በተደጋጋሚ የመድፈር ወንጀል የፈጸመው ደቡብ አፍሪካዊ 42 የእድሜ ልክ እስራቶች ተፈረደበት

የፎቶው ባለመብት, NPA
*ማሳሰብያ- ይህ ዘገባ አእምሮን ሊረብሹ የሚችሉ ዝርዝሮችን ይዟል።
እድሜያቸው ከዘጠኝ ዓመት ጀምሮ የሚገኙ ሴቶችን የደፈረው እና ሕጻናት ላይ ጥቃት ያደረሰው ደቡብ አፍሪካዊ 42 የእድሜ ልክ እስራቶች ቅጣት ተጣለበት።
ንኮሲናቲ ፓካቲ እአአ ከ2012 እስከ 2021 ባሉት ጊዜያት ውስጥ በፈጸማቸው 90 የመድፈር ወንጀል ክሶች የቀረበበት ሲሆን በሁሉም ጥፋተኛ ተብሏል።
የ40 ዓመቱ ወንጀለኛ አንዳንዴ የመድፈር ወንጀሉን ሲፈጽም ሌሎች ታዳጊ ወንድ ሕጻናት እንዲመለከቱት እንዲሁም ሴት ጓደኞቻቸውን እንዲደፍሩ ያደረግ እንደነበር የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ አቃቢያነ ሕጎች ባለሥልጣን አስታውቋል።
ፓካቲ ወንጀሎች የፈጸመው ከጆሀንስበርግ ምስራቃዊ ክፍል በምትገኘው አነስተኛ ከተማ ነው።
አርብ እለት የጆሀንስበርግ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ፓካቲ ላይ በመድፈር፣ በማገት፣ በስርቆት እንዲሁም ጥቃት በመፈጸም በሚሉ ክሶች 42 የእድሜ ልክ እስር ቅጣቶችን አስተላልፏል።
በደቡብ አፍሪካ ተደራራቢ የእድሜ ልክ ቅጣቶች የሚተላለፉት በርካታ ተጠቂዎች ላይ የሚደርሱ አሰቃቂ ወንጀሎች ተፈጽመው ሲገኙ ነው።
የደቡብ አፍሪካ አቃብያነ ሕጎች ባለሥልጣን እንዳለው የችሎቱ ዳኞች ፓካቲ “ምን ዓይነት ፀፀት ያልታየበት እና ከመታረም ያለፈ” መሆኑ ላይ ተስማምተዋል።
ፓካቲ ወንጀሉን ያደረሰባቸው በርካታዎቹ ታዳጊ ሕጻናት እድሜያቸው ዘጠኝ ዓመት እና ከዚያ በላይ ሲሆን ገና በትምህርት ላይ ያሉ ናቸው።
የፓካቲ ወንጀል ሰለባ የሆነችው በእድሜ ትልቋ ሴት እድሜዋ 44 ነው ተብሏል።
የአቃብያነ ሕጎች ባለስልጣን ፓካቲ ጥቃት ያደረሰባቸውን ታዳጊዎች በሙሉ ዒላማ የሚያደርገው ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱ አልያም ሲመለሱ ነው።
ፓካቲ የተወሰኑትን የጥቃቱን ሰለባዎች በገዛ ቤታቸው በመሄድ እና ቤታቸው የሚገኙ ኤሌክትሮኒክሶችን ለመጠገን በሚል ከገባ በኋላ መሆኑን መግለጫው ያሳያል።
ፓካቲ በ2021 ፖሊስ በቁጥጥር ስር ሊያውለው በተኮሰበት ጥይት የተነሳ እግሮቹን አጥቷል።
በደቡብ አፍሪካ በርካታ የመድፈር እንዲሁም ግድያን ጨምሮ በርካታ አሰቃቂ ወንጀሎች እየጨመሩ መጥተዋል።
ከባለፈው ዓመት ከሚያዝያ እስከ ሰኔ ወር ባሉት ጊዜያት ብቻ ከ9300 በላይ የመድፈር ወንጀሎች ተመዝግበዋል።
የፖሊስ መዝገብ አንደሚያስረዳው ይህ ወንጀል ከዚህ ቀድመ ከነበረው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ0.6 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።












