በርካታ ሴቶች የፍቅረኛቸውን ፎቶ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ማጋራት የማይፈልጉት ለምንድን ነው?

ታዋና

የፎቶው ባለመብት, Tawana Musvaburi

የምስሉ መግለጫ, ታዋና

ታዋና ሙስቫቡሪ በኢንስታግራም ገጿ 33,000 ተከታዮች አሏት። ተከታዮቿ ስለግል ሕይወቷ ሁሉንም ነገር ጠንቅቀው የሚያውቁ ይመስላቸዋል።

አብዛኞቹ ግን የፍቅር አጋሯ ማን እንደሆነ መረጃ የላቸውም። የፍቅር አጋር እንዳላት የሚገልጹ ጥቆማዎች መስጠቷ አልቀረም።

እሷ እና የፍቅር አጋሯ ወይን እየጠጡ፣ ብርጭቆ ሲያጋጩ የሚያሳይ ምሥል አጋርታለች።

የ24 ዓመቷ ታዋና የፍቅረኛዋን ፎቶ አታሳይም። "እንደ ሴትነቴ ሁሉም ነገር በቁጥጥሬ ሥረ መሆኑን ማሳየት እፈልጋለሁ" ትላለች።

የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዋ ታዋና አብዛኛውን ሥራዋን ስታከናውን የፍቅር አጋሯን አታሳትፍም።

"ስኬታማ የሆንነው በወንድ እርዳታ እንደሆነ ሊሰማን አይገባም። ሁሉንም ነገር ያሳካሁት በግል ጥረቴ ነው ስል ደስታ ይሰማኛል" ስትል ትገልጻለች።

ከፍቅረኛዋ ጋር ትዳር ብትመሠረትም ግንኙነታቸውን ይፋ ለማድረግ ፈቃደኛ አይደለችም።

"ቀለበት ስላሰርን ብቻ ስለ ፍቅር ግንኙነቴ በማኅበራዊ ሚዲያ አልጽፍም" ትላለች።

የፍቅረኛቸውን ፎቶግራፍ በማኅበራዊ ሚዲያ መለጠፍ ከማይሹ በርካታ ሴቶች መካከል ታዋና አንዷ ናት።

ታዋና

የፎቶው ባለመብት, Tawana Musvaburi

የምስሉ መግለጫ, ታዋና

ከወር በፊት ቮግ መጽሔት ስለጉዳዩ ዘገባ አስነብቧል። 'ፍቅረኛ መያዝ አሳፋሪ ሆኗል?' የሚል ርዕስ የተሰጠው ዘገባ በቲክቶክ እና ኢንስታግራም ላይ መነጋገሪያ ሆኗል።

የዘገባው ፀሐፊ ቻንቴ ጆሴፍ እንደምትለው ከተቃራኒ ፆታ ጋር የፍቅር ግንኙነት የሚመሠርቱ ሴቶች ስለ ግንኙነታቸው በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እምብዛም ሲናገሩ አይሰማም።

ፍቅረኛ መያዝ ያለውን "ማኅበራዊ ጠቀሜታ" ቢወዱትም "ከወንድ ጓደኛቸው ውጪ ስለ ሌላ ነገር ማሰብ የማይችሉ" ተብለው መሳል አይፈልጉም።

በማኅበራዊ ሚዲያ የፍቅረኛን ምሥል መለጠፍ "አሳፋሪ" እና በዘመነኛ አስተሳሰብ "እምብዛም ክብር የማያሰጥ" እየሆነ መምጣቱን ፀሐፊዋ ትናገራለች።

"የወንድ ጓደኛ መያዝ እንደ ስኬት መታየቱ አክትሞለታል። ቀደም ባለው ዘመን እንደሚታሰበው የተሻለች ሴት አያደርገንም" ትላለች።

ሴቶች ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የፍቅረኛቸውን ምሥል መለጠፍ ከማይፈልጉበት ምክንያት አንዱ "አባታዊ የሆነው እና ሴቶችን የሚጨቁነውን ሥርዓት ለመገዳደር" እንደሆነ ታስረዳለች።

ስቴፋኒ

የፎቶው ባለመብት, Stephanie Yeboah

የምስሉ መግለጫ, ስቴፋኒ

"ብዙ ሴቶች እጮኛ ወይም ባል መያዝ መልካም ነው ይላሉ። አሁን ባለንበት የፖለቲካ ዐውድ ግን ከወንዶች ጋር ያለንን ግንኙነት ቆም ብለን ማጤን አለብን" ስትል ታብራራለች።

ስቴፋኒ ያቦሀ 'ሳውዝ ለንደን' የተባለ መጽሐፍ አሳትማለች። የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪም ናት።

የወንድ ጓደኛዋን ፎቶ በኢንስታግራም ላይ መለጠፏ ይጸጽታታል።

"የወንድ ጓደኛ ካለሽ አንቺ የምትይው ነገር ለእኛ ትርጉም መስጠቱን ያቆማል ብለው ብዙዎች ገጼን መከተል አቆሙ። በአንድ ቀን 1,000 ሰዎች የኢንስታግራም ገጼን መከተል አቁመዋል" ትላለች።

