ እርግዝናዎች በስተቀር በኢንዶኔዥያ ውስጥ ፅንስ ማስወረድ ሕገ ወጥ ነው።
አይ ራህማያንቲ እንዳሉት የሕጻናት ዝውውር ቡድን ብዙውን ጊዜ ራሳቸውን እንደ የወሊድ ክሊኒኮች፣ ወላጅ አልባ ሕፃናት ማሳደጊያዎች ወይም ለችግር ተጋላጭ ሴቶችን እና ሕፃናትን የሚንከባከቡ ማኅበራዊ መጠለያዎች አድርገው ያቀርባሉ ብለዋል።
"እነዚህ ክሊኒኮች ወይም መጠለያዎች መጀመሪያ ላይ ልጅዎን መውለድ እና ወደ ቤት መውሰድ ይችላሉ' የሚሉ የርህራሄ የሚመስሉ ቋንቋዎችን ይጠቀማሉ። ነገር ግን እንደ እውነቱ ከሆነ በገንዘብ ደልለው የሕፃኑን የማሳደግ መብት በሕገወጥ መንገድ ያስተላልፋሉ" ሲሉ ያብራራሉ።
በኢንዶኔዥያ የሚሸጡ ሕፃናትን ቁጥር በተመለከተ ይፋዊ መረጃ ባይኖርም፣ የኢንዶኔዥያ የሕፃናት ጥበቃ ኮሚሽን በራሱ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀሎች ላይ ያለው መረጃ አዝማሚያው ቀጣይነት ያለው እና እያደገ መሆኑን ያሳያል።
እአአ በ 2020 የኢንዶኔዥያ የሕፃናት ጥበቃ ኮሚሽን 11 ሕፃናትን የሕገወጥ ጉዲፈቻ ሰለባ መሆናቸውን የመዘገበ ሲሆን፣ በ2023 በሕገወጥ ጉዲፈቻ ሽፋን የሕፃናት ጠለፋ እና ዝውውር ጋር በተያያዘ 59 ጉዳዮችን ተመልክቷል።
በ2024 የኢንዶኔዥያ የሕፃናት ጥበቃ ኮሚሽን እንደ ዴፖክ፣ ዌስት ጃቫ እና ባሊ ባሉ አካባቢዎች ሕጻናት ለመሸጥ ቀርበው መገኘታቸው ይናገራል።
ጨቅላዎቹ በተለያየ ዋጋ ይሸጡ እንደነበር ኃላፊዋ ይናገራሉ።
"በጃቫ ውስጥ [ዋጋው] 11 ሚሊዮን እና 15 ሚሊዮን የኢንዶኔዥያ ሩፒ መካከል ነው፤ በባሊ ውስጥ ከ20 ሚሊዮን እስከ 26 ሚሊዮን ሊደርስ ይችላል" ብለዋል ኃላፊዋ።
"ዋጋው በበርካታ አመልካቾች ላይ የተመሰረተ ነው፤ ከእነዚህም አንዱ የሕፃኑ አካላዊ ገጽታ ነው።"















