ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሩሲያ 48 ሰዎችን የጫነ አውሮፕላን ተከስክሶ ሁሉም ተሳፋሪዎች ሞቱ
በሩሲያ ሩቅ ምሥራቃዊው አሙር ግዛት በሚገኝ ጥቅጥቅ ያለ ጫካ ውስጥ የተከሰከሰው የአንጋራ አየር መንገድ አውሮፕላን ሁሉም ተሳፋሪዎች ሕይወታቸው ማለፉን የሀገሪቱ ባለሥልጣናት አስታወቁ።
42 ተሳፋሪዎችን እና ስድስት ሠራተኞችን ይዞ የነበረው አንቶኖቭ ኤ ኤን-24 አውሮፕላን፤ ከቻይና ድንበር አቅራቢያ ከሚገኘው ብለጋቪየሽክስ ተነስቶ ወደ ቲንዳ አውሮፕላን ማረፊያ ሲቃረብ ከራዳር እንደተሰወረ ተገልጿል።
ኋላ ላይም የሩሲያ የሲቪል አቪዬሽን ሄሊኮፕተር ከቲንዳ 16 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ተራራ ላይ የተቃጠለ አውሮፕላን እንዳገኘ ተነግሯል።
የአሙሩ ግዛት ገዢ ቫሲሊ ኦርሎቭ፤ አውሮፕላኑ ውስጥ ከነበሩት ተሳፋሪዎች ውስጥ አምስቱ ልጆች እንደሆኑ እና ለሟቾቹ ሦስት የሐዘን ቀናት መታወጁን ተናግረዋል።
የአደጋ ጊዜ ባለሥልጣናት እንደሚናገሩት፤ የአካባቢው ራቅ ያለና ረግራጋማ ተፈጥሮ፤ የነፍስ አድን ሠራተኞች ወደ ስፍራው ለመድረስ አንድ ሰዓት ገደማ እንዲፈጅባቸው አድርጓል።
አደጋውን በተመለከተ እየተደረጉ ያሉ የመጀመሪያ ደረጃ ምርመራዎች ክስተቱ የተፈጠረው በመጥፎ የአየር ሁኔታ፣ በፓይለት ስህተት ወይም በቴክኒክ ብልሽት መሆኑን ለማረጋገጥ እየሞከሩ ነው።
ከሩሲያ ደቡብ ምሥራቅ የተነሳው የኤ ኤን-24 አውሮፕላን የተከሰከሰው ለመዳረሻው በተቃረበበት ሰዓት ነው።
አደጋው በደረሰበት ወቅት ደመና የነበረ ሲሆን፣ አውሮፕላኑ በአየር ማረፊያው ላይ ለማረፍ ያልተሳካ ሙከራ ማድረጉን ተነግሯል።
የአየር ማረፊያው ሠራተኞች ለሁለተኛ ለማረፍ እንዲሞክር ዝግጅት እያደረጉ ሳለ የራዳር ግንኙነቱ እንደተቋረጠ ተገልጿል።
ከተሳፋሪዎቹ መካከል አብዛኞቹ በሀገሪቱ የሩቅ ምሥራቅ የሚገኝ የሩሲያ የባቡር ድርጅት ይሠሩ የነበሩ ናቸው።
የተከሰከሰው አንቶኖቭ 24 አውሮፕላን ወደ 50 ዓመት ዕድሜ ያለው ሲሆን፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ንድፉ የተሠራው በሶቪየት ዘመን ዩክሬን ኪየቭ ውስጥ ነው።
ይሁንን እንጂ ይህ ሞዴል ለበርካታ ዓመታት ዩክሬን ውስጥ አገልግሎት ላይ አልዋለም።
ባለሥልጣናት፤ አውሮፕላኑ በቅርቡ የተደረገለትን የቴክኒክ ምርመራ አልፏል።
የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ግን አውሮፕላኑ ከአውሮፓውያኑ 2018 ጀምሮ በአራት አደጋዎች አጋጥመውት እንደነበር ለዜና ወኪሎች ገልጿል።
ከሰባት ዓመታት በፊት አውሮፕላኑ ከአየር ማረፊያ መንደርደሪያ አልፎ በመሄዱ የመብረቅ መከላከያ ምሰሶ ጋር ተጋጭቶ የግራ ክንፉ ተጎድቶ እንደነበር ተዘግቧል።
ሌሎች ኤ ኤን-24 አውሮፕላኖችም በተመሳሳይ የሰው ሕይወት ያለፈባቸው አደጋዎች አጋጥሟቸዋል።
ኤ ኤን-24አርቪ አውሮፕላን ሐምሌ 2019 በኒዥንያንጋርስክ አየር ማረፊያ ሲያርፍ ከአውሮፕላን ማረፊያው መንገድ ወጥቶ ነበር። በዚህ አደጋ ሁለት የበረራ ሠራተኞች ሞተዋል።
በአውሮፓውያኑ 2011 ሌላ የአንጋራ አን-24 አውሮፕላን ሳይቤሪያ ውስጥ በኦብ ወንዝ ላይ ወድቆ ሰባት ተሳፋሪዎችን ገድሏል።
ይህንን አደጋ ተከትሎ በወቅቱ ፕሬዝዳንት የነበሩት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ፤ አሁንም በሩሲያ አገልግሎት የሚሰጡ ኤ ኤን-24 አውሮፕላኖች መቆም አለባቸው ብለው ነበር።