የማኅበራዊ ሚዲያ ተከታታዮች ስለ ወንድ የፍቅር አጋሮች መስማት ብዙም እንደማይጥማቸው ታስረዳለች።

"ስለ ፍቅር ግንኙነት ሲወራ ደስ የማይል ነገር አለው። ሰዎች ሲመለከቱት አንዳች የሚጎረብጥ ስሜት ይፈጥርባቸዋል" ትላለች።

ዶ/ር ጂሊያን ብሩክስ

የፎቶው ባለመብት, Dr Gillian Brooks

የምስሉ መግለጫ, ዶ/ር ጂሊያን ብሩክስ

በኪንግስ ኮሌጅ ለንደን የማኅበራዊ ሚዲያ ይዘት እና ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ተመራማሪ ዶ/ር ጂሊያን ብሩክስ እንደምትለው የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች "የሚሸጡት ገጽታ" አላቸው።

"የሚያሳዩትን ገጽታ የሚከተሉ ሰዎች ስላሉ መጀመሪያ ላይ ካስተዋወቁት ማንነት የተለየ አዲስ ገጽታ ለማምጣት ያስቸግራል" ስትል ታብራራለች።

"ከተጽዕኖ ፈጣሪዎቹ የሚጠብቁትን ዓይነት መረጃ ካላገኙ የሚከታተላቸው አይኖርም። የሚጠበቅባቸውን ዓይነት ይዘት የማይሠሩ ከሆነ ገጻቸውን የሚከተል ሰውም አይኖርም" ስትልም ታክላለች።

የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች የፍቅር አጋሮቻቸው ላይ "የተመረኮዘ ሕይወት ያላቸው" ሆነው መታየት አይፈልጉም።

ከማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ባሻገር የፍቅር ግንኙነታቸውን በአደባባይ ይፋ ማድረግ የማይፈልጉ ሴቶች ቁጥር እየተበራከተ ነው።

ዶ/ር ጌንዶሊያን ሲድማን

የፎቶው ባለመብት, Dr Gillian Brooks

የምስሉ መግለጫ, ዶ/ር ጌንዶሊያን ሲድማን
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሚሊ ከአምስት ዓመት ፍቅረኛዋ ጋር ቀለበት አስራለች። የ25 ዓመቷ ሚሊ የእጮኛዋን ፎቶ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ማውጣት አትሻም።

"ሕይወቴ እሱ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ሰው እንዲያስብ አልፈልግም። የፍቅር ግንኙነታችን የመላው ሕይወቴ ማጠንጠኛ አይደለም" ትላለች።

ማኅበራዊ ሚዲያ ስለ ሰዎች ማንነት የሚፈጥረው ምሥል የተገደበ እንደሆነ ትናገራለች።

"የፍቅረኛዬ ፎቶ እና ጥንዶች መሆናችን በማኅበራዊ ሚዲያ ሲገለጽ ከእሱ ውጪ ስለሌላ ነገር ማሰብ የማልችል ሰው ያስመስለኛል" በማለት ሚሊ ታክላለች።

የ20 ዓመቷ ሻርለት ለሁለት ዓመታት በፍቅር ግንኙነት ቆይታለች። ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የፍቅረኛዋን ፎቶ የማታጋራበት ብዙ ምክንያት አላት።

"በኢንስታግራም ላይ ሊለጠፍ የሚችል ፎቶ የለንም። በዚያ ላይ የእኔ እና የሱ ፍቅር የግል ጉዳያችን ነው" ስትል ምክንያቶቿን ትዘረዝራለች።

"ፎቷችንን ስለጥፍ እዩኝ እዩኝ ማለት ነው የሚመስለው" ስትልም ታክላለች።

የ21 ዓመቷ አሪታም በሻርለት ሐሳብ ትስማማለች። የፍቅር አጋሯን ምሥል መለጠፍ "ዐይን ውስጥ ይከተዋል" ብላ ታምናለች።

"ቡዳ ይበላዋል ብዬ አስባለሁ። ሰዎች እሱን አይተው እንዲቀኑም አልፈልግም። ሆነ ብለው ባይሆንም ሳያስቡት ቅናት ሊሰማቸው ይችላል" ትላለች።

በሚቺጋን ስቴት ዩኒቨርስቲ የማኅበራዊ ሥነ ልቦና ባለሙያዋ ዶ/ር ጌንዶሊያን ሲድማን በይነ መረብን ያማከለ የፍቅር ግንኙነት ላይ ጥናቶች ሠርታለች።

በበይረ መረብ ላይ የሚወጡ መረጃዎች ዘለግ ላለ ጊዜ እንደሚቆዩ በማሰብ ብዙዎች ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ግላዊ መረጃ መለጠፍ እንደማይፈልጉ ታስረዳለች።

"አሁን ላይ ብዙዎች በማኅበራዊ ሚዲያ የሚያጋሩትን መረጃ መጠን እየቀነሱ ነው። የሚለጥፉት ነገር በበይነ መረብ እስከ ወዲያኛው እንደሚቆይ ያውቃሉ። መረጃዎቹን ማጥፋት ስለማይቻል ጥንቃቄ ያሻል" ስትልም ባለሙያዋ ትመክራለች።